Tidarfelagi.com

አባቴ አክተር ነው!!

“ሜዬ በናትሽ እኔ ልብላው? እሷ ታባክነዋለች።”

እንዲህ የምትለኝ እህል እንዳይመስላችሁ። ወንድ ጓደኛዬን ነው። አቢቲ የወንድ ቀበኛ ናት። ‘እሷ’ ያለቻት ሀይሚን ነው። ሀይሚ አብራን የምትኖር የእኔም የእሷም የጋራ ጓደኛችን ናት። አቢቲ ደግሞ የአክስቴ ልጅ ናት። አቢቲ እንደምትለው ሀይሚ ወንድ ታባክናለች። እናም የሚጠቀስ የፍቅር ግንኙነት የላትም። (አቢቲ እንደምትለው ደግሞ ንብረቷን ከመሽኛነት ለተሻለ ግልጋሎት አትጠቀምበትም።) ዛሬ ቢኒን ከሌሎች ጓደኞቻችን ጋር ምሳ እቤት የጋበዝኩት ከሀይሚ ጋር እንዲጣበሱ ነበር።

አቢቲ ገና ስታየው “ሜዬ ይሄን የመሰለ ልጅ ይባክን?” ምሳ ለጓደኞቼ ለማቅረብ በተንጎዳጎድኩበት ስር ስሬ እየተከተለች። “እ ሜዬ? እሷን ታውቂያታለሽ! ኸረ ሜዬ እኔ ልብላው?”

“አቢቲ እስኪ ተይኝ። ቢኒ ቁምነገረኛ ነው። ለአንቺ የሚሆን ወንድ አይደለም።” እላታለሁ የማያዛልቀኝን መኮሳተር ተኮሳትሬ።

“ይሄን የመሰለ አቋም ይዞ ማን ያቋቁመዋል?(ቁም ነገሩን ማለቷ ነው) ኸረ ሜዬ? ” ከሷ ልብላው ማለት የጎረምሶች ጓደኞቼ ‘እሷ ትብላው። አይባክን¡’ ማለት። ሀይሚዋም ‘እንደዚህ እየቋመጠችበት ግፍ ነው። ትብላው በቃ ሜዬ!’ ብላ የታሰበላትን ሲሳይ አሳልፋ ማስረከብ። የሚዶለትለት ያልገባው ቢኒ ከመቼው አብሯት መለጣጠፍ። ከቀናት በኋላ

“እ?”

“አይይ ሜዬ አልበላሁትም። ሀይሚ ትብላው በቃ!!”

“ሀይሌ ይሙት?” (ሀይሌ የአቢቲ አባት ነው። እኔም ለምዶብኝ የምምለው በሷ አባት ነው።)

“ሀይሌ ይሙት!! አልበላሁትም!!”

ለሀይሚ ተነገራት። ሀይሚ ከአቢቲ በብዙ የተለየች ስለሆነች ‘የተነካካ አልነካም።’ አለች። አቢቲ ይሄን ስታረጋግጥ

“ዋሽቼሻለሁ። ውሃ ውሃ ይላል እንጂ በልቼዋለሁ።” አለችኝ ድምፇን ለእኔ ብቻ እንዲሰማ አድርጋ። (ያልተመቻትን ወንድ ውሃ ውሃ ይላል ነው የምትለው)

“ምን አይነቷ ነሽ? እውነት መስሏት ብትገባበትስ?” ተናድጄ ነው የማወራው። “ሀይልዬ ይሙት ብለሽ? በውሸት ትገይዋለሽ?”

“ባክሽ የእኔ አባት አክተር ነው አይሞትም!”

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...