Tidarfelagi.com

ትዝታ ዘ-አባዱላ

የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በ1993 ለሁለት በተከፈለበት ወቅት ገዥዎቻችን ያልጠበቁት አብዮት በኦህዴድ ውስጥም ፈንድቶ ነበር። በክስተቱ የደነገጠው አቶ መለስ ዜናዊ የኦህዴድ ገዲም ካድሬዎችን ተጠቅሞ አብዮቱን መቆጣጠር ተሳነው። ከሚተማመንባቸው የኦህዴድ ጓዶቹ መካከል ከፊሉ እየወላወለ፣ ከፊሉ እየከዳ አስቸገረው። በነገሩ በጣም ተጨንቆ ሲጠበብ አንድ ታማኝ ሰው ትዝ አለው።

ያ ሰው አባዱላ ገመዳ (ምናሴ ወልደዮሐንስ) ይባላል። አባዱላ ህወሓት በተጨነቀበት ጊዜ ሁሉ ነፍስ አድን አገልግሎት እየሰጠ የመሪዎቹን አንጀት ያርስ ነበር። ለምሳሌ እነ ኢብራሂም መልካ እና አስፋው ቱኔን የመሳሰሉ የኦህዴድ መሥራቾች በ1985-1986 በድርጅቱ ነፃነት ላይ ያላቸውን ቅሬታና ጥያቄ እያነሱ ሲወያዩ ከነርሱ ጋር ሆኖ በስሜት ያዋራቸው ነበር። እነርሱም በአቋሙ ተደስተው ኦህዴድን ከህወሓት ተጽእኖ ነፃ ለማድረግ አብረው ለመስራት ወሰኑ።

እነ ኢብራሂም ጥያቄአቸውን በኢህአዴግ የፖሊት ቢሮ ስብሰባ ላይ ሲያቀርቡ ግን ህወሓቶች በአባዱላ ገመዳ በኩል የአስራ አምስት ሳንቲም ሚስማር ቀረቀሩላቸው። ሚስጢረኛቸው መስሎ ሲያዋራቸው የነበረው አባዱላ ገመዳ 180 ዲግሪ ተገልብጦ “የኦነግን ጠባብ ዓላማ የሚደግፉ የጥፋት ሀይሎች ናቸው” የሚል ተውኔት ተወነባቸው። ከደርግ ውድቀት በኋላ ከሚጠቀሱት የአባዱላ ጀብዱዎች መካከል የመጀመሪያው የተመዘገበው ያኔ ነው።

በ1990/1991 ሁለተኛው የጭንቀት ጊዜ መጣ። ሻዕቢያ ባድመንና ሽራሮን ወረረ ተባለ። አዲሱ የኢፌዴሪ መከላከያ ሀይል ወራሪውን ከተያዙት ቦታዎች መነቅነቅ ተሳነው። በባድመ ግንባር የተደረገው ውጊያ በድል ቢጠናቀቅም በዚህ ግንባርና በጾረና ግንባር ብቻ ህወሓቶች ለ17 ዓመታት የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ ካጡት ሰው ጋር የሚስተካከል ሰራዊት አለቀ። ያለአቅማቸውና ያለአንዳች ወታደራዊ ሳይንስ “ጄኔራል”፣ “ኮሎኔል”፣ “ሻለቃ” እየተባሉ የተሾሙት የቀድሞ ነፃ አውጪዎች ኮንቬንሽናል አርሚ መርተው ማዋጋት የማይችሉ ሆነው ተገኙ።

ስለዚህ “የጨፍጫፊው ደርግ ጦር” ተብለው የተበተኑት የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰራዊት አባላት ሀገር በማዳን ተግባር እንዲሳተፉ ጥሪ ተደረገላቸው። በፊት ይከፈላቸው ከነበረው በእጥፍ የሚበልጥ ደመወዝ ተቆረጠላቸው። ለዓመታት ትኩረት የተነፈገው የጡረታ መብታቸውም ተከበረላቸው።

