Tidarfelagi.com

አድባርና…

በዚህ በኩል የእኛ ቤት አለ አይደል…… እንዲህ ከተሰለፉቱ አንዱ። በዚያ በኩል ደሞ ሌሎች ቤቶች ነበሩ… በነገረ-ሥራቸው ከእኛው የማይለዩ። ግራና ቀኛችን ለመቶ ሜትሮች ያህል ቤቶች። ቤቶቹ በሙሉ ትናንንሾች ሲሆኑ የምኖረው ሕዝብ ብዛት ግን የጉድ ነበር (ዛሬም እንደዛው ነው)። በዐይን ብቻ የማውቃቸው ነዋሪዎች ብዙ ነበሩ። ሠላም የምላቸው ጥቂት። ቆሜ የማወራቸው የበለጠ ጥቂት ነበሩ። በጅምላ ሕይወታቸውን መረዳት አይቻልም። ይከብዳል። በአንድ ጊዜ ሁሉንም የማያቸው ለሰፈሯ ቆሌ ሲደግሱ ነው። እዚያ አድባር ላይ የነበረው የተሰብሳቢው መጠን እንዴት እንደተወሰነ ግን አላውቅም። እኔ ስገምት ቆሌዋን ለማክበር ይመጡ የነበሩት በመንገዱ የመቶ ሜትሮች ዕርዝመትና ስፋት ላይ የሚኖሩ ይመስለኛል። ግንቦት ልደታ ቀን ማታ ከአስራ ሁለት ሰዓት ጀምሮ በየዓመቱ መንገዱን መሐል ላይ በሦስት ጉልቻ፣ በገላዎቻቸው፣ በብረት ምጣዳቸውና በቡና ማፍያቸው ይዘጉታል። ሁልጊዜም አንገቴን ሰብሬ ላልፍ ስል ይጠሩኛል……ጠሩኝ።

ከዚያ አካባቢ ውጭ እዚያ መጥቶ ንፍሮ የሚቅም ሰው ያለ አይመስለኝም። የድንበር አፈጣጠሩ ይገርመኛል፣ ያሳፍረኛል። በዚህ ምንገድ ከሚኖሩ ሰዎች ልጁ ያልሞተበት አልነበረም። እንደሰማሁት። የሚጋሩት ሐዘን አለ። ወፍራም ሰው የለባቸውም… ብዙዎቹ ፊቶቻቸው የተመጠጡና የበለዙ ወንዶችና ሴቶች ናቸው። ዝም የሚሉ ዐይኖቻቸውን እሳት ላይ የሚተክሉ የተሸነፉ አባዎራዎች ያሉበት ነበር።

የአድባሩ ንፍሮ የሚበላው በቡድን ነው። አልፎ አልፎ ከቁና ላይ ስሻማ ነጩ ስንዴ ክምር መሐል የሚገቡት፣ ገብተው የሚፍጨረጨሩትና የሚዘግኑት ብዙዎቹ ጣቶች ጥፍራቸው ያልተቆረጠ…ቆሻሻ የሰበሰቡ……አንዳንድ ጊዜም የእሳት ጠባሳ የማይባቸው ነበሩ።

