Tidarfelagi.com

አል-ዑመሪ እና ሪቻርድ ፓንክረስት

በ1330ዎቹ ነበር። በዘመኑ የምሥራቅ አፍሪቃ ታላላቅ መንግሥታት በነበሩት የኢትዮጵያ ሰለሞናዊ አፄዎች እና የኢፋት ወላስማ ሱልጣኖች መካከል ታላቅ ጦርነት ይካሄድ ነበር። በጦርነቱ ከተሸነፉት የኢፋት መንግሥት ባለሟሎች መካከል ጥቂቱ ወደ ግብጽ ሸሹ። እዚያም ለግብጹ ሱልጣን የደረሰባቸውን ሽንፈት ሲያወሱ አንድ ጸሐፊ ያስተውላቸዋል።

ይህ ጸሐፊ ኢብኑ ፈድሉላህ አል-ዑመሪ ይባላል። አል-ዑመሪ በቤተ መንግሥቱ ያገኛቸውን የኢፋት ሰዎች ለቃለ መጠይቅ ጋበዛቸው። እነርሱም ፈቃደኛ ሆኑ። ታዲያ ዑመሪ በወቅቱ የሚካሄደው የጦርነት ወሬ ብዙም አልማረከውም። ከዚያ ይልቅ በኢትዮጵያና በምሥራቅ አፍሪቃ ስለነበሩት ሰባት ሱልጣኔቶችና ስለአፄው ግዛተ መንግሥት ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ (Socio-Economic) ሁኔታ መጠየቁን ነበር የመረጠው። በዚሁ መሠረት ስለኢፋት መሬት ስፋት፣ የመልክዐ ምድር ገጽታ፣ የተፈጥሮ ሀብት፣ አየር ንብረት፣ የግብርና ሁኔታ፣ እፅዋት፣ የዱር አራዊት፣ የቤት እንስሳት፣ የህዝቡ አሰፋፈር፣ የቤት አሰራር፣ የአመጋገብ ባህል፣ የአምልኮ አፈፃፀም፣ የቤት ቁሳቁስ፣ የግብይት ሁኔታ፣ የገንዘብ ዓይነቶች፣ የመንግሥት አገዛዝ ዘይቤ፣ የጦር ሰራዊት ወዘተ… የሚያወሳ ልዩ ልዩ መረጃ በመሰብሰብ “መሳሊኪል አብሳል- ፊ መማሊኪል አምሳር” በተሰኘ ዝነኛ ድርሳኑ ውስጥ አኖረው። ይህ መረጃም የኢፋት ሱልጣኔትን ጥንታዊ ገጽታ ለመረዳት እንደ መጀመሪያ ደረጃ የሚያገለግል ዓይተኛ መሳሪያ ሆኖ እያገለገለ ነው።

አል-ዑመሪ ከጻፋቸው መረጃዎች አንዳንዶቹ በጣም ያስደንቃሉ። ምሳሌ ልስጣችሁ።
• “ኢፋቶች ሁለት የዝናብ ወቅት ነው ያላቸው” ይላል አል-ዑመሪ። እነርሱንም “ኪረም” እና “በል” ይባላሉ ብሏል። አል-ዑመሪ ለማለት የፈለገው “ክረምት” እና “በልግ” ነው። ወቅቶቹን “ኪረም” እና “በል” ብሎ የጠራቸው መረጃውን የሰጡት ሰዎች በሚናገሩት ቋንቋ እንደዚያ ተብለው ስለሚጠሩ ነው። ይህ ቋንቋ በኔ ጥናት መሠረት የጥንቱ የ“ሀረላ” ቋንቋ ሆኖ አግኝቼዋለሁ (ዝርዝሩን በቀጣዩ መጽሐፌ ውስጥ አቀርበዋለሁ)።
• አል-ዑመሪ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለጤፍ የጻፈ ምሁር ነው። እንዲህ ይላል።
“በነርሱም ዘንድ በቋንቋቸው “ጣፊ” የሚሉት የእህል ዘር አላቸው። መጠኑ የጎመን ዘርን ያክላል። መልኩ ቀይ ነው። ከርሱም እንጀራ ይሰራል”
(ኢብን ፈድሉላህ አል-ዑመሪ፡ 2001፡ 40)
አል-ዑመሪ በብዕሩ “ጣፊ” በማለት የገለጸው “ጤፍ”ን ነው። ይህ ሰብል ለመጀመሪያ ጊዜ በጽሑፍ የተጠቀሰው በዚህ መልክ ነው። ደራሲው “መልኩ ቀይ ነው” በማለት የጻፈበት ምክንያት በዘመኑ ከቀይ ጤፍ በስተቀር ነጩ ጤፍ በኢፋት ምድር ስላልታወቀ ይሆናል። ታዲያ ሰብሉ የተጠራበት “ጣፊ” የሚለው ስም በስህተት የተፈጠረ አለመሆኑን ልብ በሉ። ይህም ስም መረጃውን ለደራሲው የሰጡት ሰዎች ከሚናገሩት ቋንቋ የፈለቀ ነው።
እንዲህ ነው አል-ዑመሪ! እርሱ እነዚህን መረጃዎች ባይጽፍልን ኖሮ በታሪክ ድርሳናት የምናነበው የጦርነት ወሬ ብቻ በሆነ ነበር። ይሁንና ከርሱ በኋላ የመጡ ጸሐፊዎች ይህንን አካሄድ አልተከተሉትም። በአብዛኛው የነገሥታትን ገድልና የጦርነት ወሬዎችን ብቻ ነው እንደ ታሪክ ሲጽፉ የከረሙት። በመሃሉ እነ ዐረብ ፈቂህ፣ ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ እና ጀምስ የመሳሰሉት ጥቂቶች የጻፏቸውን ስራዎች ለማየት ቢቻልም የጥንቱ የሀገራችን የታሪክ አጻጻፍ ሳይቀየር እስከ ሃያኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ዘልቋል። በሃያኛው ክፍለ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ የመጡ የአውሮጳ ምሁራን ግን ይህንን ያፈጀ ልማድ ከስረ መሠረቱ ቀይረውታል። በዚህ ረገድ ጎልተው የሚጠቀሱት እንደ ኤኖ ሊትማን፣ ኢኛሲዮ ጉይዲ፣ ካርሎ ኮንቲ ሮሲኒ፣ አውገስት ዲልማን እና ኤንሪኮ ቼሩሊ ናቸው። አዲሱን ምሁራዊ መንገድ ከጫፍ ላይ ያደረሰው ግን ሪቻርድ ፓንክረስት ነው።

