እንድትሞት በጭራሽ አልፈልግም ነበር። ስለምወዳት አይደለም !!!…. በቁሟ ልበልጣት …. ላሸንፋት ነበር ትግሌ ….. ሞቷማ ኪሳራዬ ነው።
የሞቷ ቀን ማታ በሬን አንኳኳች …….. ደፈራርሰው ያበጡ ዓይኖቿ …. የተንጨባረረው ፀጉሯ ….የሚንቀጠቀጡ እግሮቿ … የሆነ ነገር እንደተፈጠረ ገባኝ።
“ትዳሬን? ኤዱዬ ፍቅሬን? እንዴት እንደምወደው እያወቅሽ? ምን ብበድልሽ ነው እንዲህ የከፋሽብኝ? እስኪ ንገሪኝ እኔ ምንድነው ያደረግኩሽ?” ከንፈሯ ይንቀጠቀጣል….. እንባዋ ይከታተላል ….. አሳዘነችኝ …. ማታ አልጋቸው ላይ ሲዋደቁ የእኔን ስም እንደጠራባት ነገረችኝ … ፈገግታዬ አመለጠኝ።
“ይሄን ነው prove ማድረግ የፈለግሽው? ከኔ የተሻልሽ መሆንሽን ከባሌ ጋር ተኝተሽ ነው ማረጋገጥ የምትፈልጊው?” እየተናደደች መጣች …” …. ጤነኛ አይደለሽም ….. ይሄ በሽታ ነው!….. ” ደሞ ምልስ ትልና አሳዛኝ ትሆናለች … “እንዴት ክፉ ነሽ ግን በማሪያም?….” ኩርምት ብላ ትንሰቀሰቃለች።
ዝም ብዬ እሰማታለሁ። …. ስታለቅስ… ምን ያህል ክፉ ሴት እንደሆንኩ ቃላት እየቀያየረች ስትነግረኝ… ስትናደድ … አንድ ሰዓት ያህል ዝም ብዬ ሰማኃት …
ለምንድነው የመሸነፍ እንጂ የድል ስሜት የማይሰማኝ ታዲያ? ….. በክፋት መብለጥ የለም ይሆናል….
“ታውቂያለሽ ወንድምሽ ከደፈረኝ በኃላ አብሬው የተኛሁት ወንድ ባልሽ ነው!!” አልኳት …. (አታውቅም… እንደማታውቅም አውቃለሁ። …. ፊቷ የሆነ ነገር የፈነዳበት ይመስል ተመሰቃቀለ።)
“ቤተሰቦችሽ እኔ ለተደፈርኩት … እህትሽ ከሰማች ትጎዳለች … እንዳትሰማ ብለው ተጠነቀቁልሽ። … አስበሽዋል? እኔ እሳት ውስጥ ሆኜ እየነደድኩ …. ሙቀቱ አንቺን እንዳይነካሽ እየከሰልኩ ዝምም ጭጭጭጭ ብዬ ስነድ?”
ዝም አለች። ክው ብላ ደርቃ ከአፌ የሚወጡት ቃላት የሆኑ የሞት ፍላፃዎች ይመስሉ እየተንቀጠቀጠች ትጠብቃቸዋለች …..
ሁሌም እንደዛ ነበር … የሆነ የተረገመ ቀን እቤታችን የመጣች እንግዳ
“በስመአብ ቁልጭ እናትሽ አይደል እንዴ? ነፍሷን ይማረው ፀጉሯን እንዲህ ማስያዝ ትወድ ነበር እሷም!” ብላ የማውቅ የመሰላትን ቦንብ ከማፈንዳቷ ቀን በፊት
‘ውይ ልጄ ደረቅ ዳቦ አትወድምኮ’ ተብሎ እኔ ደረቅ ዳቦ ስበላ ለእህቴ እንቁላል መሰራቱን በክፉ ተርጉሜው አላውቅም ነበር።
‘እሷ ጎበዝ ተማሪ ስለሆነች’ ተብሎ እሷ የግል ትምህርት ቤት ስትማር እኔ የመንግስት መማሬን ጉብዝናዋ የሰጣት ሽልማት ነው ብዬ ከማሰብ ዘልዬ አላውቅም።
‘እሷ ቆንጆ ስለሆነች ጎረምሳ አያስኬዳትም’ በሚል የሚያመላልሳት መኪና ሲከራዩላት … እኔ ጥፍጥፍ መሆኔን አምኜ ከሷ ትምህርት ቤት የሚርቅ ትምህርት ቤቴን መንገድ በእግሬ እየፈጨሁ ለእህቴ ጥበቃ ከመደሰት ያለፈ የተሰማኝ አልነበረም።
እህቴ ናታ…. በመልክም በባህሪም በጭራሽ የማንመሳሰል መንታ እህቴ ….
“እናቴ ማናት?” ብዬ ጎፈላሁ እንግዳዋ ከሄደች በኃላ ….. 13 ዓመቴ ነው። እናቴ(አሳዳጊዬ) እህቴ እንዳትሰማ እሽሽሽሽ አስብላኝ
“ይሄን ነገር ግን በፍፁም እህትሽ እንዳትሰማ… እንዴት እንደምትወድሽ ታውቂያለሽ አይደል? ቃል ግቢልኝ በፍፁም ለእህትሽ እንዳትነግርያት …. ” ብላ መርዶዬን ነገረችኝ …. እናቴ የኛን ቤት ተከራይታ የምትኖር የቡና ቤት ሴት እንደነበረችና እኔን ስትወልድ እንደሞተች ነገረችኝ …..