ዙሪያችንን ሕፃናት ይጫወታሉ። መንገዱ ቢመሽም ሙቀቱ አልጠፋም። የእኛ ቤት በር ተከፍቶ ነበር። በዚያ ክፍት ወፍራም የ40 ቁጥር ሻማ አምፖል ብርሃን ጨለማው ምንገድ መሀል ነጭ ቁመተ-ረዥም አራት ማዕዘን ቀዳዳ መስሎ ወድቋል። ከዋናዎቹ ሁለት ጎዳናዎች ከላይም ከታችም ብዙ ድምፅ አይመጣም። የንፋስ መውጫ የግራር አድባር ትዝ አለችኝ። ጀርባዬን ይበርደኛል። ምናልባት ንፋስ በጎዳናው ውስጥ እንደ ወንዝ ይፈስ ይሆናል። ፊት ለፊቴ የተቀመጠ አሰፋ የሚል የጎረቤታችን ሰው በስተግራ ካለው ቤት የሚኖር እፍኝ እፍኝ ንፍሮ እየዘገነ በአፉ ቀዳዳ ያስገባል……….ጉንጩ እንደ ቡጢ ያብጣል……….ዐይኖቹ ብርሃን ገብቶባቸው እንደማያውቁ መንታ ጉድጓዶች የሚመስሉ……….የእሳት ብርሃን አልፎ አልፎ እየወደቀባቸው እዚህ ጉድጓዶች ውስጥ የተጨማደዱ ተጋልጠው ሊወጡ የፈሩ የብርሃን ብልጭታዎች……….ግንባሩ ላይ ግራና ቀኝ ላይና ታች መስመሮችና ረባዳዎች……ፊቱ ብድር ይመስል ነበር። ብድሩን ያልከፈለ ሰው ፊት ይመስል ነበር። ምናልባት እንደ ሁላችን ፊት። አድባር ለመድረስ ካልተመቻት ሴትዮ ደሳሳ ቤት ሩካቤውን አጠናቆ የወጣ ወንዳታ ፊቱን በታላቅ ጥረት አንገቱ ውስጥ በዕፍረት የደበቀ………እሱንም እንደ ማጋለጥ የሚከተል በጨለማ ውስጥ እንደ ቁራ የሚበር ልቅላቂ ውሃ………ወርቅ ወንድነቱ አልማዝ ሴትነቷ ጎዳና መሃል ሊሰበር………በታችኛው ምንገድ ቀዝቃዛ ፖለቲከኞች በቀዝቃዛ ቶዮታ ክሩይዘር ያልፋሉ። ትኩስ የጠገበ ሻኛቸው እንደ ፍሬቻ ያበራል። የጎፈሬአቸው ጫፍ እንደ ክብሪት የተለኮሰ ነው። ዥው ብለው ሲያልፉ ባሕላቸው ሳይሆን አይቀርምና የብርድ አዙዋሪት ይሰራሉ።

