Tidarfelagi.com

ኢትዮጵያ በአማልክት እና በተከታዮቻቸው ዓይን

“… እናቴ ሆይ በዚህች በምባርካት አገር በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሰዎችን እስከ ዓለም መጨረሻ ድረስ አሥራት ይሆኑሽ ዘንድ ሰጥቼሻለሁ። እናቴ ሆይ አሁንም ወደዚያች አገር እንሄድ ዘንድ ተነሺ። ደሴቶችና የተቀደሱ፣ ወንዞችዋ ያማሩ፣ ውሃዎችዋ የጠሩ፣ ዛፎችዋና ተራራዎችዋ የተዋቡ ናቸውና አሳይሻለሁ አለኝ።” ይላል አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል በሚል ርዕስ ስል ግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም የሚናገር፤ማ ርያም ከመድሃኔዓለም የተበረከተላት ስጦታ የሚል መጽሐፍ።

ልጅ ሳለሁ፣ የእስራኤል ስም በተደጋጋሚ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሶ ሳነብ መንፈሳዊ ቅናት ያድርብኝ ነበር። የማላምንበትን እምነት በሚሰብክ ሃይማኖት ውስጥ እንኳን ስለ ኢትዮጵያ የሚነገር ቃል ስሰማ ይነዘረኛል፤ የህፃናት የሚመስል ንፁህ ፈገግታ ልቤ ውስጥ የሚመላለስ ይመስለኛል። በአማልክት ዘንድ የምትወደድ፣ በአማልክት ዘንድ ሞገስ ያገኘች አገር እንዳለቺኝ ሳስብ ከፍ ከፍ የማለት ስሜት ይሰማኛል።

በነቢያት ዘንድ የተወደደች፣ ከነበሩት ሁሉ የተሻለች ስለመሆኗ ብዙ የሃይማኖት ድርሳናት አስነብበውን የለ …
የክለዳውያን ንጉስ የእስራኤልን ልጆች በማረኳቸው ጊዜ እግዚአብሔር ኤርምያስን እንዲህ ተናገረው። “ከኃጢአት ብዛት የተነሳ አገሪቱን አጠፋታለሁና አንተ ውጣ” እንዲህ ሲለው የነብዩ ጭንቅ ሌላ ነበር፣ የአገሪቱ መጥፋትና፣ የእርሱ ከተማው መራቅ ብቻ አልነበረም ያሳሰበው።
“ኤርምያስም፣ ጌታዬ እለምንሃለሁ ሕዝቡን ብዙ ዘመን ለጠበቃቸው ባርያህ ካገሩ ሰው ሁሉ ለጠበቀኝ ለኢትዮጵያዊው ሰው ለአቤሜሊክ የማደርገውን ግለጥልኝ ብሎ ተናገረ። እርሱ ከረግረግ ጉድጓድ አወጣኝ፣ አንድያህን ያገሪቱን ጥፋት ያይ ዘንድ አልወድለትም አለ።”
እግዚአብሔርም የኤርሜያስን ልመና ሰማ “… ህዝቡን ወዳገራቸው እስክመልሳቸው ድረስ እኔ እሠውረዋለሁ” አለና በአንዲት በለስ ዛፍ ስር፣ ለስድሳ ስድስት አመት ያህል የሚቆይ ብርቱ እንቅልፍ በአቤሜሌክ ላይ ጣለበት፣ ዓይኖቹም የኢየሩሳሌምን ጥፋት ከማየት ዳኑ።
በቅዱሳት መጻሕፍት ብቻ ሳይሆን፣ በስመጥሩው የግሪክ ባቅኔ ድርሰት ውስጥ ኢትዮጵያ በሚሞቅ ቀለም ስሟ ተጽፏል። በአንደኛው ድርሰቱ ውስጥ “ዜውስ በጠባያቸው ውስጥ ነቀፌታ ከማይገባቸው ኢትዮጵያን ዘንድ ግብር ሊያበላ በውቅያኖስ በኩል አድርጎ ትናንትና ሄዷል፣ የቀሩትም ሁሉ ተከትለውታል” ይላል።

