Tidarfelagi.com

ኑሮ እና ብልሃቱ

የዘጠኝ አመቷን የጓደኛዬን ልጅ የአማርኛ ምሳሌያዊ ንግግር ላስተምር እየታተርኩ ነው።

ሶስተኛው ላይ ነን።

መፅሃፉ ላይ በተርታ ካሉት ውስጥ ለሷ የሚመጥነውን መርጬ አንብቢ አልኳት።

‹‹ሁለት ጉድጓድ ያላት አይጥ አትሞትም›› ጮክ ብላ አነበበች።

‹‹ጎበዝ! ምን ማለት ይመስልሻል?››
‹‹እ….እ….›› አለች እያንጋጠጠች።

‹‹ቀስ ብለሽ አስቢ.›› አልኳት ራሷን እየደባበስኩ።

ደቂቃ ለማይሆን ጊዜ ‹‹እ…እ ››እያለች ስታስብ ቆየችና፤

‹‹ልክ እንደ ቶም እና …እንደ ቶም እና ጄሪ ነው አይደል?››ስትለኝ ሳቅኩ።

‹‹እንደ ቶም እና ጄሪ አይደለም?›› አለችኝ መልሳ።

‹‹ነው…ልክ ነሽ…ግን… እስቲ አስረጂኝ…›› አልኳት ‹‹ምን ልትለኝ ይሆን?›› በሚል ጉጉት ተወጥሬ።

‹‹እ…አሁን ጄሪ ቶም ሲያባርራት ከጉድጓዷ ቶሎ ትወጣና…ታመልጠውና…›› አለችና ድንገት ዝም ስትል ‹‹ያለአቅሟ አስጨነቅኳት እንዴ›› ብዬ ራሴን እንደ መውቀስ አድርጎኝ ‹‹በቃ ተይው ሌላ እንሞክር…ይሄን እይው የኔ ማር…እይው….ስላት፤
‹‹እምቢየው..!የጉድጓዱን መልስ ንገሪኝ›› አለችኝ።

በራሴ ላይ ገመድ ማሳጠሬ እየተሰማኝ፣ እንዴት ብዬ እንደማስረዳት አስቤ ቀላል ቃላት ልመርጥ ስሞክር ቆየሁና በጀመረችው የቶም እና ጄሪ ምሳሌ ብሄድ ይቀልላል ብዬ እንዲህ አልኳት።

‹‹ይሄውልሽ የኔ ማር፤ አሁን ጄሪ ቶም መጥቶ ሊመታት ሲል ከአንዱ ጉድጓድ አምልጣ ሌላ ጉድጓድ ሄዳ ትደበቅበት የለ?››

‹‹አዎ…›› አለች።

ትኩረቷ ያስገርማል።

‹‹ጄሪ ሁለት ጉድጓድ ባይኖራት ግን የት ሄዳ ታመልጥ ነበር..?.ቶም አንዱ ጉድጓዷ ውስጥ አግኝቶ ይመታት ነበር አይደል…?.››

‹‹አዎ….››

‹‹ስለዚህ ሁለት ጉድጓድ ያላት አይጥ አትሞትም የተባለው፤ ልክ እንደ ጄሪ አይነት አይጥ እንደ ቶም አይነት ድመት አንዱ ጉድጓድ ጋር ቢመጣባት ወደ ሌላኛው ጉድጓድ ሄዳ ታመልጣለች ለማለት ነው…ገባሽ…?.›› አልኳት ‹‹ይሄ ውስብስብ ነገር በቀላሉ ይወርድላት ይሆን?›› ብዬ እየሰጋሁ።

ለአፍታ መልስ ሳትሰጠኝ ትኩር ብላ ስታየኝ ስትቆይ መልሼ፤ ‹‹አልገባሽም እንዴ?›› አልኳት

‹‹አይ…ገብቶኛል…›› አለችኝ የሌባ ጣቷን ጥፍር እየበላች።
‹‹ታዲያ ምነው?››

‹‹ሒዊ…››
‹‹ወዬ የኔ ማር?››
‹‹አይጧ ሁለት ጉድጓድ ካላትማ ሁለት ድመት ነው የሚኖረው››

ምንም ልላት አልቻልኩም። የሰማሁትን ባለማመን ድንዝዤ ቁጭ አልኩ።

አስር አመት ሳይሞላት ኑሮ እና ብልሃቱ እንዲህ የተገለጸላት ይህች ልጅ፤ ይህንን አለም በአጭር ታጥቃ ልትጋፈጠው መሆኑን ሳውቅ ግን ፈገግ አልኩኝ።

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...