Tidarfelagi.com

ትንሣኤ

አምላክ፦
የአዳም ዘር ይድን ዘንድ፣ ግድ ቢለው ፍቅሩ፤
ሰው ሆኖ ወረደ፣ ከሰማያት ክብሩ።

->
አይሁድ፦
የእርሱ ፍቅር ሳይሆን፣ ክብራቸው ገዷቸው፤
እውነቱ… ተግሣጹ… ስላሳበዳቸው፤
ለክፉ ሥራቸው፣ ነፃነት ፈልገው፤
እጅና እግሮቹን፣ በችንካር ሰንገው፤

“በክፉ ዓለማቸው፣ ደጉን እንዳያዩት፤
ዝቅ ብሎ ቢመጣ፣ ከፍ አ’ርገው ሰቀሉት”።

->
እኛ፦
ከሰማይ መውረዱ፤
ከሰው መወለዱ፤
መከራ ስቅለቱ፣
ሕማምና ሞቱ፣
ቢገባን ባይገባን፣ የበዓሉ ምሥጢራት፤
ትንሣኤ ሸጋ ነው፣ ደግሶ ለመብላት።

->
እንዲያውም…
በጾም ሳያደክም፣ በሕማም ሳይነካ፤
ቢሆን ደስ ይለናል…
ሁልጊዜ ትንሣኤ፣ ሁልጊዜ ፋሲካ።

 

->
እንደዚህ ነን በቃ!
መከራን ረስተን፣ ደስታን አድማቂ፤
ያለ ሕማማት ሞት፣ ትንሣኤን ናፋቂ።
—>
ነገር ግን…
ተፈጥሮ ምሥጢሯ፣ ይኸው ነው እውነቱ፤
ትንሣኤን ይቀድማል፣
መከራ ስቅለቱ… ሕማሙ እና ሞቱ።

መልካም የስቅለት በዓል !

->
(((የግርጌ ማስታወሻ፦
ሥዕሉ የገብረክርስቶስ ደስታ ነው። ሠዓሊና ገጣሚ ገብረክርቶስ ደስታ “ለምን ክርስቶስን እንደዚህ በቀይ ቀለም ብቻ ሣልኸው?” ተብሎ ሲጠየቅ “ምክንያቱም ክርስቶስ የሁላችንም ወገን መሆኑን ለማሳየት ነው። እንደምታውቁት ክርስቶስን ነጮች ነጭ አድርገው ይስሉትና በዘረኛ አስተሳስባቸው የእነርሱ ወገን ብቻ ለማድረግ ይጥራሉ። እኔም ጥቁር በመሆኔ ኢየሱስ ክርስቶስን ጥቁር አድርጌ ብስለው ዘረኝነት ይሆንብኛል። እርሱ በመስቀል የሞተው ዘር ቀለም ሳይለይ ለሰው ልጅ ሁሉ ነው። የዋጀንም በደሙ ነው። ሁላችንም ወገኑ የምንሆነውም በደሙ ነውና ደምን በሚመስል ቀይ ቀለም ብቻ ሣልሁት” ብሎ እንደመለሰ ተጽፎ አንብቤያለሁ። ድንቅ መረዳት ነው መቼስ!!! አይ ጥበብ እኮ በእውነተኞቹ ጥበበኞች እጅ ስትሆን… ስታምር!!!)))
===>

melakual@shegerblog.com'
ለሀገር መለኛ ሐሳቦችን እናዋጣለን!

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...