በጥንታዊ የጋርዮሽ ስርአት የመጀመርያው የሰው ልጆች ስራ አደንና ፍራፍሬ መልቀም ነበር፤ አንድ ወንድ እና ሴት ተጣምረው ዱር ለዱር ይንከራተታሉ። እንጆሪ ለቅመው ወይም የዱር ፍየል አድነው በጋራ ይበላሉ፤ከእለታት አንድ ቀን ሴቲቱ ታረግዛለች፤
ሆዷ ገፍቶ እንደ ድሮው ዛፍ መውጣት ወይም መስክ በሩጫ ማቋረጥ በሚሳናት ጊዜ ባልየው አንድ ዋሻ ውስጥ ጥሏት ወይም አስጠልሏት ይሄዳል፤ ገራም ከሆነ ዞሮ ዞሮ ይመለሳል ፤ የተረገመ ከሆነ እንደወጣ ይቀራል፤ ቀስ በቀስ ሴቷ ባንድ ቦታ ልትረጋ የተፈጠረች መሆኑን ትረዳለች፤ ጎጆም ትቀልሳለች።
ባንድ ቦታ ረግቶ መቀመጥ በሴት ሆርሞን ውስጥ ያለ ነገር እንደሆነ ሁሉ ፤ መቅበዝበዝ በወንድ ልጅ ደም ውስጥ ያለ ነገር ነው። ሲሄድ ውሎ ሲሄድ የሚያድር ወንድ እንጂ ወንዝ አይደለም፤ ወንድ ልጅ የእመቤቶች ለማዳ እንስሳ ከመሆኑ በፊት ባንዲት ጣራ ስር እሺ ብሎ እሚቸከል ፍጡር አልነበረም፤ እንዲያም ሆኖ ፤ሰበብ እየፈጠረ፤ወታደር፤(ዋትቶ- አደር) ሲራራ ነጋዴ፤ ፖስታ አመላላሽ ፤ አሳሽና ሀዋርያ አድርጎ ራሱን እየሾመ የመሄድ ሱሱን ሲያረካ ኑሯል።
ቤት መስራትና መንደር ምስረታን የጀመሩት ሴቶች ሲሆኑ ድልድይና ጎዳናን መስራት የጀመሩት ደሞ ብጤዎቼ ይመስሉኛል ፤ ስራ ላይ ራሱ ተመልከቺ ፤ አሁን ወንድ ልጅ ምንም ቢገደድ ሁለት ሰአት ሙሉ ብቅል ሊፈጭ ይችላል? ራሱን በወፍጮው ልጅ ፈጥፍጦ ቢገል ይቀለዋል፤ ታይፒስት መሆን ይችላል? ወንድ ልጅ ባንድ ቦታ ቁጭ ብሎ የሚሰራው ስራ አለ? እንጃ! ምናልባት ልብስ ሰፊነት ? እሱንም ቢሆን ታግሶ የተቀበለው ከታች እግሩን ማንቀሳቀስ ስለሚችል ነው፤ ልብ ብለን ካየነው የሽመና ስራም የቅምጥ ስራ አይደለም ፤ሰውየው ባይንቀሳቀስ ቆለጡ እሱን ወክሎ ወድያ ወዲህ ይላል፤
ምን ልል ፈልጌ ነው? ቀሳው በዚህ ከቀጠለ ወንዶች ከነጨርቃችን እናብዳለን ፤ሴቶች እንደነበሩት ይቀጥላሉ፤ግፋ ቢል ወንዱ አብዶ ሲፈነዳ ፍንጣሪው ቢነካቸው ነው፤
እኔኮ በራሴ አየዋለሁ፤ እግሬ ቢታሰር አእምሮየ ይንቀዠቀዣል፤ ሁለት የዩቲውብ ሳንዱቅ ከፍቼ አንዱን ሳላይ ወደ ሌላው እዘልላለሁ። ልደቱ አያሌውን መስከረም ሰላሳ ላይ አስደግፌ ወደ ባህሩ ቃኘ የሄድኩበት ፍጥነት ጉግልን ራሱ ሳያሳስበው አልቀረም። what is the attention deficient hyperactivity disorder የሚል እርእስ ያለው ሌክቸር ሪኮመንድ አደረገኝ፤
በነገራችን ላይ እያንዳንድሽ እግዜር ባያይሽ ጉግል ያይሻል፤ ባለፈው፤ ባለንጀራየ በየነ ገላውን ታጥቦ፤ መቸም ብቻየን ነኝ ብሎ፤ ላፕቶፑን ሳይዘጋ ታችኛውን ላጨ። ከዛ ዩቲውብ ገብቶ ባህላዊ ዜማ እየሰማ እያለ Recommended for you እሚል መጣለት፤ እና ጎግል የመረጠለትን ቢድዮ ርእስ ሲሾፈው ምን ይላል፤ How to enlarge your penis without a medical aid .
አርፌ ባህሩ ቃኘን ባዳምጥስ ?
እህ እንዴት ነው ገዳ-ዎ
እንዴት ነው ገዳ-ዎ
እንዴ?😳 ባህሩ ቃኘ ስለገዳ ስርአት መዝፈናቸውን እንዴት እስከዛሬ ልብ ሳልል ቆየሁ?