Tidarfelagi.com

አልወዳትም እንጂ አልጠላትም (ክፍል ሁለት)

“ከእኔና ከርሷ ምረጥ ብትባል?”
“ደሞ ጀመረሽ …. ተይ ኤዱ እረፊ…. ”
“ንገረኝ… ምን መስማት እንደምፈልግ ታውቃለህ!! … ንገረኝ!!” እጮሃለሁ … በጥፍሬ ቆዳውን እጫነዋለሁ …. ሚስቱ(እህቴ) ሰውነቱ ላይ ምንም ምልክት እንድታገኝበት አይፈልግምኣ …
“አንቺ!!.. አንቺ ትበልጫታለሽ!” ይለኛል። ከሚስቱ ንፁህ ልብ እና ከእኔ እብድ ጭን መሃል እየዋለለ … ቃላቶቹ አፉን ለቀው ሲወጡ ይጎመዝዙታል….. ያስታውቅበታል። …..

ፍቅር ይሁን ተንኮል አልጋው ላይ የምሰራው አይገባኝም ….. ፍቅር የያዘኝ በውጊያችን መሃል ከሚነግረኝ ቃላቶች ነው …. የሰውነታችን ግብ ግብ ብዙም አይስበኝም ….
እሱ ከህሊናው ይልቅ ግለቱ ያሾረዋል!! … እኔ ከህሊናዬ ይልቅ ቅናቴ ያነደኛል። … ሁለታችንም ፀፀት አለብንኮ …. እንደ vampire diaries ቫምፓየሮች … let us shut it down! ብለን የምንዘጋው የህሊና ማስቀመጫ ሳጥን የለንም …
ነገሩ አንደኛው ስሜት ሌላኛውን የመደፍጠጥ ጉልበቱ ነው …. እሱ ፀፀቱን በደምስሩ የሚንቀለቀል ግለቱ ይበልጥበታል። እኔ ቅናቴና እሷን ለመብለጥ ያለኝ ፉክክር ፀፀቴን በብዙ እጥፍ ያስከነዳል። … ወጥረን እንዋጋለን!!
እኔ እሷ መሳተፏን እንኳን በማታውቀው ውግያ ማሸነፌ ሲነገረኝ ….. የምን ፀፀት … የምን ህሊና… የምን ሲኦል …..
“ለእሷ እንዲህ አድርገህላት ታውቃለህ?”
“አዎ”
“አልፈልግም በቃ አቁም!! …. አልፈልግም አልኩ እኮ ” እጮሃለሁ ….
“እሷ ግን እንዳንቺ አትጣፍጠኝም!” (ውሸቱን እንደሆነ አውቃለሁ …. ቢሆንም ደስ ይላል)
“እሺ አታቁም …. ቀጥል” እላለሁ ፈገግ ብዬ
…..
…..
….
አንድ ቀን ሀቅ አመለጠው …”እውነቱን ልንገርሽ … አልጋ ላይ ትበልጫታለሽ …. ልቧ ግን ይበልጥሻል። ንፁህ ሴት ናት እሷ!”
“ውረድልኝ ወደዛ …. እላዬ ላይ ዘጥ ዘጥ እያልክ ስለንፁህነት በሙሉ አፍህ ታወራኛለህ?”
አስጠላኝ ….. ሲደውል አላነሳለትም …. በየቀኑ የሚፀፀትበትን ውጊያ ለመዋጋት ለምን እንደሚለምነኝም አይገባኝም ….. !!!
…..
…..