ከምሽቱ ሦስት ሰዓት አካባቢ ነበር። ከማታ ትምህርት ቤት የምወጣው በዚህ ሰዓት ነው። ደብተሬን ላስቀምጥ ብዬ ምክንያት በመፍጠር ቤቴ ገብቼ ለመተኛት ወይም ራቴን ልብላ ብዬ ጫልቱ ዘንድ በመሔድ ከዚያ የአድባር ስብሰባ ለመሸሽ ፈለግሁ። የአሰፋ ፊት ግን እንደ ታላቅ ቅዱስ መፀሐፍ ተከፍቶ………“ውጋት ነው። የሕይወት ታሪኬ ውጋት ነው። የሕይወት ታሪኬ የጀርባ ውጋት ነው። እዚያ እሳት ዙሪያ እንደ ዶሮ ተሰብስቤ ንፍሮ የምበላው ውጋቴን ለማሸት ነው። አታየውም እንጂ የገላዬ ቆዳ በየቦታው ተቀዳዷል። በቆሌ በዓሌ፣ በትንሽ ቀልድ፣ በፌዝ ክር ነው የምሰፋው። የደረት አጥንቶቼ በስጋ የተያያዙ የበረዶ ዘንጎች ናቸው። ልቤ በዕዳ ሙሉ ነው። ንፍሮ ያልያዝኩበት እጄ በደመወዝ የሞዴል ፎርሞች፣ በሠፈር የአራጣ አበዳሪ የሥምምነት ወረቀቶች ታስሮአል………ሲመሽ የቀረ ጉልበቴን ሚስቴ ላይ አፈሳለሁ። ልዩነታችን ምንድን ነው? ተጉዘን ተጉዘን የምናርፍበትን እኔም አንተም አናውቅም። እነሆ የልጅነት ተስፋዬን ለአገሬ ሰጠሁ፣ ጠጋ በል ወንድሜ ጠጋ በል………ለቃቅመን እሳት የለኮስናቸው እንጨቶች ይሙቁህ። አትፍራ። እኔና አንተ የምንፈራው የለም። ጫማ ለብሰን፣ ጨርቅ ደርበን የምንዞር ሬሳዎች ነን” የሚለኝ መሰለኝ። መሔድ አፈርኩ። ለመሳቅ እየሞከርኩ ምንገድ ዳር ድንጋይ ላይ ቁጭ ብዬ ንፍሮ መሻማት ጀመርኩ። ጥቂት ሕፃናት ሊዘፍኑ ይሞክራሉ። ብሰማቸውም ግድግዳ ውስጤ እንዳለ ይታወቀኛል—ከትንንሽ ድንጋዮች የተሰራ እድሞ……የእነዚህ ሕጻናት ድምፅ እንደ ውሃ ሊሸረሽኝ ሲሞክር እሰማዋለሁ……የድምፃቸው ክንድ እስከ እንጦጦ እንደ ላስቲክ እየተሳበ ሲወጣ…… ወፍራም የዋሕነት ነው። ወፍራም እንደ እንጎቻ የሚጎመድ የዋሕነት ነው። የሰፈሬ አርማ ተስፋ መቁረጥ ነው። አንድ ልጅ ወደ ተቀመጥኩበት መጥቶ ግራ እግሬን አቀፈኝ። ምን እንደሚፈልግ አላውቅም። ደብተሮቼን የያዝኩበት እጄን አልቦኛል። ነጠላና ኩታ የደረቡ ልጃገረዶች መጥፋት የጀመረው እሳት ዙሪያ ለመዝፈን ጭብጨባ ጀምረው እየተፋፈሩ ከመሀል ያቆማሉ። ‘አንቺ በይ’ ‘አንቺ በይ’ ይባባሉና ከመሐል በወሬ የተሳሰረ ፀጥታ ይመጣል። በስተ ግራዬ አንዲት ወይዘሮ ዝናሽ የሚባሉ ሴት ፊታቸውን አንድ እጃቸው ላይ አስደግፈው የእሳቱን ፍም አግድም ያዩታል። ውስጣቸው እንደበረደ ያስታውቃል። አንጀታቸው ውስጥ ቀዝቃዛ እርጥብ የጨርቅ ኳስ እንደተቀመጠ ሁሉ ነበር……ስለዚያም ጨርቅ እንደሚያስቡ። ጥቁር በጥቁር ለብሰዋል። አጠገባቸው መጥቼ ከተቀመጥኩ ጀምሮ አልተናገሩም። ሰዎች ከሚቀባበሉት ንፍሮ አልፎ አልፎ ይቆነጥራሉ። ቡናቸው ላይ ኮስታራ ናቸው። ቅንድቦቻቸው የንብ ደጋን ናቸው። የከሳ ገፃቸው ላይ ሳያቋርጡ የሚያናውዙ አስገራሚ ትላልቅ ዐይኖች አሉ። አፍንጫቸው ላይ በደብዛዛው ጨለማ ውስጥ አፍጦ የሚታይ በእርጋታ የሚያንቀላፋ የማድያት ጥቁር ልጋግ አለ። አልፎ አልፎ እንደ ሲጃራ አጢያሽ ይስላሉ። የሚጫወቱትን ወጣቶች በገለልተኛ ዐይኖች ያጤናሉ። ከዚያ እሳቱን ያያሉ። ከዚያ ጥሬ እንዲዘግኑ የተዘረጋላቸውን ቁና በትዝብት በጎሪጥ አይተው በቸልታ ይዘግናሉ። ሲያላምጡ የመንጋጋቸው አጥንት ሪጋ ፊታቸው ላይ ቦግ ድርግም ይላል። ለቅፅበት እዚያ የተሰበሰበነው ሁሉ አደጋ ላይ እንዳለን ገባኝ። ዙሪያችንን የከበበው ብርድ ጠንክሯል። ጥቂት ሰዎች ወደ የቤታቸው እየገቡ ነበር። ሽሽት?

