አቶ ሀዲስ አለማየሁ በልቦለድ ፀሀፊነታቸው የተጋረደ የፖለቲካ ሰብእና ነበራቸው። በተለያየ ጊዜ ስለ ኢትዮጵያ ሁኔታ የሰነዘሩዋቸው አስተያየቶች እንደ ደረቅ ትንቢት የሚቆጠሩ ነበሩ። ለዛሬ: መጋቢት 19: 1985 አመተ ምህረት ባዲሳባ ዩንቨርሲቲ ካቀረቡት ንግግር የሚከተለውን ለመቀንጨብ ወደድሁ። በጥሞና አንብበን በሰከነ መንፈስ እንወያይበት።
የንግግሩ ቅንጫቢ ይሄው-
“…አሁን በይፋ የሚደረጉትን አንዳንድ ነገሮች ስመለከትና እንዲሁም በይፋ በየመድረኩ የሚደረጉትን አንዳንድ ነገሮችን ስሰማ በኔ አስተያየት የኢትዮጵያ ህልውና አስጊ ሁኔታ ላይ ቆሞ የሚገኝ ይመስለኛል።
ይህን የምልበት ምክንያት ዛሬ ራሳቸውን በልዩ ልዩ የነፃነት ግንባር የሰየሙ ቡድኖች “የህዝቦች የራስን እድል – እስከነፃነት በራሳቸው የመወሰን መብት ” ለተባለው ድንጋጌ : የተሳሳተ ትርጉዋሜ ሰጥተው : የራሳቸው ነፃ መንግስት እንዲኖራቸው ..ያሰቡት ሀሳብ ፍፃሜ የሚያገኝ ከሆነ ይህ ከኢትዮጵያ ህልውና ጋር የማይጣጣም ሆኖ ስለሚታየኝ ነው።
“የህዝቦች የራሳቸውን እድል እስከ ነፃነት..”የሚለው ድንጋጌ በነፃነት ግንባሮች የተሰጠው ትርጉዋሜ የተሳሳተ ከመሆኑም ሌላ : እንደ ኢትዮጵያ ብዙ ነገዶችና በነገዶችም ውስጥም ብዙ ጎሳዎችና ንኡስ ጎሳዎች በሚኖሩባት አገር: በቃል የሚነገረውን ያክል በግብር መተርጎሙ ቀላል ሳይሆን ሊወጡት የማይቻል ገደል ነው።
በተጎራባች አገሮች መካከል ያለው የወሰን :የወንዝ ክፍፍል :የጎሳዎችና የንኡስ ጎሳዎች አስተዳደር .የሚያስነሱት ዘልአለማዊ ሁከትና ጦርነት : ለሀገርና ለልማት ሊውል የሚገባውን ሀብትና ጉልበት እየበላ ሁልጊዜ አደህይቶና ሰላምን አሳጥቶ የሚኖር በመሆኑ : የሚሸሹት እንጂ እንኩዋንስ ሊይዙት የሚቀርቡት አይደለም።
…
ይህ ንኡስ አንቀፅ ተፈፃሚነቱ ለሽግግር መንግስቱ እድሜ ብቻ እስከሆነ ድረስ የሚፈጥረው ችግር ቢኖር ጎልቶ ላይታይ ይችል ይሆናል። አሁን ወደሚረቀቀው ቀዋሚ ህገመንግስት የሚተላለፍ ከሆነ ግን :በየነገዳቸው ህዝብ ላይ ስልጣን መያዝ ለሚፈልጉ ሁሉ በር ከፋች ሁኖ: መጨረሻው ለማይታይ ሁከትና ጦርነት መንስዔ ሊሆን ስለሚችል :ህገመንግስቱን ለማርቀቅ ሀላፊነት የተጣለባቸው ክፍሎች አጥብቀው ሊያስቡበት የሚገባ ይመስለኛል። ተመሳሳይ ህገመንግስት በነበሩዋቸው አገሮች: በሶቭየት ህብረትና በነይጎዝላቢያ ዛሬ የደረሰውም ትምህርት ሊሆነን ይገባል”
(ምንጭ: ኢትዮጵያዊነት: መፅሄት:1985)