Tidarfelagi.com

አድዋ እና ‹‹ደማሟ ኢትዮጵያ››

ከውጫሌ ውል መፍረስ በኋላ፣ ኢጣሊያኖች አድዋን እና አክሱምን እንደያዙ እየገፉ መጡ።
ፍልፈሎቹ የሀገራችንን መሬት እየቆፈሩ ገቡ።
‹‹በአምስት አመት ከባድ ረሃብ የተጎዳውን ችግረኛ ህዝቤ አላዘምትም›› ብለው ሲያቅማሙ የነበሩት ምኒልክ የነገሩን ገፍቶ መምጣት ሲመለከቱ ቀጥሎ ያለውን የክተት አዋጅ አወጁ።
‹‹…አገር የሚጠፋ፣ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት፣ እግዚአብሔር የወሰነልንን የባህር በር አልፎ መጥቷልና፣…ያገሬ ሰው..ጉልበት ያለህ በጉልበት እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሀዘን እርዳኝ።››
የንጉሳቸውን የክተት አዋጅ ሰምተው ኢጣሊያን ለማርበድበድ የተነሱት ግን ወታደሮች ብቻ አልነበሩም።
ሴቶች፣ ሽማግሌዎች፣ ህጻናት፣ ቄሶች እንኳን አልቀሩም።
ዳገቱን ሲወጡ፣ ቁልቁለቱን ሲወርዱ፣ ሸለቆውን ሞልተው ሲሄዱ እየተጯጯሁ፣ እየዘፈኑ ነበር። ለሚያያቸው ለውጊያ የሚሄዱ አይመስሉም።
ግን ሁሉም ጀግና አልነበረም። ሁሉም ‹‹ወደፊት›› ባይ አልነበረም። ሁሉም ‹‹ግፋ፣ ብረር፣ ወደፊት ሄደህ ጠላትህን ግጠም›› እያለ በወኔ የሚያስገመግም አልነበረም።
…አንዳንድ ያለ አቻ ጦርነቱን የፈሩ ሰዎች ለምኒልክ የኢጣሊያን ሃያልነት እና ገናናነት በመናገር ምኒልክ ከጦርነት ይልቅ ወደ እርቅ እንዲሄዱ ሊገፋፉ ሞክረው ነበር።
በሀገራቸው ነፃነት ድርድር የማያውቁት ምኒልክ፣
‹‹በሀገሬ በኢትዮጵያ መሬት የሮማን ባንዲራ አለስተክልበትም›› ያሉት እምቢ ባዩ ፣
ልበ ሙሉው ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ግን እንዲህ ብለው መለሱ..
‹‹አንፍራ። እኔ እንደሆንሁ መዝመቴን አልተውምና ስለኢጣሊያ ዘመናዊ መሳሪያና ገናናነት አትንገሩኝ። ሀይል የእግዚአብሔር ነውና እጋጠማለሁ። ብትዘምቱም ፣ብትቀሩም ሬሳዬን ከጦር ሜዳ ፈልጉት። ››
እናም ረሃብ እና ጥም፣ ፍርሃት እና ማመንታት ባላሸነፋቸው ኢትዮጵያውያን ምክንያት፤
ሃያ ሺህ ያህል ወታደሮች ያሉብት የኤሮፓ ጦር በአፍሪካ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተሸነፈ።
አፍሪካ ውስጥ ታላቅ የተወላጆች ሃይል መነሳቱ ታወቀ።
የአፍሪካ ተወላጆች ታሪክ ተለወጠ።
ጥቁሩ አለም በኤሮፓውያን ላይ ሲያምፅና ሲያሸንፍም የመጀመሪያው ሆነ።
‹‹ ደማሟ›› ሀገራችንም በከባድ የደም እዳ ዳግም እንደገና፣ በነፃነት አሸብርቃ ቆመች።

ለዚህም ነው እንዲህ ተብሎ የተገጠመው፤
‹‹ ቆሞ አተኩሮ ትክ ብሎ ላያት፣
ወትሮም ኢትዮጵያ ደማም ናት ደማም ናት››

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...