ቀዝቃዛው ንፋስ በከተማዋ እንደ እንድስቅጤ……አንድ ግራጫ እንድስቅጤ ከተማችን ሳንባ ላይ እንደተለጠፈ እሰማለሁ። በእንጦጦ በሽሮ ሜዳ ሲወርድ……ስድስት ኪሎ ቤንዚን ሞልቶ የየካቲት 12 አደባባይን ሐውልት ሰብሮ……አራት ኪሎ ቤንዚን ሞልቶ በፒያሳ……መርካቶ…… ከመርካቶ በተክለ ሐይማኖት…… ማይጨው አደባባይ…… ከማይጨው አደባባይ…… አብዮት አደባባይ…… ከዚያ ቦሌ…… ከቦሌ አስመራ ምንገድ…… በራሱ ላይ ተረማምዶ…… በወሎ ሠፈር…… ፖፖላሬና ቄራ…… በቄራ…… በኮቶኒ…… ልደታ…… ከልደታ እኛ ሰፈር መግቢያ አስፋልቱ ዳር አፉን ከፍቶ…… ጅራቱ ግን ከእንጦጦ ሳይነሳ።

አድባር ለማመስገን የሰበሰበው ሰው እንደ ጭኮ ኮረብታ እየተናደ ነው። ጥቂት ሰዎች ብቻ ቀርተናል። እኔ በሕልሜ የምኖር ይመስለኛል። ከፊት ለፊቴ አንዲት ጠይም ልጅ፡
“ከበኩረ ጋር የምትኖረው ልጅ ነህ አይደል አለች?” አለችኝ

“አዎ” አልኳት
“በኩረ አለ እቤት?”
“እኔ እንጃ…”
“አንቺ ምነው በኩረ በኩረ አበዛሽ…” አለቻት አንድዋ ሌላ ጠይም። መንታ ይመስላሉ።
“ምነው አንቺ?” አለች በመሽኮርመም
ብዙ ለመናገር አልፈለግኩም።
“ለምን ንፍሮ አትበላም? ስትበላ አላየሁህም” አለችኝ።
“ብዙ በላሁ”
“አድባር ደስ አይልም?” አለችኝ
“አዎ” ሌላ የምመልሰው አልነበረኝም።
“ደስ አላለህም እ?” አለች ሌላዋ።
“ጫማው ደስ አይልም?” አለች አንድዋ

