Tidarfelagi.com

‹‹ነገ ዛሬ ይሆን››

እንግዲህ ጅማሬው ከሆነ ከአንጀታችሁ
‹‹እናዳምጣለን….ንገሩን›› ካላችሁ…

የይስሙላ፣ የእድሜ ማራዘሚያ፣ የጥገና እና ተንፏቃቂ ለውጥ አንፈልግም።
ጉልቻው እንዲቀያየር፣
ሽንቁር የበዛበት ግድግዳ ቀለም ፣ አሳማው ሊፕሰቲክ እንዲቀባ አንሻም።
ባረጀ እና ያፈጀው ‹‹ተሃድሶ›› ሀረግ ዳግም መደለል፣ ዳግም መታለል አንፈልግም።

የ‹‹ተጨፈኑ ላሞኛችሁ›› ፖለቲካ አንገሽግሾናል።
የዘመናት‹‹እድሳት ላይ ነን›› ፕሮፓጋንዳ በቅቶናል።

ከእንግዲህ እምቢ አንሞኝም።
በገዛ መንግስታችን የጎሪጥ አንታይም።
ሀገራችንን በወደድን፣ ለሃገራችን ዋስ በሆንን በእስር-በሰው ሀገር- ፍዳ- አሳራችንን አናይም።

ጥቂቶች በፈንጠዝያ- ብዙዎች በሰቆቃ የሚኖሩባትን ሀገር እሺ ብለን አንቀበልም።
ህዝብ መንግስት እንዳሻው የሚነዳው የበረት ከብት አይደለምና ‹‹ወግዱ!›› እየተባልን መቀጥቀጥን አንታገስም።

እንግዲህ ነገሩ ከሆነ ከአንጀታችሁ …
‹‹እናዳምጣለን…ንገሩን›› ካላችሁ…

ከራሱ ህዝብ ጋር እልህ የሚጋባ መንግስትን አንሸከምም።
ከእንግዲህ መሪን እንጂ ገዢን ‹‹በጄ›› ብለን አንታዘዝም።

የምንወዳት ሀገራችን እና ህዝቧ እጣ ፈንታ ጭብጥ በማይሞሉ ሰዎቸ እንዲወስን አንፈቅድም።
ነውሩን ገልጠን ስንነግረው በመለወጥ ፈንታ በእፍርታምነት በሚቀጥል መንግስት አንወከልም።
በጃጀ አእምሮ፣ ወደ ፊት ሳይሆን ወደ ኋላ በሚመለከቱ፣ አርጩሜያቸው እንጂ ጆሯቸው ለህዝብ ቅርብ ባልሆነ ሰዎች አንተዳደርም።

እንግዲህ ነገሩ ከሆነ ከአንጀታችሁ …
‹‹እናዳምጣለን ንገሩን›› ካላችሁ…

ዋለልኝ መኮንን የጃንሆይን መንግስት እንዳለው እኛም እንዲህ እንለችኋለን…

‹‹የፖለቲካና ኢኮኖሚ ነፃነት መጠየቅ ከሱቅ ዱቤ እንደመጠየቅ አይደለም። ስለሆነም፣ ‹ዱቤ ዛሬ የለም- ነገ›› አጥጋቢ መልስ አይሆንም።ይሄ ነገ ዛሬ መሆን አለበት››

የይስሙላ፣ የእድሜ ማራዘሚያ፣ የጥገና እና ተንፏቃቂ ለውጥ አንፈልግም።

ኢትዮጵያችን ከወደቀችበት እንድትነሳ እንጂ…
ጉልቻው እንዲቀያየር፣
ሽንቁር የበዛበት ግድግዳ ቀለም ፣ አሳማው ሊፕሰቲክ እንዲቀባ አንሻም።፡
ባረጀ እና ያፈጀው ‹‹ተሃድሶ›› ሀረግ ዳግም መደለል፣ ዳግም መታለልን ከቶ አንፈልግም።

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...