Tidarfelagi.com

አለመታደል ነው ቀላውጦ ማስመለስ ( የመጨረሻ ክፍል)

“ታውቃለህ? ምን ማድረግ እንዳለብኝ አላውቅም። ትክክል መሆኑንም እንጃ!” አለችኝ እቤት እንደገባን
“ምኑ?”
“የሚሰማኝ ስሜት”
“ምንድነው የሚሰማሽ?” ከአፏ የሚወጣው ዓረፍተ ነገር ምንም ቢሆን እኔ ጆሮጋ ሲደርስ ‘ላንተ ፍቅር‘ የሚል ቢሆን እየተመኘሁ
“በደለኝነት፣ ሀጢያተኝነት፣ ጥፋተኝነት……ከዳተኝነት… ክምር ወቀሳ!” ጭንቅላቷን ይዛ ጫማዋን እያንቋቋች ተረማመደች። ልቤን ሲበርደው ታወቀኝ።
“ለምን? በምን ምክኒያት?” የራሴ የማይመስል ድምፅ ነው ያወጣሁት። እግሬም የዛለብኝ መሰለኝ እና ተቀመጥኩ።
” ታውቃለህ? ድሮ ድሮ የዛሬ 8 ዓመት በድብቅ ፍቅር እንደጀመርን አንድ ቀን ከሰፈር አርቆ ይዞኝ ሄደ። … … ሁለታችንም ህይወት እንደምናያቸው የፍቅር ፊልሞች መጨረሻቸው ግጥምጥም ግጥምጥም ብሎ… … ‘በደስታ ለዘለዓለም ኖሩ‘ የሚሆን የሚመስለን ወቅት… (የወቅቱን ስሜት በትዝታ ልጓም ጎትታ እንደመቦረቅ እያለች) …… የሆነ ህንድ ፊልም ላይ እንዳየው የእኔንም የሱንም የቀኝ እጅ የቀለበት ጣታችንን ጫፍ በምላጭ ቆርጠን አደማነው። …… ያስቃል አይደል? የሆነ የጅል ቀልድ ነገር ይመስላል? ግን አያስቅም እሺ… … የሁለታችንንም የደሙ ጣቶች አጋጥመን ቃል ገባልኝ። ቃል ገባሁለት። …… እሱ የገባልኝን ቃል የኖረው ሁለት ዓመታት ብቻ ነው። …… እኔ እያንዳንዷ ቃሌን ለመጠበቅ ስምንት ዓመታቴ ተቀርጥፈው ተበሉ። … ለሱ ብዬ ሁሉንም ተውኩ። ለማንም ወንድ ልቤንም አካሌንም አስደፍሬ አላውቅም።…… እስከህይወቴ ፍፃሜ በልቤ ከርሱ ሌላ ላይነግስ ምዬለታለኋ? ምን እንደሚሰማኝ ታውቃለህ? ደሙ በደሜ ውስጥ ያለ (ትኩረቴን ላለማጣቷ እያረጋገጠች ) …… እውነታው ባይገጣጠምም እኔ ግን እዛው የዛሬ 8 ዓመት ላይ ነኝ። …… ” ማውራቷን አቋርጣ ማልቀስ ጀመረች። ሞቅታውም እያገዛት መሆኑ ገብቶኛል።