ፓንክረስት የአዲሱ ፈር ቀዳጅ መንገድ ተከታይ መሆኑን ያሳወቀው ለመጀመሪያ ጊዜ ባሳተመው ስራው ነው። “The Economic History of Ethiopia” ይባላል። ከርሱ በፊት በዚህ ርዕስ ላይ ሙሉ መጽሐፍ የጻፈ ደራሲ አልነበረም። ፓንክረስት ሲቀጥል ደግሞ “History of Ethiopian towns” የሚል በጣም ጥልቅ የሆነ ድርሰት አቀረበ። በዚሁ መንገድ የኢትዮጵያንና የህዝቦቿን ታሪክ እየመረመረ በብዙ ርእስ-ጉዳዮች ዙሪያ በመዟዟር ታሪካችንን በድርሳናት መዘገበው።

ፓንክረስት ያልጻፈበት ርዕሰ ጉዳይ የለም። ስለጥንታዊ የብራና መጻሕፍት፣ ስለእደ ጥበብ ሙያና ሙያተኞች፣ ስለባህል ህክምና፣ ስለጀበርቲ ሙስሊም ነጋዴዎች፣ ስለጣሊያን ወረራ፣ ስለአክሱም ሃውልቶች፣ ስለላሊበላ አድራባት፣ ስለጥንታዊ የዋሻ ስዕሎች፣ ስለአፄ ቴዎድሮስና ጄኔራል ናፒየር፣ ስለኢትዮጵያ ዘመናዊ ደራሲዎች ወዘተ… ብዙ ጽፏል። የመሪዎቹንም ታሪክ በደንብ ጽፏል። ሌላው ቀርቶ የፎቶ ጥበብ ወደ ኢትዮጵያ ከገበባበት ጊዜ ጀምሮ ለስድሳ ዓመታት (ከ1867-1935) ፈረንጆች ያነሷቸውን በቀላሉ ሊገኙ የማይችሉ ፎቶዎችን በአንድ ጥራዝ ሰብስቦ ከልዩ ልዩ መግለጫዎች ጋር ያሳተመው ፓንክረስት ነው።

እኔ ፓንክስረትን በጣም የምወደው እንዲህ ዓይነት Multi-Dimensional በመሆኑ ነው። ይህንን የምትረዱት የታሪክ ጥናት ውስጥ ስትገቡ ነው። አብዛኛው ደራሲ በመጽሐፉ የሚዘግበው የጦርነትን ዜና ወይንም የፖለቲካ ታሪክን ነው። ሁሉም ነገር የጦርነት ወሬ ይሆንባችሁና ስልችት ይላችኋል። ፓንክረስትን የመሰሉ ጥቂት ጸሐፍት ግን በስራዎቻቸው ታሪክ ፈርጀ ብዙ መሆኑን ያሳዩአችኋሁና አንጀታችሁን ያርሳሉ።

——
የጥንቱ አል-ዑመሪ አንጀቴን አርሶታል። አላህ ይርሓመሁ!!
የዘመናችን ፓንክረስትም አንጀቴን አርሶታል። ዕድሜና ጤና ይስጠው!!

Afendi Muteki is a researcher and author of the ethnography and history of the peoples of East Ethiopia

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...