Tidarfelagi.com

‹‹አብሮ አይሄድም››

 

ለስብሰባ ከመጣች ኖርዌያዊት የስራ ባልደረባዬ ጋር የባጥ የቆጡን እየቀባጠርን ነበር። ኢትዮጵያንም አፍሪካንም ስታይ የመጀመሪያዋ ነው።

ምሳ ደረሰና ቡፌው ጋር ስንሄድ፣ ገበታው የጸም እና የፍስክ በሚል መከፈሉን ስታይ ተከታታይ ጥያቄዎች አዘነበችብኝ።

‹‹ብዙ ሰው ይጾማል?››
‹‹ምን ያህሉ ሰው ኦርቶዶክስ ነው?››
‹‹ምን ያህል ሙስሊሞች አሉ?››
‹‹አብዛኛው ሰው በእግዜር ያምናል?››

ምሳ እየበላን ጥያቄዎቿን ለመመለስም፣ ገፅታ ለመገንባትም፤ ስለ ሁዳዴ ፆም፣ ስለ ኢትዮያዊያን ሃይማኖትን አጥባቂነት እና ፈሪሃ እግዚአብሄር ጠብረር እያልኩ ብዙ አወራሁ።

ከዚያ ግን ባልጠበቅኩት ጥያቄ አስደነገጠችኝ። አሸማቀቀችኝ። ኩምሽሽ አደረገችኝ።

‹‹ሕይወት፣…አንድ ጥያቄ አለኝ…ቅር ካላለሽ?›› አለችኝ።
‹‹ጠይቂኝ ምንድነው?›› ቶሎ መለስኩ።
‹‹ እ….ጠዋት በነበረው ውይይት በአሁኑ ሰአት እርስ በርስ ግጭት የተነሳ ከሶስት ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን በላይ እንደተፈናቀሉ ሰምቼ ነበር። …››

‹‹አዎ ልክ ነው›› አልኩ እንደተበሳ ጎማ እንስ እያልኩ።

‹‹እ…ባለፉት ቀናት የመስክ ጉብኝቴም ብዙ የሚዘገንኑ ነገሮቸ ሲፈፀሙ ያዩ ሰዎችን አነጋግሬ ነበር። እናት አባታቸውን በጎረቤቶቻቸው የተገደሉባቸው ህጻናት፣አካላቸው የጎደለ ህጻናት፣ የተደፈሩ ሴቶችን አግኝቼ ነበር። ››

‹‹እ…አዎ ልክ ነው›› የበለጠ ኩምሽሽ እያልኩኝ መለስኩ።
አንገቴ መሰበር ጀምሯል።
ፊቴ ላይ ላብ መንቸፍቸፍ ጀምሯል።
እግሬ መሬት መደብደብ ጀምሯል።

‹‹…በእኔ ሃገር አብዛኛው ሰው ሃይማኖተኛ አይደለም….እንዲያውም በእግዜር የማያምን ይበዛል….ግን እንዲህ ያለ ችግር የለም….ማለቴ እርስ በርስ መገዳደል….ኢትዮጵያዊያን አንቺ እንዳልሽው ሃይማኖተኛ ከሆኑ እና እግዜርን ከፈሩ እንዴት እርስ በርስ ይገዳደላሉ? እ…እንዴት እዚህች ሃገር ላይ እንዲህ ያለ ነገር እንዴት ይፈፀማል?…ይቅርታ፣ ግር ስላለኝ ነው…አለ አይደል..፣ አብሮ አይሄድም››

ሆዴን በጩቤ የወጋችኝ ያህል ነው ያመመኝ። በቢላ የከተፈችኝ ያህል፣ በዱላ የደበደበችኝ ያህል።

ኢትዮጵያውያን፣ ምን ልበላት? ምን አይነት ፈጣን እና ብልህ መልስ ልስጣት? ምንስ ሰበብ ደርድሬ ላሳምናት?

ምክንያቱም ልክ ናት፤ እርስ በርስ መገዳደል እና ፈሪሃ እግዚአብሄር አብሮ አይሄድም።
እርስ በርስ መጨራረስ እና ሃይማኖተኝነት አብሮ አይሄድም።

ኢትዮጵያውያን፣ ምን ልበላት? ምን አይነት ፈጣን እና ብልህ መልስ ልስጣት? ምንስ ሰበብ ደርድሬ ፣እንዴት ብዬ ላሳምናት?

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...