” ታውቃለህ አይገባህም! እኔን ስትሆን ብቻ ነው የሚገባህ!”
አንዳንዴ ከምክኒያታዊነት የሚልቅ ስሜት እንዳለ አሰብኩ። … በቦታው ስትገኝ ብቻ የሚገባህ… …… አለሟ ትዳሯ ነው። አለሟ ቤቷ ነው። አለሟ ልጇ ናት። አለምን እንደማሸነፍ የላቀ ምን ሀሴት አለ? ምንስ ስኬት ይኖራል? ትዳሯን እንደገና ማሸነፍ… … እንደገና በሱ ልብ መንገስ… … ለልጇ የምትወደውን አባቷን መመለስ…… አለሟን የራሷ ማድረግ……
ሲመስለኝ ያልተረዳችው ነገር አብዛኛው ወንድ ወደድኩሽ ሲል ሊያስመስል ይችላል። ጠላሁሽ ካለ በቃ ማለቱ ነው። …… አርሴማን ሊወስድ ሲመጣ እግረ መንገዱን አብሯት መተኛቱ ከፍቅር ጋር ተካልሶባታል …… የነሳትን ክብር ጋርዶባታል።
“አንዳንዴ እንዲጠላኝ ያደረው ፖሊስ መሆኔ ነው ብዬ አስብና ራሴን ወቅሳለሁ። ምናለ እሱ እንደሚፈልገው የቤት እመቤት ብሆን? እላለሁ! ልጄ በየቀኑ የምታየው አባት ይኖራታል።”
ለንፅፅር የምታቀርበው ነገር ሲኖርህ ነው የተሻለ እና የባሰ ብለህ ደረጃ የምታወጣው። እሷ ከእርሱ ውጪ የምታውቀው የላትም። …… በምን ንፅፅር የምትለውጠው ህይወት የተሻለ መሆኑን ትመዝናለች?
“ታውቃለህ አንዳንዴ እርግፍ አድርጌ ትቼው ቤተሰቦቼን ሄጄ ይቅርታ ልለምናቸው አስቤ አውቃለሁ። …… ያሳፍራል አይደል? እሱ ይበልጥብኛል ባልከው ሰው ተክደህ በሚያነክስ ልብ መመለስ? …… አሁን እረፍዷል… … 8 ዓመት ዘግይቻለሁ። …… ግን ምን የሚሉኝ ይመስልሃል? ዘመድ አዝማድ እየተጠቋቆመ ቅስሜን የሚያደቀው አይመስልህም?”
ሰው እንኳን ወድቀህ ተመቻችተህለት ክርስቶስ ሰው ሆኖ ቢመጣ በመኮነን የተቀባበለው ፍጡር ነው።… … ምንም የሰራኸው ሃጢያት ባይኖር በእናትህ በደል አንተን ይፈጅሃል።…… ለድርጊት ፈሪ የሆኑ ሰዎች ማድረግ የሚችሉት የሰውን ውድቀትና ጥፋት መንቀስ ብቻ ነው። …… ስምሪት ሰው የራሱ ጉዳይ የማለት አቅም ያላት ሴት እንዳይደለች አውቃለሁ። … … ቤተሰቦቿን በተመለከተ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለብኝ ይሰማኛል። ጊዜው በትክክል መቼ መሆኑን ባላውቅም። በሞቅታ ስለምታወራ ከመስማት ውጪ አፌን አላላቀኩም።
“ታውቃለህ ለሷ ብለህ ምንም ለመሰዋት የተዘጋጀህላት ህፃን ልጅህ ምርጫ ቢሰጣት እሱን እንደምትመርጥ ማወቅ እብደት ቅልቅል ያለው ስሜት እንደሚሰጥ? አታውቅም!! …… ህፃን ናት በሷ እኮ አልፈርድም። የሚሰማኝን ፍርሃትና ህመም ግን ልታውቀው አትችልም። …… ለነገሩ አንተ የምትሳሳለት ሰው ኖሮህ አያውቅም።” አለችኝ
ኖሮኝ አያውቅም። እስከገባኝ ድረስ በአንዲት ክስተት ስለእርሷ የተገለጠልኝ ስስት ግን የሶስት ዓመት ጥርቅም እንጂ የዛች ቅፅበት ብቻ አልነበረም። …… ሶስት ዓመት ሙሉ በያንደንዷ የስራ ቀን የቀኑን መንጋት ያህል ስምሪት የተለመደ ክስተቴ ነበረች። …… ቡና አብሪያት ስጠጣ… … ስትናደድ ጉንጯ ሲቀላ ደስ ስለሚለኝ ሳበሳጫት፣ ለማንም የማላወራውን ስሜቴን ሳወራት፣… …… እሷ እንደማውቃቸው ሴቶች አልነበረችም። ……… አሁን ያን ላስረዳት አልሞከርኩም። …… ከብዙ ወሬዋ በኋላ አልጋው ላይ ተጋድማ ማውራቷን ቀጠለች። …… እያወራች እንቅልፍ ይዟት ሄደ። …… አልቀሰቀስኳትም አጠገቧ ተጋደምኩ። ……