ዜውስ የአማልክት ሁሉ አምላክ ነው ተብሎ በጥንታውያን ግሪኮች ዘንድ ግዙፍ ቦታ የሚሰጠው ፈጣሪ ነው፣ ዜውስ በዓመት ለአስራሁለት ቀናት ያህል ሌሎች አማልክትን አስከትሎ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣ ነበር ብለው ፅፈዋል፣ ኢትዮጵያን ነበር ለእረፍት የመረጡት…
አስርቱ ትዕዛዛትን ከእግዚአብሔር ልጅ ተቀብሎ ያቀበለን ሙሴ ኢትዮጵያይቱን ነበር ያገባው። የገዛ ዘመዶቹ ግን ኢትዮጵያዊቱን በማግባቱ ደስተኛ አልነበሩም፣ እናም ተናገሩት። እግዚአብሔር በነሱ መከፋት ደስተኛ አልነበረምና እንዲህ አላቸው። “… እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው። እኔ አፍ ለአፍ በግልጥ እናገረዋለሁ፣ በምሳሌ አይደለም፣ የእግዚአብሔርም መልክ ያያል፣ በባሪያዬ በሙሴ ላይ ትናገሩ ዘንድ ስለምን አልፈራችሁም” ብሎ የጋብቻውን ቅድስና አረጋግጧል።

ኢትዮጵያ በአማልክት አንደበት ስትገለፅ “ደሴቶቿ የተቀደሱ፣ ወንዞችዋ ያማሩ፣ ውሃዎችዋ የጠሩ፣ ዛፎችዋና ተራራዎችዋ የተዋቡ …” መሆናቸውን አንብበናል። ኢትዮጵያ፣ ከግሪክ አማልክቶች ሁሉ የበላይ በሆነው በዜውስ ልቦና ስትመዘን ነቀፌታ የማይገኝባቸው ህዝቦች መናኸሪ የመሆኗን በሆሜር ሥራዎች ውስጥ አንብበናል።
ኢትዮጵያ፣ ታማኝ የአምላክ ባለሙዋሎች የሚያብቡባት ማለፊያ የአትክልት ቦታ መሆኗን በሙስሊም ድርሳናት አንብበናል… ተከታዮቻቸውን በጉያዋ ሽሽግ በእንግድነት ማስተናገዷን …በተከተለው እምነት የተነሳ ብዙ ስቃይ የተቀበለውን የመጀመሪያው ሙአዚን የመሆን እድል ያገኘው ቢላል ማብቀሏን …
ሀበሻ ማለት የእግዜር ፈገግታ በርቶበት የሚውል ስፍራ ነው ተብሎ የተመሰከረለት ይመስል የየዕምነቱ ቅዱሳን ገድሎች ለኢትዮጵያ ያጨበጭባሉ። …
ኢትዮጵያ ብዙ ናት። አንብበው የማይጨርሷት ምጽሐፍ ናት። የቀራንዮ ተራራ ናት። ልጆቿ በየዕለቱ፣ በየሰዓቱ የድህነትን መስቀል ይዘው ይወጣሉ። ትከሻቸው ሰፊ ነው፣ ደንዳና ነው፣ አቀርቅረው የሚሄዱት የተሻለ ቀን እንደሚመጣ የመሸው ቀን እንደሚነጋ በማመን ነው።
ለእኛ ግን እንደዚህ አይሰማንም። ለራሳችን የምንሰጠው ክብር በየእለቱ እያነሰ ነው። “በማይመች አካሄድ እንደተጠመደ” የእምነት ሰው የጥፋተኝነት ስሜት እየተጫወተብን ነው። ራሳችንን አላከበርነውም፣ በአማልክት ዘንድ የመወደዳችንን ምስጢር ለመመርመር ፋታ አላገኘንም። ራሳችንን ንቀነዋል። በቆሸሸ ስፍራ ለብዙ ዓመታት እንዲቆም እንደተፈረደበት ሰው … ሀፍረት ወረረን።
አፈርን፣ ሀበሻ ነን ማለትን አፈርን፣ ከማይፈለግና ከተናቀ ዘር የተወለድን ይመስል ኢትዮጵያዊ መሆናችንን ማመን ጠላን፣ ኢትዮጵያዊ መባልን ጠላን …
ስለተተዳንበት ምንጭ ጠልቆ የማወቅ ትዕግሥታችንን ማን ነጠቀው፣ ስለ ጓዳችን ስለ ጉድጓዳችን መጠየቅ ወደ ኋላ የመቅረት ምልክት መስሎ ታየን።
… በልባችን ውስጥ የድህነት አረም በቀለ። ኢትዮጵያችንንም ብልፅናናችንን የምትሰርቅ ሌባ አድርገን ቆጠርናት። አረሙን የመንቀል አቅም ያጣነው የመንቃትና የመነቃቃት ድፍረት ስልጣን ነው።

