ካናዳ የሚገኘው የመስሪያ ቤታችን ቅርንጫፍ ባልደረባ ለስራ ጉዳይ የኢሜል መልእክት ልካልኝ ምን ብላ ጀመረች?
‹‹እንዴት ይዞሻል? አዲስ አበባ ያላችሁ ሰራተኞች ከቻላቸሁ ከቤት እንድትሰሩ እንደተመከራችሁ ሰማሁ። እኛ ያው በግድ፣ በመንግስት ትእዛዝ ቤት ታሽገን ተቀምጠን ልናብድ ነው። ወላ ሬስቶራንት ሄዶ መብላት የለ፣ ሰታር ባክስ ኮፊ የለ፣ ከሰው መገናኘት የለ፣ ቤት ተዘፍዝፎ የኔት ፍሊክስ ፊልም ሲያዩ መዋል አንዴት ይታክታል መሰለሽ! የባርነት ስሜት እየተሰማኝ ነው። ትንሽ የምንፅናናው ነገሩ በዚህ ከቀጠለና ከስራ ከተባረርን መንግስት የስራ አጥነት ኢንሹራንስ ክፍያ እና የሶስት ወር ደሞዛችንን እንደሚሰጠን ሳስብ ነው። ኢትዮጵያ ዛሬ 25 ሰው እንደደረሰ ሰማሁ…ቤት መቀመጡ ጨንቆሻል? ከጨነቀሽ እዚህ ስንቀባበለው የነበረ አንድ አሪፍ በስነ ልቦና የሚያግዝ ቪዲዮ አለ…እልክልሻለሁ….››
አይ ቤት ተዘፍዝፎ ፊልም ሲያዩ ስለተዋለ የባርነት ስሜት መሰማት!
አይ መንግስት ሰራሁም አልሰራሁም ደሞዝ ይከፍለኛል፣ ሆዴን ይሞላልኛል፣ የቤት ኪራይ ይሸፍንልኛል ግን ቤት መዋሉ ጨንቆኛል ማለት!
አይ የሰው ኑሮ መለያየት!
ሳልንዛዛ፣ ነገሬን ሁሉ አሳጥሬ ልነግራት ፈለግሁ፤ አንዲህ ልላት ፈለግሁ….
‹‹አይ የኔ ቀበጥ! አንቺ ደልቶሻል እቴ! እዚህ ዘጠና ዘጠኝ በመቶው ሰው …
ጠዋት ካልሰራ ማታ አይበላም …
ለወትሮም ከወር ወር የማታደርሰው ደሞዙ ብትቀርበት፣ ዛሬ ቢሰናበት ነገ ይበላው ምግብ፣ ይጠለልበት ጎጆ አይኖረውም…
ነግጄ አተርፍ ብላ በቀን አምስት እና አስር ብር የምትለቅም የመንገድ ዳር ባተሌ እናት ልጆቿን የምታልስ የምታቀምሰው አይኖራትም….
የእኛ ጭንቀት ይሄ ነው…እንቀልፍ የሚነሳን ሃሳብ ይሄ ነው….
የእኛ ጭንቀት ቤት ታሽገን መዋላችን ሳይሆን፣ ባለመውጣታችን የምናጣው የእለት ጉርስ፣ የአመት ልብስ ነው….››