“እናትህ ማገገሚያ ነው ያሉት።” አለችኝ ጠዋት ቀድማኝ ተነስታ ያበሰለችውን ቁርስ እየበላን… … ዝም አልኩ። ቀጥላ በምትጠቀማቸው ሱሶች ምክኒያት መግባቷን አከለችልኝ።…… ደነገጥኩ? አዘንኩ? ላያት እፈልጋለሁ? ስሜቴ ድብልቅልቅ አለ። …… ከስምሪት ጋር ከነጋ ከተወሰኑ ቃላት በላይ አልተነጋገርንም። ልቤን ከብዶኛል።
…… ምንም የማውራት ፍላጎት የለኝም። ብዙ ዝም ካልኩ በኋላ
“የት ነበረች?”
“እናታቸውጋ ድሬዳዋ!”
አያት እንዳለኝ ዛሬ ገና መስማቴ ነው።
የረባ ቃላት ሳንለዋወጥ አማኑኤል ሆስፒታል ደረስን። ሳያት ምን እንደምላት አላውቅም፣ ባታውቀኝስ? የለየላት እብድ ሆና ቢሆንስ? ቆምኩ። የተዘጋጀሁ አልመስል አለኝ። ስምሪት ገብቷታል። …… እየደጋገመች እጄን ትጨምቀኛለች። እሷም ተጨንቃለች። ……
ልክ ሳያት ልጨብጣት? ልቀፋት? ፈገግ ልበል? ላልቅስ? የትኛው ላለሁበት ቦታና ስሜት እንደሚመጥን አላወቅኩትም።
ስታየኝ ለመመለስ ፈልጋ ነበር። ስምሪት ቀድማ አቀፈቻት። ምንም ሳልናገር አጠገቧ ሄጄ ተቀመጥኩ። …… ሳላገኛት በፊት ብዙ ጥያቄዎች ብትመልስልኝ ደስ ይለኝ ነበር። …… ከእድሜዋ በላይ አርጅታለች። … ሰውነቷ ተጎሳቁሏል። …… ማለት የቻልኩት ዝም ብቻ ነው።
“ትልቅ ሰው ሆነሃል!” አለችኝ ፊቷን ከኔ አዙራ… … እያለቀሰች እንደሆነ አውቃለሁ። …… ላባብላት እፈልጋለሁ ግን አላደርገውም። …… ድንገት ለመሄድ ተነሳች። ሳላስበው እጇን ያዝኳት።
“የቱንም ያህል ብትጠላኝ አልፈርድብህም። ይገባሃል።” አለችኝ ፊቷን ደብቃኝ
“አልጠላሽም። ባታወሪኝ እንኳን ትንሽ ደቂቃ አጠገቤ ሁኚ።” አልኳት። ድምፅ አውጥታ እያለቀሰች ተቀመጠች። ስምሪት አብራት ታነባለች። የማደርገው ጠፋኝ። ……
“እያስጨነቅሽኝ ነው። እባክሽ አታልቅሺ። ” አልኳት አቅፌ ባባብላት ደስ ይለኛል። የሚሰማኝ እሩቅነት ነው። እጄን ሰድጄ መለስኩት። …… በዝምታ ብዙ ካወራን በኋላ ተነሳሁ።
“መጥቼ አይሻለሁ። … ” አልኳት። ብርግግ ብላ ተነሳች። አንድ እርምጃ ጀርባዬን ሰጥቻት እንደተራመድኩ
“ባቢሾ?” ብላ ጠራችኝ። የቤት ስሜ ነበር። አጠራሯ የፈለገችው ነገር ኖሮ ልትጠይቀኝ የፈራች ይመስላል። …… ምን ቸግሯት ይሆን ብዬ እያሰብኩ ተጠግቻት
“ምነው?” አልኳት
በጣም እያመነታች ቀና ብላ እያየችኝ እጇን ወደ ፊቴ እያስጠጋች
“አንዴ ልንካህ?” ስትለኝ ጭንቅላቴ በከባድ ነገር የተመታ መሰለኝ። ያ ስሜት ለዘመናት የያዝኩባትን ቂም የማጠብ አቅም ነበረው። ልጇን ለመንካት ያስፈቀደች እናት ህመም የእኔ እናት ህመም ብቻ ነው። የዘረጋቻቸውን እጆቿን ሳምኩላት። …… እናትነት እንዲሰማት ማድረግ ተመኘሁ። ……
“ልጅሽ እኮ ነኝ!! ብትቆነጥጪኝ እንኳን በኔ ላይ ስልጣን አለሽ!!” አልኳት በእጇ አንገቴን ፀጉሬን ፊቴን ደባብሳኝ በቆምኩበት ጥላኝ ሄደች።…… ብቻዬን መሆን ፈለግኩ። ስምሪትን ተሰናብቻት ማሰብ እስካቆም ጠጣሁ። ………