አልነቃንም። እንቅልፍ እኛን ገዝቶናል። መተኛት የሙሉ ሰዓት ሥራችን ሆኗል። ጊዜያችንን በእንቅልፍ ጠብመንጃ አነጣጥረን የተኮስንበት መስሎን ገደልነው ስንል ገደለን። በቁም ቀበረን። እኛ በተኛንበት ሰዓት ብልፅግና እያሳቀብን አለፈ። ድንቁርናና ድህነት እኛን አቅፎ ለማደር ራሱን አዘጋጀ…
ዓይናችንን ወደ ውስጣችን አልላክነውም። ራሳችንን አላየንበትም። ከራሳችን ይልቅ የጎረቤታችንን ዓይን ነው የምናውቀው። ዓይኑ ውስጥ የምናየውን ብርሃን ነው ስናደንቅ የምንውለው፣ በጎረቤታችን ዘንድ መፈለግ ብርቃችን ሆኗል። ለመወደድ ብለን ሌላውን ብርሃን እንላለን፣ ራሳችንን ጨለማ ውስጥ ደብቀን “የብርሃናት አባት” ብለን ለጎረቤታችን ሹመት እንሰጣለን።

አማልክት አዲስ ዓይን እንዲሰሩልን ልንማፀናቸው ይገባል፣ አዲስ ዓይን ያልተሰራልን እንደሆነ በድንግዝግዝ ብርሃን እንደሚራመድ አረጋዊ እንቅፋት ያነጉደናል። ያኔ እንወድቃለን፣ አወዳደቃችን ሌሎችን ለሳቅ ይጋብዛል።
አላንኳኳንም፣ ወደ ገዛ ቤታችን ደጅ አልቀረብንም፣ በገዛ ቤታችን ውስጥ መኖር አፍረናል፣ የሀገራችንን ጓዳ ጠልተናል፣ ወደ ጎረቤታችን ሳሎን መቀላወጥ ልማዳችን ሆኗል። ወደ ጎረቤታችን ካልሄድን በቀር ሳሎናችን ስላኖርነው ቅርስ የማናውቅ ሆነናል። ለአገራችን እንግዶች ነን፣ ፀሃይዋና ለመሞቅ ትዕግስቱ የለንም፣ ጠልዋ ባረሰረሰን ቁጥር ለመነጫነጭ የፈጠነው እንደቤታችን ኢትዮጵያን ይረግማል፣ ምናለ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰው ሆኜ ከምፈጠር አሜሪካን አገር ዕድ ሆኜ ከምፈጠር አሜሪካን አገር ዕድ ሆኜ በበቀልኩ ይላል።

እናም አንዳንዴ እንዲህ እላለሁ፤ እንዲህ እመኛለሁ፤ እንዲህ እጠይቃለሁ …
አማልክት ሆይ፣ ትላንት እንደዚያ ያሞካሻችኋት ኢትዮጵያ፣ በቅዱስ አንደበታችሁ በተረጋጋው መንፈሳችሁ የባረካችኋት ኢትዮጵያ ዛሬ በገዛ ልጆቿ ያለመፈለግ እጣ ሲገጥማት ዝም ያላችሁበት ምስጢር ምንድነው?
ኢትዮጵያ በአማልክት ዘንድ ክብርና ሞገስ ያገኘች ሀገር ናት ብለን ስንፅፍ ድሮም የተረት ዓለም ሰዎች መሆናችን ነው ወደኋላ ያስቀረን የሚል ተስፋ ቆራጭ ትውልድ ሲበዛ ዝም የማለታችሁ ምስጢር ምንድነው?
አማልክት ሆይ የዛሬይቷን ኢትዮጵያ የምታዩበት መነፅር እንዴት ያለ ነው? ረስታችሁት ነው ወይስ ረስተናችሁ ነው እንደ ደህና ገበያ መንገድ ላይ የተላለፍነው? የዛሬይቷን ኢትዮጵያ እንዴት ባለ ሚዛን ነው የሰፈራችኋት? በእናንተ ሚዛን ስንሰፈር ከብደን ለመገኘት ከኛ ምን ትጠብቃላችሁ? ድህነትን እንደ ቆሻሻ ጥራጊ አርቀን እንወረውረው ዘንድ ስለምንድነው የመነቃቃት አቅማችንን የማታበረታቱት? … ተቅበዝብዘን ስንጠፋ ዝም የማለታችሁ ምስጢር ምንድነው? በእናንተ አይን ድሮ እንዲያ ታይተናል። ዘንድሮስ እኛ ለናንተ ምንድነን?
እንግዲያውስ ምንድነው የእኛ እጣ ፈንታ? ድህነትን አንበርክከን ለመግዛት፣ ድንቁርናን አስደንግጠን ለማባረር ለማን ምን መሳል ምን መሆን፣ ምን መስዋዕት ይጠበቅብናል?
የመርገምት ልጆች የሆነን ይመስል በውርደት ውስጥ የመኖራችን ምስጢር ምንድነው ብለው ለሚጠይቁን የአገር ተወላጆች ምላሻችን ምን ይሁን?

One Comment

  • woudassegaga@yahoo.com'
    JOJO commented on October 26, 2017 Reply

    SIMPLY BEST …WELL DONE

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...