Tidarfelagi.com

አለመታደል ነው (ክፍል አራት)

እኔም አልገባኝም። …… ስምሪት ለምን እናቴን አስታወሰችኝ? …… ‘ስምረት ሞተች‘ የሚለው የአርሴማ ጥሪ የፈጠረብኝ ድንጋጤ እንዴት ብሽቅ ለሆነው የአሁኑ ስሜቴ ጎታች ምክኒያት ሆነ? በውል ያለየሁት ለስምሪት የተሰማኝ ስሜት በምን ስሌት ወደልጅነት ትዝታዬ አሸመጠጠኝ? አላውቅም…… ምናልባት እስከማስታውሰው ለሰው ግድ የሰጠኝ በዚህ ክስተት ስለሆነ? ምናልባት ሰው መሆን ለሰው ማሰብን ያካትት ይሆን? ምናልባት ሰው ሆኜ ይሆን? ምናልባት ሰው በሆንኩ ቅፅበት እንደሰው ግድ ሳይሰጡኝ ያለፍኳቸውን ክስተቶች ማሰላሰል መጀመሬ ይሆን? አላውቅም…… ብቻ ‘ምንም ሽራፊ ስሜት አይሰጠኝም‘ ያልኳቸው ስንጣቂ የኑሮ ሰበዞቼን ሳይቀር ሳልፈልግ እያሰብኳቸው ነው። ……………

“እያስጨነቅኩህ ነው?” አለችኝ ስምሪት ደጋግማ የማልወዳትን እናቴን እና የተለየ ስሜት የፈጠረችብኝን ሴት ምን እንዳመሳሰላቸው ስትጠይቀኝ ቆይታ

“እናቴን እንደማልወዳት እርግጠኛ እየሆንኩ አይደለም።” መለስኩላት… … ፀጥ አለችኝ። ……… አይኖቿን አጥብባ ስታየኝ ቆየችና። ……

“ለምን አታረጋግጥም?” አለችኝ

“ምኑን?”

“ለእናትህ የሚሰማህን ስሜት?”

“እንዴት? በምን?”

“ፈልጋቸዋ!! ፈልገህ አግኛቸው።”

“የት ብዬ? ትሙት? ትኑር? እንኳን ማወቅ ይከብዳል። 11 ዓመት ብዙ ነው።” ይሄን ለሷ ስመልስላት ራሴን ሰማሁት…… ጥያቄዬ ልፈልጋት? ወይስ አልፈልጋት? የሚለውን እርከን አልፏል። …… ‘አልፈልጋትም‘ የሚለውን ጭራሽ አለማሰቤ አስገረመኝ። እሷም ይህ የገባት መሰለኝ… … ፈጠን ብላ

“ራስህን ዝግጁ ካደረግክ ፍንጭ የምናጣ አይመስለኝም።” አለችኝ ዝግጁነቴን ለማረጋገጥ ነው መሰል ከአፌ የሚወጣውን ቃል አፏን ከፍታ እየጠበቀች። ፀጥ አልኩ። ፀጥ አለችኝ። …… እያየኋት እንደሆነ ሲገባት ታቀረቅራለች……… እያየችኝ እንደሆነ ሳውቅ አይኖቼን በሌላ አቅጣጫ አርቄ እልካቸዋለሁ።

“ስምሪት?”

“አቤት?”

“እስኪ አንድ ጥያቄ ልጠይቅሽ?” ራሷን በመነቅነቅ እንድቀጥል ተስማማችልኝ።

“ለምንድነው ከሌላ ሰው በተለየ የምትቀርቢኝ? የምትሰሚኝ?የምታወሪኝ?”
የጠበቀችው ሌላ ጥያቄ እንደሆነ ሁሉ ፊቷ ረገበ………

“ከአይምሮ ይልቅ ልብ ይማርከኛል።” መልሷ እርግጠኛነት ነበረው

“ማለት?”