የሚቀጥሉትን ቀናት የተለመደው አይነት ህይወት ቀጠልኩ። … አዲስ ነገር እናቴን እየሄድኩ አያታለሁ።… … አንዳንዴ ከስምሪት ጋር እንሄዳለን። ስላለፈው አናነሳም። …… ከስምሪት ጋር ልክ እንደበፊቱ ሆንን። ምንም እንዳልተፈጠረ፣ ሳያት ምንም እንደማይሰማኝ፣ ስታረፍድ እንደማልንቆራጠጥ… …
አንድ ቀን ባሏ ሲመጣ ሳትኳኳል እንደጠበቀችው እና አስጠሊታ መሆኗን ነግሯት ልጁን ይዞ እንደሄደ ነገረችኝ። ……
በተደጋጋሚ ይሄን በማድረጓ ሴክስ ማቆማቸውን ነገረችኝ።
ከሳምንታት በኋላ ወደ ድሬዳዋ አያቴጋ መሄድ እንደምፈልግ ስነግራት እሷም ፈቃድ ወስዳ አርሴማን ለአባቷ ሰጥታ አብራኝ ሄደች። …… አያቴ ደስ የሚሉ አሮጊት ናቸው። ማን መሆኔን ሲያውቁ ሰፈሩን በእልልታ አቀወሱት። ሶስት ቀን አብረናቸው ከረምን። ስለእናቴ ማወቅ እንደምፈልግ ስነግራቸው። ሲያድበሰብሱብኝ ቆይተው። እርሳቸውም ሴተኛ አዳሪ እንደነበሩ ነገሩኝ።
“ያስተማርኳት እንጀራ አልጋ ላይ እንደሚጋገር እንጂ ት/ቤት አይደለም። አትፍረድባት።እኔ ስታመም እሷም ትምህርቷን አቋርጣ በዚሁ ቀጠለች። ከፍ ስትል አንዱ ጥጋበኛ እዚህ ቁምስቅሏን ሲያሳያት አዲስ አበባ ገባች።” ብለው ታሪኩን ቋጩት ሀዘን አንጀታቸው ስር እንደተነጠፈ ገብቶኛል። እንዲቀጥሉልኝ ጎተጎትኳቸው
ያገባችው ባሏን በጣም ትወደው እንደነበር ከቡና ቤት እንዳገባት ነገሩኝ። ‘ጥጋበኛ‘ ያሉት ሰው አዲስ አበባ ገብቶ የባሏን ‘ንብረት‘ ሰልቦት እንደመጣ ሲነግሩኝ ፊልም ነገር ነው የመሰለኝ። ……
“ከዛ ምን አለፋህ እሷ እንደበደለችው እያመሃኘ ስራው መጠጣት ሲሆን ቡና ቤት ተመልሳ መስራቷን ቀጠለች።…… ከኔም ጋር ለብዙ አመት ተቆራረጠች።…… የማትላቀቀው ሸክም ሆነባት። በዚህ መሃል አንተ መጣህ!! ቤቱን አባትህ ነው የገዛላት! (የማውቀው ቤተሰቦቿ እንዳወረሷት ነበር) አባትህ ቱሪስት ነበር። ሀገሩ ኑሮ ስለነበረው ጥሏት ሄደ። አንተ መፈጠርህንም አያውቅም። …… በል በቃህ!!” አሉኝ… …