የቀድሞው ጦር አባላትም በዘመቻው ተሳትፈው ሰራዊቱን እየመሩ ሻዕቢያን በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ከሁሉም ግንባሮች አባረሩ። በዚህም ውትድርና ራሱን የቻለ ሳይንስ መሆኑ ተረጋገጠ። የነ ጄኔራል ተስፋዬ ሀብተማሪያምንና ጄኔራል በሃይሉ ክንዴን የማዋጋት ችሎታ የሚመለከቱ የተለያዩ ዜናዎችና ሪፖርታዦችም በፕሬስ ውጤቶች ታትመው ወጡ። ያኔ ታዲያ ኢህአዴጎች ደነገጡ። የነርሱ ሠራዊት አቅመ-ቢስ መሆኑ መረጋገጡ በጣም አሳፈራቸው። ስለዚህ አንድ ሰው ሰራዊቱን ወክሎ በጋዜጣዊ መግለጫ ስም ማስተባበያ እንዲሰጥ ተመደበ። ለዚህ የተመረጠው ደግሞ ሜጄር ጄኔራል አባዱላ ገመዳ ነበር። እርሱም በሰኔ ወር 1992 ወደ ቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብሎ እንዲህ አለ።

“ሀገርን ከወራሪ ለማስለቀቅ በተደረገው ርብርብ ውስጥ የደርግ ወታደሮች አስተዋጽኦ ኢሚንት ነው”

ከዚህ ሁሉ በኋላ ነበር የ1993ቱ የኦህዴድ አብዮት የመጣው። አባዱላ ገመዳ በዚያ ወቅት በሜጄር ጄኔራል ማዕረግ የምድር ጦር አዛዥ ነበር። እናም ለአቶ መለስ ዜናዊ “ኦህዴድ ችግር ላይ ነው፣ ስለዚህ ከሰራዊቱ ተሰናብቼ ድርጅቴን ማዳን እፈልጋለሁ” የሚል ደብዳቤ ጻፈ። አቶ መለስም ሰውዬው ጥያቄውን ለብዙ ጊዜ ያቀረበ በሚመስል መልኩ “እስከ ዛሬ ድረስ ለጥያቄዎ መልስ ሳልሰጥ የቆየሁት በሠራዊቱ ውስጥ ሆነው የሚሰጡት አገልግሎት ስለሚበልጥብን ነው፤ ሆኖም ሐሳብዎን የማይለውጡ ከሆነ ህገ-መንግስታዊ መብትዎትን መግፋት ስለማይቻል ከዛሬ ጀምሮ በታላቅ ክብር ከሠራዊቱ የተሰናበቱ መሆንዎን አስታውቃለሁ” የሚል የመልስ ደብዳቤ ጻፉለት (ሁለቱም ደብዳቤዎች በነፃው ፕሬስ ላይ ወጥተው ነበር)።

በዚሁ መሠረት ጄኔራል አባዱላ ከሳምንት በኋላ “ታጋይ አባዱላ” ሆኖ ብቅ አለ። ከሳምንት በኋላ በኦህዴድ ድርጅታዊ መግለጫዎች ላይ መገኘት ጀመረ። ከሳምንት በኋላ ማንም ባልገመተው መንገድ የኦህዴድ ሊቀመንበር ሆኖ ተመረጠ። ብዙዎች በጉጉት ሲከታተሉት የነበረውን የኦህዴድ አብዮትንም ሙሉ በሙሉ አከሸፈው።

የፌስቡክ ጓደኞቼ “አባዱላ በዛሬው ዕለት በፓርላማው ድራማ ሰርቷል” እያሉ ነው። በግሌ ማስረጃ የለኝም። ነገር ግን የጀርባ ታሪኩን የምናውቅ ታዛቢዎች ሰውዬው አደገኛ ድራማዎችን ሊሰራ እንደሚችል እናምናለን። ባለፈው ጊዜ “የስልጣን መልቀቂያ ጥያቄ አቅርቤአለሁ” ሲል እምነት ያልጣልንበትና በችኮላ የፕሮፋይል ፒክቸራችንን በርሱ ፎቶግራፍ ያልቀየርንበት ዋነኛ ምክንያትም ይህ ነው። ለማንኛውም ጠርጥሩ ለማለት ያህል ነው።

ጭማሪ
አባዱላ ገመዳ “የኦሮሞ ህዝብ ትግል ከየት ወደየት” የሚል መጽሐፍ ጽፎ ነበር። ያ መጽሐፍ ብዙዎችን ያናቆረ፣ ብዙዎችን ያናከሰና በውሸት ዝብዘባ የተሞላ ነው። ዋናው ጥያቄ “መጽሐፉን ማን ጻፈው?” የሚለው ነው። በወሬ ወሬ የሚባለውን ሰምተናል። እስቲ እናንተም የሰማችሁትን ንገሩን።

Afendi Muteki is a researcher and author of the ethnography and history of the peoples of East Ethiopia

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...