ሁለቱም በሕብረት እግሮቼን ዝቅ ብለው አዩ። እንደ ጅራት አልጠቀልላቸው። ብዙ እንደ ሬዲዮ አንቴና የማይጠቀለሉ ነገሮች አሉ። ሁለቱ፡ ብዙ የሚያወራ ምላስና አዲስ ጫማ ያጠለቁ እግሮች።
ቀዝቀዛ ንፋስ ጀርባዬ ላይ ይሰማኛል። ይህቺም ቆንጆ ነበረች። በትዝብቴ ፀጥታ ግን የላትም ብዬ መዘንኩ። ከአፍዋ የሚወጣው ድምፅ የተፈጥሮ ውበቷን እያጠፋው ነው። የሚያምሩ ጥርሶች አላት…… እደው እንዲህ በጨለማው ውስጥ እንደ ማሾ የሚያበሩ። ዐይኖቿ ይጫወታሉ። ቀዝቃዛ ንፋስ ከጀርባዬ የመታኝ ይመስለኛል። አውሬ እንደ ፈራሁ ሁሉ ወደ ኋላ አያለሁ።
“መሸ ልሂድ…… ከማታ ት/ቤት እንደመጣሁ ደብተሬንም አላስቀመጥሁ” አልኩ።
“አድባራችንን ወደሃታል ማለት ነው?”
“አዎ…… ደህና እደሩ”
አንድዋ ልጅ አጠገቤ ያለችው የጠይሟ ጓደኛ እጅዋን ዘረጋች። ተንደፋድፌ እጄን ሰጠሁዋት። ደረቅ ናት። ቆንጆ ነበረች ግን እሳት ያጥራታል። እሳት አልነበራትም። አፍ ነበራት…… ወላፈን የላትም…… ታስታውቃለች። ብልጥ ናት። አንገቷን እንደ መስበቅ አደረገች። ደረቷ እንደ ሳንቃ ሰፋ ይልና ጡቶቿ በእራፊ ጨርቅ የተጠቀለለ በትንሹ ከዐይን የተደበቀ (ቡዳ ተፈርቶ?) የሕፃን ልጅ ቂጥ ይመስላሉ። የቀሚሷ ደርዝ ገደድ ያለ ነበር…… ከፊት ለፊት ዘቅዘቅ ከኋላዋ ወደ ላየ የተሳበ። ተራ ሳቅ ሳቅሁ፤ ትርጉም የሌለው። ወደ ኋላ አየሁ……
እኛ ገብሶች ነን። እኛ የገብስ ቆሎዎች ነን፡፤ እኛ ከገብስ ቆሎ የተሰራን ዱቄቶችነ ነን፤ እኛ ቅቤ የተነከርን (ከራሳችን ጭንቀት የታለበ) የገብስ ዱቄቶች ነን። እኛ የጭኮ ኮረብታዎች ነን…… ከደኖቻችን ከኮረብቶቻችን እንድስቅጤ የበቀለ። ከፍ ብሎ ከሰማይ ላይ/ከሰማይ መሀል ታላቅ ጎሚ አፉ ተከፍቶ አየሁ…… እዚህ ቆነጃትት እንደሚሰበሩ አውቃለሁ። ታች፣ በጣም ታች…ታች ወድቀው ተሸራርፈው ያልቃሉ……እኔም እየተበላ በሚጠፋው ግማሽ ጎኔ እንደ እንሽላሊት ሞቼ የምለብሰውን አፈር እስባለሁ……

ብርዱ አንጀት ውስጥ ከበሮ ሰማሁ። ድቤ አዳምጣለሁ። እሳት ዘሪያ ተስፋቸው የተቃጠለ እጆች የቅማንት ዜማ በጭብጨባቸው ይወልዳሉ። ከዛ እስከ ነገ…… ከነገም እስከ ነገ የቸላማ ችቦ ነው ከግራጫ ነበልባል የበለፀገ። አድባሯ – ያቺ አሮጊት ልጃገረድ በቀሯት ማውለቢያዋ ትስቅ ይሆናል አልኩ። መፍነክነኳ በቅሬታ የተተበተበ……

ቤት ስገባ ማንም አልነበረም። ጓደኞቼ በሩን ከፍተው ምን አልባት ጎረቤት ጠላ ሊጠጡ ሔደው ይሆናል አልኩ።
ታላቅ ዲን አድባሯና እንድስቅጤው ሲጣሉ ነፍሴ መስክ ላይ ሰማሁ። መታዘቢያ እንጂ መፎከሪያ ድምፅ አልነበረኝም።
የዚች አድባር ጡቶቿ እንዴት ደርቀው ነበር?
ባቶቿ እንዴት ከስተው ነበር?
ሮጬ ወጥቼ ከሴቶቹ ጋር ልቀላቀል ፈለግኩ። ወገባቸውን ይዤ አብሬአቸው ልዘፍን ፈለግኩ።
ግን ከልቤ ማዕከል ዘፈን አልፈልቅ አለኝ።

ከዕለታት አንድ ቀን…….
ምናልባት ከዕለታት አንድ ቀን……
ልጃገረዶቹም ፈጥነዋል…….
በየቤታቸው ገብተዋል…….
መስኮት ከፍቼ ለምን እንደሆነ አላውቅም……. ወደ ውጭ ሳፈጥ ብዙ ቆየሁ። ጫማዬ? ዝነኛው ጫማዬ አስከፍቶኝ ቤቴ እንደ ገባሁ ነበር ያወለቅኩት።

ግራጫ ቃጭሎች (355 – 360)

አዳም ረታ አንጋፋ የሀገራችን ደራሲ ነው፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...