“አይዞሽ ኤዱ አይዞሽ..” ይለኛል የእህቴን ሬሳ ልሰናበት በቆምኩበት የሚንዠቀዠቅ እንባዬን እያየ
‘የምርህን ነው ግን እንዲህ እየተንፈራፈርክ የምታለቅስላት?’ ልለው ያምረኝና … እኔስ የምሬን ነው? ለምንድነው የማለቅሰውስ? … ምናልባት እሱም ከቅንዝራምነቱ አስበልጦ አይወዳት ይሆናል እንጂ ይወዳታልኮ …. እኔም ከቅናቴ አያይልም እንጂ…. እህቴኮ ናት!!
አለቀስኩ ….. ምርር ብዬ እየተንገፈገፍኩ አለቀስኩ … ለሷ ይሁን … ለራሴ… ለሀጢያቴ … ለፀፀቴ ….. ብቻ ድንኳኑ ገና አሁን ሞቷን የተረዳ ይመስል በለቅሶ ግልብጥብጡ እስኪወጣ እሪሪሪሪሪሪሪ አልኩ …..
“ገደልሽ ….. ገደልሽኝ …… ገደልሽኝ” ደጋግሜ የምለው ይሄን ነው …… ያደረግኳትን ሁሉ በሞቷ ተበቀለችኝ ….
……
የሙሽራ ቀሚሷን ካበላሸሁባት በኃላ … ለወራት አኩርፋኝ ነበር …. ሌላ የተገኘውን ቀሚስ ሚዜዎቿ ተከራይተው ተሞሽራ አለፈ። ….
“ትጠይኛለሽ?” አለችኝ ከወራት በኃላ እቤት መጥታ …
“አልጠላሽም!” አልኳት
“ታዲያ ለምንድነው ሀዘኔን ማየት የምትፈልጊው? እኔ ምንድነው የበደልኩሽ?”
“ምንም! …… አላውቅም!! ምናልባት አንቺን ከምወድሽ በላይ ራሴን እጠላዋለሁ መሰለኝ …. አላውቅም!!”
“ኤዱዬ በስመአብ ወልድ …. !!(አማተበች) እሺ ለምን አታወሪኝም? ልስማሽ ንገሪኝ!”
“መናገር እንደማይሆንልኝ ታውቂያለሽ!”
አቅፋኝ ብዙ ቆየችና “እሺ እኔ ምን ላድርግልሽ? ኤድዬ ለኔኮ ያው መንታ እህቴ ነሽ…. ከአንድ ማህፀን አለመውጣታችን it doesn’t matter at all… እንዲህ አድርጊ በይኝ ላንቺ ጥሩ ስሜት ከሰጠሽ አደርጋለሁ።”
“ማሸነፍሽን ተይኝ!!” አልኳት ሳላስበው …. ግራ ገባት …. “አየሽ …. የሰርግ ቀንሽን አበላሽቼብሽ እንኳን ምንም እንዳላደረግኩኝ …. ጭራሽ ታዝኚልኛለሽ …. እኔ ልጥልሽ እታገላለሁ …. አንቺ ሳትታገዪ ሁሌም ታሸንፊኛለሽ …. ተይ በቃ …. እንደ እኔ ክፉ መሆን ባትችዪ እንኳን መልካም አትሁኚልኝ!!”…
በጣም ግራ ተጋብታ ስታየኝ ቆይታ
“ኤዱዬ እባክሽ ሳይካትሪስትጋ ሂጂ …. ቢያንስ ስትተነፍሺ ይወጣልሻል። ቁጣሽ ይበርዳል!!” አለችኝ …… አልሰማችኝም ….. ያልኳት አንዱም አልገባትም ….. አሁንም በለጠችኝ!!! ለዛ ነው የማላወራው …. ለማንም አይገባም ….
……
…..
….
“ገደልሽኝ …. ገደልሽኝ ….. ” እሪታዬን ማቆም አቃተኝ ….. ድምፄ እየተዘጋ መጣ ….. አባቴ መጥቶ ከወደቅኩበት አነሳኝ …..
“ልቀቀኝ …. ልቀቀኝ!” ብዬ የጮህኩት ምንም የማክበር ለዛ በሌለው ቁጣ ነው …. ደንግጦ እጁን አሸሸ…. ራሴን ፈራሁት … እሱም የፈራኝ ይመስላል …… እንዳልፈነዳ እና እንዳልፈጀው ….
……
…..
…..
ለመጨረሻ ጊዜ ‘አባ’ ብዬ የጠራሁት ቀን 17 ዓመቴ ነበር ….. እንባ እና ንፍጤ ፊቴ ላይ ተለዋውሰው …. እንደ አባት መከታ እንዲሆነኝ ዓይን ዓይኑን እያየሁ … ባለፈው እህቴ ከትምህርት ቤት ስትመለስ መንገድ ላይ ጎረምሳ በጥፊ መቷት … እያለቀሰች ስትነግረው ደም ስሩ ተገታትሮ እየፈላ ሄዶ ልጁን አሩን እንዳበላው …. ‘እኔ አባትሽ እያለሁ’ እንዲለኝ …..የእኔማ ይብሳል …. ይገድላቸዋል…. የገዛ ቤቱ … ልጁ ተደፍራ … አለቀላቸው ….
“አባ …” መናገር አቅቶኝ እንሰቀሰቃለሁ …. ሲጨነቅ ቆይቶ
“ይሄን ጉድ ለማንም እንዳትናገሪ የኔ ልጅ !!” አለኝ … የቱን ጉድ እንደሆነም በደንብ አልገባኝም … እኔ በአራት ጎረምሳ መደፈሬ? ወይስ ከደፋሪዎቹ አንዱ አብሮን የሚኖረው የሱ ወንድም ልጅ መሆኑ? እቤቱ መሆኑ? ….
“የኔ መደፈር ነው የሚያሳስብህ ስምህ?” አልኩት ተናግሬው በማላውቀው ቁጣ
“መደፈር ብለሽ ጭራሽ ነገሩን አታጋኚው …. ድንግል የነበርሽ ነው የሚመስለው። ሲጀመር ክፍልሽ ድረስ አራት ጎረምሳ ምን ስታደርጊ አስገባሽ?”
እንባዬ ደረቀ …”ቤቱ ነውኮ …. ወንድሜ ነውኮ …. እህቴ ናት ብሎ ነው ለጏደኞቹ ያስተዋወቀኝ….ሰላም ልንልሽ ነው ብለው ነው የገቡት … ውጡ ልበላቸው? ይሄ ይሆናል ብዬ አስባለሁ?” ማስረዳት ቸገረኝ…..
“ወንድምሽ አይደለም። ልጄ … ነገሩን የባሰ አፀያፊ እያስመሰልሽው ነው። … በደም እንደማትዛመዱ ታውቂያለሽ!! ቀድሞውኑ እንደ እህትሽ ስብስብ ብለሽ ብትቀመጪ ……”
ከዛ በኃላ ያወራውን ብዙም አልሰማሁትም ….
“እሱ ወንድሜ ካልሆነ … እሷስ በምን በኩል እህቴ ሆነች? አይደለችም!” አልኩት …..

አልወዳትም እንጂ አልጠላትም (ክፍል ሦስት )

One Comment

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...