Tidarfelagi.com

ትናንት ዛሬ አደለም

ይገርማል!! ያገራችን ገበሬ የሚያርስበት በሬና ማረሻ ጥንታዊ ሰው ከአራት ሺህ አመት በፊት ይገለገልበት የነበረውን ነው። ይሁን እንጂ ቢቀናው ክላሺንኮቭ ይታጠቃል። ደሞ ገበሬውን ዘመናዊ ጠመንጃ እንጂ ዘመናዊ ማረሻ ለማስታጠቅ የሚያልም አክቲቪስት አይተን አናውቅም።

ዘመናይ የብሄር አክትቪስት ጦርነት በናፈቀ ቁጥር ያባቶቹን ጀብድ ይዘክራል። ባባቶቹና በሱ መካከል በሰፊው የሚያዛጋ የጊዜ ገደል እንደተዘረጋ አይገባውም። የድሮ ሰዎች ከማረስ ይልቅ መዋጋት ቢወዱ አይገርምም። ያኔ ጦርነት ወጭው ትንሽ : ትርፉ ብዙ ነበር። ጥቂት የተደራጀ ጭፍራ ጥቂት ፈረስና ጦር ይዞ በሺ የሚቆጠር የቀንድ ከብት መማርክ ይቻል ነበር። ዛሬ አንድ መንደር አርሶ የሚያበላ ትራክተር ባስራ አራት ሺህ ዶላር መግዛት ትችላለህ። አንድ መንደር አፈር የሚያስበላ ታንክ ለመሸመት ከፈልግህ ግን ዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር መክፈል ይጠበቅብሃል። እና በዚህ ዘመን ተዋግቼ አተርፋለሁ ብሎ ጉራውን የሚነፋ አዲስ የተመረተ ዴዴብ መሆን አለበት!!!

ድሮ በሰላምም ሆነ በጦርነት ባጭሩ መቀጨት ያባት የናትህ እዳ ነበር። በጦርነትም ሆነ በሰላም ጊዜ ከሞት ጋር ያለህ ርቀት ተቀራራቢ ነው። ይህን የሚያውቁት ቀዳማዊ ሀይለስላሴ በማይጨው ዋዜማ የክተት አዋጃቸው “ቤትህ ቁጭ ብለህ በሳልና በጉንፋን ከመሞት ጠላትን መክተህ ብትሞት ክብር ነው” ብለው ዜጋውን ጀንጅነውታል። ልክ ነው! በህዳር በሸታ ከመሞት በጦርነት መሞት ስም እና ምርኮ ሊያስገኝ ይችላል።

ዛሬ ሰላም ወጭ ቆጣቢ ነው። ሰላም ያለው ብዙ ሀብት ብዙ እድል ብዙ ተስፋና ብዙ እድሜ ይኖረዋል። ታድያ ለሰላም ሲባል ወደረኞቻችንን ብንለማመጣቸው ብናቆላምጣቸው ብንወያያቸው እንዴት ነውር ይሆናል? ዛሬ መደራደር መወያየት የሚያሳፍርበት : ውረድ እንውረድ የሚያስኮራበት ዘመን አይደለም።

ዛሬም እንደ ጥንቱ በርስት ወይም በማንንት ሰበብ የሚደረግ ጦርነት የሚጎዳው ዜጎች እንጂ ጌቶች አይደለም። ከእምባቦ ከሰገሌ እና ከባድመ ክሽፈት እንዳየነው አገሬው በጦርነት ያልፋል: አገር መሪው ግን ይተርፋል። በምባቦ ጦርነት ንጉስ ምኒልክና ንጉስ ተክለሃይማኖት ገጥመው በብዙሺህ የሚቆጠር ባላገር ያአሞራ ቀለብ ሆነ። ሁለቱ ሃያላን ግን ታርቀው ተፋቅረው ረጅም እድሜ ኖሩ። ሰገሌ ላይ የንጉስ ሚካየል ባላገርና የተፈሪ መኮንን ባላገር ተፈሳፈሰ። ደሙን ለሁለቱ መሳፍንት የክብር ሲል አፈሰሰ። ንጉስ ሚካኤልም ሆነ ተፈሪን ግን ከጦርነቱ ማጠናቀቂያ ባንድ ድንኩዋን ውስጥ ተቀምጠው ” አባቴ እንኩዋን አተረፈዎ! ልጄ እንኩዋን አተረፈህ” እየተባባሉ ተቃቀፉ። በባድመ ጦርነት ያ ሁሉ ወጣት አላማም ሆነ ኢላማም በሌለው ጦርነት ሜዳ ላይ ቀረ። የጦርነቱ ጠንሳሾች ለሙታን ተገቢውን መታሰቢያ ሳያደርጉ ላደረጉት ይቅርታ ሳይጠይቁ በህይወት ይርመሰመሳሉ ። ነገም ከዚህ የተለየ አይሆንም!!

እና እምቢ በል!!! አሻፍረኝ በል!! በቀረርቶ አትወሰድ! በመፈክር አትሸወድ!! ለሚያዋጉ እንጂ ለማይዋጉ ጦርአውርዶች : እንኩዋን ህይወትህን ትኩረትህን ለመሰጠት አትሞክር!!

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...