“ከእውቀት ይልቅ ለቅንነት ዋጋ እሰጣለሁ ማለት ነዋ!! ቅንነት የሌለበት እውቀት በዜሮ ይባዛብኛል። ቅንነት የሞላበት አለማወቅ እንኳን ይገዛኛል። ልብህ ቅን ነው።” ብላኝ ከኔ መልስ እንደማትጠብቅ ተደላደለች… …

እሷ በገለፀችኝ ልክ ልበ—ቅን መሆኔን እጠራጠራለሁ። …… ቅንነት ይመነዘራል። እኔ ስለራሴ እስከማውቀው ከራሴ ውጪ ለማንም ግድ ኖሮኝ ለሰዎች ቀና ለማድረግም ሆነ ቀና ለማሰብ ተጨንቄ አላውቅም። …… ማንም ጉዳዬ አይደለም። የማንም ጉዳዩ እሆናለሁ ብዬም አስቤ አላውቅም። ……… እሷ እንደዚህ ናት። ስለእኔ ስታወራ ባለቤቱ እርግጠኛ ከሆንኩት በላይ እርግጠኛ ናት… … ምናልባት እኔ ራሴን ከማዳምጠው በላይ እሷ ስለምታዳምጠኝ ይሆን?

ሁሌም የምትጠቁመኝ ኪሩቤል መድረስ የሚችልበትን ጫፍ እንጂ ሰወች ወይ እሷ ‘መዳረሻ‘ ብለው የሰቀሉትን ጫፍ አይደለም። ……

“ስምሪት?” ባልጠራትም እየሰማችኝ እንደሆነ አውቃለሁ። ከእስከዛሬው ሁሉ በተለየ እንድትሰማኝ ፈለግኩ።

“አቤት?”

“ከዛን ቀን በኋላ አንቺን እንደአለቃዬ ወይም እንደጓደኛዬ ማሰብ እየቻልኩ አይደለም።” አልኳት። ከአፌ እስኪወጣ እየጠበቀችው ያለ ንግግር እንደሆነ ሁሉ መገረምም መደንገጥም ሳይታይባት

” አንድ እርምጃ ጠልቀህ ያወቅከኝ ስለመሰለህ ነው?” መልስ የምትፈልግም አትመስልም

“ማለት?” አልኳት ያለችው ሳይገባኝ ቀርቶ ሳይሆን የማስረዳት አቅም ከድቶኝ

“ኪሩ ልብሳቸውን ስትገፍ ያወቅካቸው እንደሚመስሉህ ሴቶች እርቃኔን ስላየኸኝ ገበናዬን የገለብክ አይምሰልህ።” የምታወራበት ቅላፄ የማላውቀውና ምሬት የተቀላቀለበት ነው።

ምን እንደምላት እና ለሷና ለማውቃቸው ሴቶች የሚሰማኝን የአንድ ጤፍ ፍሬና የተራራ ያህል የገዘፈ የስሜት ልዩነት ማስረዳት ባለመቻሌ ተናደድኩ።

“እንደዛ አይደለም የተሰማኝ። ውስጤ የቀረውን የገላሽን ምስል ሳስበው አብሬሽ መተኛት አይደለም የሚሰማኝ። ተሰምቶኝ በማያውቅ መልኩ ከወለሉ ላይ አንስቼሽ አልጋ ላይ ያደረስኩሽ ቅፅበት የእድሜ ዘመኔን ያህል ረዥም እንዲሆን ነው የሚሰማኝ። ክንዴ ላይ እንዳቀፍኩሽ የተከደኑ አይኖችሽን በስስት እያየሁ ዘመናቴ ቢያልቁ ነው የተሰማኝ። …… ” ይግባት አይግባት እንጃ… … ከዚህ በላይ ማስረዳት ግን አቃተኝ። …… ደቂቃዎችን ትንፋሽ ያጠረኝ እስኪመስለኝ ፀጥ አለች።

ሲገባኝ ሁሉም ሰው የሆነች “የለውጥ ኩርባ” አለችው። አስተሳሰቡ ወይ ስሜቱ ወይ ድርጊቱ… … የሚቀየርባት። ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚታጠፍበት……ወይም ከወደቀበት መቀመቅ የሚስፈነጠርበት……… ወይም ለዛለው ጉልበቱ አቅም የሚያገኝበት… … ያቺ የለውጥ ኩርባ አንድ የሆነች ኢምንት ክስተት ልትሆን ትችላለች…… ወይም ዓረፍተ ነገር… … ወይም… …
…የኔ የለውጥ ኩርባ ያቺ ቀን ነበረች። ……

“ልክ አይሆንም። እኔና አንተ ከዚህ ቀደም ከነበረን የዘለለ ግንኙነት ሊኖረን አይችልም።” አለችኝ

 

አለመታደል ነው (ክፍል አምስት)

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...