ደስ ደስ የሚል ስሜት እየተሰማኝ አዲስ አበባ ደረስን። …… ስምሪትን ልሸኛት እቤቷ ስንደርስ ባሏ አለመኖሯን አይቶ ሲመለስ ደረስን። ብዙ ስድብና ጥቂት ጥያቄ ቀላቅሎ አምባረቀ። ልትከላከል በማያስችላት ፍጥነት በጥፊ አላት… በምን ፍጥነት እንዳደረግኩት አላውቅም። በቡጤ ጉንጭና አገጩን አጎንኩት። ስምሪት መሃል ገባች። ተወራጨ። ካልገደልኩት ብሎ ኡኡ አለ። ስምሪት መሃል ስለገባች እንጂ እንደፈራ ያስታውቅበታል።
“ሴት የሚማታ ወንድ ከወንድ ጋር የመደባደብ ብቃት የለውም። ሽንታም!!” ካልኩት በኋላ ስምሪትን ያስከፋኋት ስለመሰለኝ አየኋት ጥርሶቿ ባይስቁም አይኖቿ ሲስቁ አስተዋልኩ። …… ከብዙ ድንፋታ በኋላ ሄደ። …… እቤቷ አስገብቻት ልሰናበታት ስል
“ሳመኝ?” አለችኝ። ሰምቻታለሁ። ዝም አልኳት።
“ኪሩ?”
“ወዬ?”
ጉንጯ ቀላ… … አላስደገምኳትም። እየሳምኳት አቋረጠችኝ።
“ምነው?” አልኳት
“ቆይ የሚቀጥለውንም እኔ ካልጠየቅኩህ አታደርግም?” አለችኝ።

 

8 Comments

  • ጀማል commented on May 24, 2016 Reply

    ሃይ ሜሪ ስሁሽ ጥሩ ነበር ትንሽ አጨራረሱ ግራ ያጋባል ድንገት ቁርጥ ነው ያረግሽው ተረፈ ጥሩ ነው ወድጀልሻለሁ

  • sisshi@gmail.com'
    Sisay commented on July 5, 2016 Reply

    Great observation; and you are quite a story teller, Merry. I might be wrong, but I see a glimpse of Adam Reta’s influence in your writing – which is absolutely NOT WRONG/BAD. I would love to read more of your works. Kudos – KEEP IT UP, girl! 🙂

  • Anonymous commented on July 18, 2016 Reply

    ዋው! በጣም ምርጥ !

  • Senay.tesfay31@gmail.com'
    Senay commented on April 2, 2017 Reply

    ተባረኪ ምን ልል ፈልጌ ነው ልብ ወለድሽ ውስጤ ነው

  • Senay.tesfay31@gmail.com'
    Senay commented on April 8, 2017 Reply

    በጣም ኣሪፍ ብቻ ኣይገልጸውም ውብ ኣይባልም እንጂ ማራኪማ ቢባል እጹብ ድንቅ ሊሆን ይችል ነበር ይሄን የመሰለ ጽሁፍ ጽፈሽ ስላስነበብሽን እናመሰግናለን
    “ቆይ የሚቀጥለውንም እኔ ካልነገርኩሽ
    አትጽፊም?”

  • ክንፈ አሰፋ commented on August 14, 2018 Reply

    ሜሪዬ በጣም ደስ ይላል በዚሁ ቀጥይ

  • value commented on September 7, 2018 Reply

    ጡሩ ነዉ

  • value commented on August 14, 2019 Reply

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...