አሳዳጊዎቼ ልጅ የመውለድ ተስፋቸው ባዶ መሆኑን በዶክተርም በጥበቃ ብዛትም ባረጋገጡበት ወቅት የእኔ እናት እንደ ተዓምር ከማን እንዳረገዘች የማታውቀውን ልጅ ልታስወርድ ዱብ ዱብ ስትል ነው አሳዳጊዎቼ በደስታ እኔን ሊያሳድጉኝ ቃል ገብተውላት እናቴ የወለደችኝ …. ቆይ ….!!!! እህቴ ከእኔ ጋር ግብ ግብ የጀመረችው ገና ሳላውቃት
ሳታውቀኝ … በእናቴ ሆድ ሆኜ ነው…
ለዓመታት ልጅ አልሸከም ያለው የአሳዳጊዬ ማህፀን ልክ እናቴ ሆድ እኔ መደላደል ስጀምር እህቴን ቋጠረ። …. ውድድሩ ተጀመረ….
“በቃ አሁን የራሳችንን ልጅ ስላገኘን ልጅሽን የማሳደግ ፍላጎታችንን ትተነዋል” ብለዋት እንደነበር አድጌ ያቺ እንግዳ ናት የምትነግረኝ … እናቴ በማላውቀው ምክንያት ልትወልደኝ ወሰነች…. ስትወልደኝ ሞተች። አሳዝኛቸው…. ወይም ልውሰዳት ያለ ዘመድ ስለጠፋ… አልያም እግዜሩን ፈርተው ለፅድቅ ትሆነናለች ብለው … አላውቅም። ወሰዱኝ…… በወሩ እህቴ …. መንታዬ ተወለደች።
ቤተሰብ ያጣሁት እኔ …. የኖርኩት ህይወት ሁሉ እንክትክት ብሎ የውሸት ካብ ሆኖ የተናደብኝ እኔ …. የተዋሸሁት እኔ …. “እሷ ከሰማች ይከፋታል…” ተብሎ የምትጠበቀው እሷ ….
“ለምን አልነገርሽኝም? እንዲህ ሁሉ ስትሆኚ ምናለ ብትነግሪኝ? ይሄ ጅብ እንዴት እህቱ ላይ እንዲህ ያደርጋል?” አለችኝ መልሳ ወንድሜ የምትለው የአጎቷ ልጅ ከጏደኞቹጋ ያደረገኝን ስነግራት … ባሏን እንዳባለግኩባት ረስታው አቅፋኝ ለእኔ መንገብገብ ጀመረች …..
“ቤተሰቦችሽ ሁሉም ነገር በደም ካልተገመደ ዋጋው አይታያቸውም ….. በደም ስለማንገናኝ እህቱ አልነበርኩም ….. ደም ስላልፈሰሰኝ ደፈረኝ እንዳልል ዝም አስባሉኝ …. ስህተት ነው ተባለለት …. ድሮም የጀመረችው ነው ተባለና የሱን አውሬነት በእኔ ጥፋት ከደኑለት ….. እሽሽሽሽሽሽ ዝም በይ ተባልኩ።”
አሁንም ልክ እንደ ቅድሙ መንሰቅሰቅ ጀመረች …..
“በህይወቴ አንድ ነገር ይሁንልሽ ብሎ ፈጣሪ ቢጠይቀኝ ምን እንደምሻ ታውቂያለሽ?” አልኳት ….
“ምንድነው?” አለችኝ ማድረግ የምትችለው ነገር ቢሆን አሁኑኑ የምታሳካልኝ በሚመስል ጉጉት
“አንቺን እንዲያደርገኝ …. አንቺን መሆን”
ዝምምምምም አለች።….. አሳዘንኳት …. ዝምምምም አለች …..
“እሺ እኔ ምን ላድርግ? እነአባቢን ልጣላቸው? ያ ደስ ይልሻል? ወይም እኔን እንደሚወዱኝ እንዲወዱሽ ልንገራቸው? ስራ ልተው? ስራ ባይኖረኝ ደስ ይልሻል? አብርሽን ብቻ ተይልኝ አትበይኝ …. እሱን አልችልም…. ኤዱዬ እሱን ከራሴ በላይ እወደዋለሁ። ሌላ የፈለግሽውን ላድርግልሽ እንዳሸነፍሽኝ ከተሰማሽ…” አለችኝ ……….
አዎ በክፋት አይበለጥም ……… ይኸው አሁንም በዝረራ አሸነፈችኝ ….
“ውጪልኝ!!” አልኳት በቀስታ ….. “ውጪልኝ …. ከህይወቴም ከቤቴም ውጪልኝ … ” እያልኳት ለራሴ ‘በቃኝ’ እላለሁ ….. ርቄ እሄዳለሁ … ሁላቸውንም የማላይበት …. ሁሉንም ከኃላዬ ጥዬ ብንንንንንን ብዬ እሄዳለሁ ….
3 Comments
በርቺልኝ ❤❤👌👌
great!!!