Tidarfelagi.com

አንጀት የመብላት ጥበብ

የሆነ ጊዜ ላይ የሚሰራበት መስርያ ቤት፤ ለዓለምአቀፍ ስብሰባ ወደ ውጭ ሀገር ላከው:፤ በተላከበት የፈረንጅ ከተማ ሆቴል ውስጥ ፤ አንድ ሳምንት በስብሰባ ዛገ፤ እናም፤ ያንቀላፋ ልቡን የሚቀሰቅስለት አንድ ነገር ፈለገ፤

አንድ ቀን ሆቴሉ አጠገብ የሚገኝ ቡና መጠጫ ቤት ውስጥ ገባ። ካፌው ውስጥ ላንድ ሰው የሚሆኑ ብዙ ጠረጴዛዎችና ወንበሮች ቢኖሩም ፤ እሱ ግን ካንድ በላይ ሰው የሚያስተናግድ ሶፋ መርጦ ተቀመጠ ፤ ለዘዴ ነው፤ ብዙም ሳይቆይ አንዲት፤ ብስል ኮክ ፍሬ የመሰለ ፊት ያላት ፤ ፈረንጅ፤ ጠረጴዛውን ተጋራችው፤ አይንና ጥርስማ የዝጊሃር ስራ ነው/ ግርም ያደርገው ያፍንጫዋ ጌጥ ነው! በሁለቱ ያፍንጫዋ ቀዳዳዎች የሰካችው ቀለበት የወርቅ ነስር ይመስላል።

ይዞት የመጣውን መፅሀፍ ጠረጴዛው ላይ ዘረጋው ፤ ሲያስመስል ነው፤ ተስተናጋጆች ሁሉ ሙባይላቸው ላይ በተደፉበት ካፌ ውስጥ፤ መፅሃፍ የሚያነብ ሰው ትኩረት እንደሚሰርቅ ያውቃል፤ አልተሳሳተም: ሴቲቱ ስታየው አያት’

“ሃይ” አላት ተሽቀዳድሞ፤
“ሄሎ”
በግብዳው ፈገግ አለ፤ ቀጥሎ ምን መናገር እንዳለበት ሲያስብ፤
“ስምህ ማነው?” አለችው፤
” ምኡዝ”
“ሚውዝ?”
“ምኡዝ”
“ሚውዝ?”
ምን አጨቃጨቀኝ ብሎ ባዎንታ ራሱን ደፋ ቀና አደረገ፤

“ያንቺስ?”

“ኦሊቭያ”

“ምንድነው የምታነበው?” አለቺው፤

የማያነበውን መፅሀፍ ሽፋን አሳያት።

“ከምትሰራው ጋር የተያያዘ ነው?”

ራሱን ባሉታ ነቀነቀ፤I’m stranger here..I’m alone. So reading is the antidote for my loneliness አላት። (ላገሩ እንግዳ ነኝ፤ ብቸኛም ነኝ፤ ንባብ የብቸኝነቴ ማርከሻ ነው”ለማለት ፈልጎ ነው፤

አንገቱዋን ዘመም አድርጋ በርህራሄ ተመለከተችው ፤ተከዘች። አንጀቱዋን እንደበላው ርግጠኛ ሆነ፤ ሂደቱን ያውቀዋል፤ መጀመርያ አንጀቱዋን ይበላታል፤ከዚያ ወርዶ ይበላታል፤

….

ድሮ ወንዶች ሴቶችን የሚማርኩበት ዋና መሳርያ ጉልቤነት ነበር፤ ምክንያቱ ግልፅ ነው፤ ጉልበት ያለው ወንድ ቤቱንና ልጆቹን ከዱር አራዊትና ከቀማኛ ይጠብቃል። አድኖ ካልሆነም ዘርፎ አምጥቶ ጫጩቶቹን ይቀልባል ። ሚስቱን ከደፋሪ ይታደጋል፤ በጣም አላማላዩ ወንድ ጉልበተኛ ወይም ጉልበተኛ ጭፍራ ያለው ነው፤ ሴቶች ቀይ ሆኖ ተወልዶ፤ በጠባሳና በሰንበር ብዛት የጠየመ ወንድ ሲያዩ፤ ልባቸው ወከክ ይል ነበር፤

