“ከኔና ከሱስ ምረጥ” ስትለኝ ቀኑ ቅዳሜ ነበር። …… ስልኬን ጆሮዬ ላይ እንደለጠፍኩ ዙሪያዬን ቃኘሁት። …… በሱሶቼ ተከብቢያለሁ።(ያሟላሁ ሱሰኛ ነኝ።)
“መቼ?” አልኳት
“አሁኑኑ!”
“ዛሬ ከሆነ ሱሴን ነገ ከሆነ ግን አንቺን!” መለስኩላት። ዘጋችው። …… መልሳ እንደማትደውል አውቃለሁ። ……
ጥፋተኛው ማነው? ራሷን ከቅጠል ጋር፣ ከጭስ ጋር በሚዛን አስቀምጣልኝ… … ምን ልበላት? ‘ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው‘ ዋጋዋን ከሷ በላይ እንዴት ላውቀው እችላለሁ?
ስንተኛዬ እንደሆነች የማላስታውሳት ሴቴ ናት። …… ሴቶቼ እድሌ ሆኖ ነው መሰል ሱሴን ይጠምዱታል። …… እኔ ደሞ ፀባዬ ሆኖ ሱሰኛ ሴት ቅልሽልሽቴን ታመጣዋለች። “በማን ላይ ተቀምጠህ ማንን ታማለህ?” ትለኛለች አለቃዬ(ስምረት) እኔ ስምሪት ነው የምላት…… አትናደድብኝም። …… ከጠዋት ይልቅ ለለሊት የቀረበ ሰዓት ላይ ቢሮ ትገባና ተሰይማ ትጠብቀናለች። ………… ከጠዋት ይልቅ ለከሰዓት በቀረበ ሰዓት ቢሮ እከሰታለሁ። ……
“እስቲ አንተን የማላባርርበት አንድ ጥሩ ምክኒያት ብቻ ንገረኝ” ትለኛለች
“ያንቺ ደግነት!” እላታለሁ
“ወደ ስራ!” ብላ የመጨረሻውን ተሰማሪ ታሰማራኛለች…… ስምሪት
ሴት ወዳለሁ። ‘ማን ይጠላል?‘ አልክ የአዳም ዘር? ሃሃሃሃ I mean it! እኔ ወዳቸዋለሁ… ሳስበው ፈጣሪ በምድር ላይ እንደሴት ውብና አማላይ አድርጎ የፈጠረው ነገር መኖሩን እንጃ!! ገና ሳስባቸው ደም ስሬን የሚወጥሩ ፍጥረቶች ናቸው። …… ኤጭ አሁን ራሱ ደሜ ሞቀ……
እነሱ ከሚወዱኝ የበዛ ይናደዱብኛል!! “ሴት ሳይሆን ስሪያ ነው የምትወደው” ይሉኛል። … “ስሪያው ታዲያ ከወንድ ጋር ነው እንዴ?” እላቸዋለሁ።
በእርግጥ ከሴት ጋር ሱስ ስለማቆም ከማውራት… … እንትን የሚያቆም ወሬ ማውራት እመርጣለሁ። እንደውም ሳስበው መቃብሬ ላይ ራሱ አልቤርጎ ሚሰራ ነው የሚመስለኝ።
“አብረኻት ሆነህ የተለየ ደስ የሚል ስሜት የፈጠረችብህ ሴት የለችም?” ትለኛለች ስምሪት ስለሴቶቼ ስናወራ
“አብሬያት ሆኜ የሚያስጠላ ስሜት የፈጠረችብኝን ሴት አላስታውስም።” እመልስላታለሁ።
እውነቴን ነው። …… በእርግጥ ረዥሙ ከሴት ጋር ቆይታዬ ሁለት ወር ነው። …… አንድም ቀን ያወቅኳትን ሴት ሁለት ወር ከማውቃት እኩል እወዳታለሁ። ……
ስምሪት ደወለች።
“ወዬ? …… ”
መልስ የለም
“ወዬ ስምሪት?” … ትንፋሽ ብቻ
ዘጋሁት። …… መልሼ ደወልኩ። ይነሳል። መልስ የለም።
በነገራችሁ ላይ ስምሪት በኔ ውስጥ ፆታ አልባ ናት!! የሆነ ከማውቃቸው ሴቶች የሚለያት እንደሴት እንዳላስባት የሚያደርገኝ ነገር አላት። …… ምናልባት የምትለብሰው የፖሊስ ልብስ…… ምናልባት ሁለት ሰዓት ለፍልፌባት በ2 ደቂቃ የምትመልስልኝ ልብ የሚያሳርፍ መልሷ…… ምናልባት አለቃዬ መሆኗ…… ምናልባት የምትመርጣቸው ሮክ ሙዚቃዎችና የስለላ ፊልሞች ከሴቶች ምርጫ መለየቱ…… ምናልባት… …ምናልባት… … … በብዙ ምናልባቶች ፆታ አልባ ናት!!
…… ወንድ ጓደኛ ቢኖረኝ ላወራው የምችለውን ቅሽምናዬን ሳወራት በከፊል ፈገግታ ከመስማት ውጪ አትፈርድብኝም። …… ስለማህበረሰብ ወግና ስርዓት አትሰብከኝም። …… የሚሰለቸኝ ስብከት መሆኑን ታውቃለች። …… ይሄ ማህበረሰብ ምኔ ነው? ምን የሰጠኝን ነው ሊቀበለኝ እጁን የሚዘረጋው? የእጁ አሻራ እስኪጠፋ ዶቭ ሳሙና እንዳላማለለ ከተለያየ ሴት ጋር መታየቴ ሀጢያት መሆኑን ሊነግረኝ ይዳዳዋል።…… በዚህ ዘብራቃ ማህበረሰብ ውስጥ ሀጢያትህን ሀጢያት የሚያደርገው ድርጊቱ ሳይሆን ያደረግከው ድርጊት በግልፅ መሆኑ ነው።…… ተደብቀህ ካደረግከው ፅድቅህ ይተረካል።
3 ዓመት አብረን ሰርተናል። እሷ መርማሪ ፖሊስ መሆን ህልሟ ነው። እኔስ? ቅዠቴ…… ይሄ ግራ የገባው የጦዘ የኑሮ ስሌት እና አስተዳደር አላሚና ቃዢን በአንድ ያስተዳድራል።… …
ለሶስተኛ ጊዜ መልሼ ደወልኩ። በተኮላተፈ አንደበት እና በተሰባበሩ ፊደላት የመለሰችልኝ ህፃን ናት።…… ቀጣጥዬ የተረዳሁት
“ስምረት ሞተች” የሚለውን ንግግር ነው። ዘልዬ ብድግ አልኩ። ይሄኛውን ራሴን አላውቀውም። በምንም ክስተት እንዲህ እደነግጣለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም። ……
ከርቀት የማውቀው የስምሪት ቤት ለመድረስ ላዳ ታክሲ ያዝኩ…… ሆኜ እንደማላውቀው ቁጭ ብድግ ሰራሁ ታክሲ ውስጥ… … ሮጬ ቤቱን ሳንኳኳ የከፈተችልኝ ቅድም በስልክ ያዋራችኝ ህፃን ናት…… የኦቲዝም ተጠቂ መሆኗን ለመገንዘብ ከአንድ እይታ በላይ አይጠይቅም። …… ዘልዬ እየገባሁ ምን መጠየቅ እንዳለብኝ ግራ ስጋባ በእጇ ምልክት የሻወር ቤቱን አሳየችኝ። ክፍት ነው። …… ስምሪት ወለሉ ላይ እርቃኗን ተዘርራለች።