Tidarfelagi.com

“ኑ ሀገር እንስፋ!”

ክፍፍል መችነበር፥
በአምላክ አሰራር ፥በቅድመ አፈጣጠር
ሰው ሰው ብቻ ነበር ፥ዘሩ ሳይቆጠር።

ሰውነት ተንዶ፥
እንዲህ እንደዛሬ ፥ ሳይኖር መበታተን
የመቆጣጠር ዛር ፥ መቃብር ሳይከተን
አንድ እናት ነበረን ፥
ቀሚሷ እንደኪዳን ፥ ሁላችን ምንለብሰው
ዛሬ ተለያይተን፥
ክብሯን እንደ እቃቃ ፥ ዳቦ ሳንቆርሰው።

ሻህላ ወረሰን፥
ውስጣችን ተበላ ፥
ፍቅር የጠመቅንበት ፥ ተሰበረ ጋኑ
ለናታችን ቀሚስ፥
ጥጥ የነደፍንበት ፥ ተጣለ ደጋኑ።

ሰው ተተነተነ፥ ሰው ተቆራረሰ
ዘር ስንቆጣጠር ፥ ሀገር ፈራረሰ።
ፍቅር እንደቁና ፥ አርጅቶ ተጣለ
ጥላቻ ድንኳኑን ፥ በላያችን ጣለ።

የናታችን ቀሚስ፥
ባለሶስ ቀለሙ ፥
በሰማይ ዳስ ሲጥል ፥ ለምድር የሚያጠላው
ትውልድ ሲናጠቅ፥
በ”የኔ ነው !” “የኔ ” ፥ የጥል እሳት በላው።

ይኼው እና ዛሬ…!
ያች ሙሉ እመቤት
ያቺ ሸዋ ግርድሽ፥
በክፍፍል ክናድ ፥
ከፍቅር ሰገነት ፥ከርማ ስትገፋ
እርቃኗን ቆማለች፥
የቃልኪዳን ልብሷን ፥ ቀሚሷን ተገፋ።

ያ ብልህ አያቴ
ትውልድ በሽሚያ ፥ የቀደደው ልብሷን
ሊሰፋ ይጥራል ፥ የክብር ቀሚሷን።

ስሩ ተቀምጬ፥
በልጅ አእምሮዬ ፥ ጥያቄ ይዘንባል
በቦዘዙ ዐይኖቹ፥
ክሩ ከመርፌው ጫፍ ፥ ላይገባ ይዛባል።

(እንዲህ ጠይቃለሁ?
ምን ነካህ አባባ ፥
ይኼ ቅዳች ቀሚስ ፥ ዳግም ተጠግኖ
እንደቀድሞው አይጥል ፥ ውበቱ ጀግኖ?”
ለምን ትለፋለህ ፥? ብዬ ስጠይቀው
አያቴ እንዲህ አለኝ፥ እንባው እያነቀው።
ልጄ ሆይ አድምጪ፥
መስፋቴ ቅኔ ነው ፥ እንደወርቅ እንደሰም
አላዳውር አይል ፥ ስንጥቅ ኖሮት ቀሰም።
አስተውይ ልጄ፥
መርፌ ማለት ፍቅር ፥ ሰርስሮ ሚገባ
ክር ማለት ሰላም፥
ቀዳዳን ጠግኖ ፥ ዳግም ሚገነባ።

ይለኛል አያቴ፥
ፍቅር ባለው መርፌ፥ ነፍሱ እየተወጋች
ክር ላለው ሰላም፥ ደጀን እየተጋች
የእናቴን ቀሚስ
ሲጠግን ስላየሁ…፥

እንሆኝ አንድ ቃል…!
የናት ክበር ወድቆ፥
የለምና ለክብር ፥ የሚሰነቅ ተስፋ
ኑ እርቃን እንሸፍን፥ ኑ ሀገር እንስፋ።

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...