ሴቶች ለደካማ እና ለፈሪ ልባቸው እንደማይደነግጥ የሚያውቁ አያቶቻችን፤ ብርቱና ጀግና ለመሆን ይጥራሉ፤ አለበለዝያም ጀግና እና ብርቱ መስለው ለመታየት ይፍጨረጨራሉ ። ያን ጊዜ፤ ለወንድ ልጅ ትልቁ ኪነጥበቡ ፉከራ ነበር፤ የፉከራ መልክት ባጭሩ -ጀግንነቴን ሌሎች ባይነግሩሽም እኔ ልንገርሽ- የሚል ነው ፤ ያፄ ዮሃንስ አሽከር የነበሩት የዋድላው ልጅ ከልካይ ዳንዴ፤ ጀብዳቸውንና ሚስታቸውን ባንድ ግጥም ሲያስተዋውቁ እንዲህ ይሉ ነበር፤

“ከልካይ የዳንዴ፤ የደም እራቱ
የወርቅነሽ ባል ፤የአይናማይቱ”

ዘመናት አለፉ። ጉልበተኝነትም እያለፈበት መጣ፤፤ ቤትህን ዘበኛ ይጠብቅልሀል። ልጅህም መዋእለ ህፃናት ይጠብቅልሃል፤ ንብረትህን ባንክ ይጠብቅልሀል። ፖሊስ ይጠብቅሃል። ጉልበት ምናባህ ያረግልሃል? የግለሰቡ ጉልበት ነፈሰበት፤ መስህቡን አጣ! ህግና ገንዘብ ጉልቤነትን ከጥቅም ውጭ አደረጉት፤ እና ወንዶች ዘመኑን የሚመጥን ፤፤ ባይነቱ ለየት ያለ፤ ሴት ማማለያ ፤መፈብረክ እንዳለባቸው ተገነዘቡ።

የሴቶች ደካማ ጎን ማጥናት ጀመሩ ፤ ሴቶች በእናትነት ገፃቸው ለህፃን ይራራሉ፤ስለዚህ ወንዶች እንደ ህፃን አቅመቢስ ፤አሳዛኝ ፤ምስኪን ሆነው ቀረቡ፤ባጭሩ እንጀት መብላትን ፈሊጥ አደረጉት፤ የአስራሁለተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ፤አንድ ባልንጀራየ ያፈቀራትን ልጅ አንጀት ለመብላት ከመፈለጉ የተነሳ ፤ ግራ ክንዱን በቤሳ ምላጭ በመብጣት፤ በደሙ እያጣቀሰ ደብዳቤ መፃፉ ትዝ ይለኛል፤ ( አያቱ ፍቅረኛቸውን ለማማለል፤ በጠላታቸው ደም የተነከረ ሸማ ልከውላት ይሆናል)

አንጀት መብላት፤ በያና በይህ ትውልድ ጅንጀና ውስጥ ያለውን ቦታ ለመረዳት፤ ባለፉት አርባ አመታት ዝነኛ የነበሩ ዘፈኖችን ግጥም ማየት ይበቃል፤

“ምነው ባደረገኝ የደጅሽን አፈር
አንቺ ስተርግጭኝ እኔ እንድንፈራፈር”
(ሙሉቀን መለሰ)

ምፅ! ምፅ!

“ቆዳየ ተገፎ ይሁንልሽ ጫማ
አጥንቴም ይደገም ላንቺ ከተስማማ”

(አለማየሁ እሸቴ)

ምፅ ! ምፅ !

‘እኔ ልሁን እንጂ የማልጠቅም ርካሽ
ምንም ጊዜ ቢሆን አንችን ክፉ አይንካሽ”

(ጥላሁን ገሰሰ)

ምፅ ! ምፅ! ምፅ!

“ድህነት ሆነና ፤ደልቶኝ ባላኮራሽ
እንባ አያጣም አይኔ ላዘን ለመከራሽ”

( ሙሉጌታ ተስፋየ -አበበ ተካ)

“ ባይተዋር አረግሽኝ፤ ዘመድ አሳጣአአአሽኝ
አላሳዝንሽም ወይ?!”

(Ass ናቀ ፤ገብረየስ)

(ገና ካልተፃፈው፤ “መግባትና መውጣት፤ ቁጥር ሁለት” ከተሰኘው መፅሀፌ የተቀነጨበ)

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...