Tidarfelagi.com

ታጋቹ ማስታወሻ

ቀሳ ከወጣሁ ጊዜ ጀምሮ ቤቴ ውስጥ ያገኘሁት ምግብ ሩዝ ብቻ ነው ፤ ሰኞ ሩዝ በቲማቲም- ማክሰኞ ሩዝ በጅንጅብል- ረቡእ ሩዝ እንደወረደ፤ ወዘተ…ባጭሩ በሩዝና በሪዝ ተከብቤ ሰነበትሁ ማለት ይቻላል፤ አንዳንዴ ምግብ የቀየርኩ እንዲመስለኝ የምበላበትን ቦታ እቀያይራለሁ፤ ሳሎን ውስጥ ሁለት ማንኪያ እጎርስና የተረፈውን በረንዳው ላይ ተቀምጨ እጨርሰዋለሁ፤

ሩዝ ጠዋት ማታ ከመብላቴ የተነሳ ወደ ማጅራቴ ሲሸሽ የነበረው ፀጉሬ ተመልሶ ቅንድቤ ድረስ ግጥ—ም አለ ፤ የህንድ አክተር ለመምሰል የቀረኝ በሱሪ ላይ ቀሚስ መደረብና ባየር ላይ የሚበር ሞተር ሳይክል መንዳት ነው።

የሆነ ግልገል ጉንዳን ጠረጴዛየ እምብርት ላይ ከተበተኑት የሩዝ ቅንጣቶች መካከል አንዲቱን መርጦ ተሸክሞ ሲያዘግም ተመለከትኩ ፤ኩንታል መሸከሙ ነው፤ አይ ጉንዳን! አሁን ጉንዳንን የመሰለ ታታሪ ፍጡር በሚኖርበት አለም የሰው ልጅ የላባደሮችን ቀን ያከብራል ? ልይዘው ሞከርኩ ፤የጣቶቼን ጥላ ሲያይ ኩንታሉን እንደተሸከመ መሮጥ ጀመረ፤ አምልጠህ ሞተህል ባክህ! !ባውራ ጣቴና በነገረኛ ጣቴ መካከል አጣብቄ ያዝኩት ፤ የሞተ መስሎ ፀጥ አለ፤ ለካ አስመሳይነት የሰው ልጆች ባህርይ ብቻ አይደለም፤ ትወናውን አድንቄ በተሸከመው የሩዝ ቅንጣት ላይ አንዲት የቲማቲም ፍሬ መርቄለት ለቀቅሁት፤

ባለፈው ለለውጥ ያክል የሱካር ድንች ለመቀቀል ሞከርኩ፤ የአሜሪካ የሱካር ድንች አንዱ ፍሬ የድሮ ካውያ ያህላል ፤ ችግሩ በቀላሉ አይበስልም፤ እንዲያውም ካሜሪካ ሱካር ድንች፤ የኢትዮጵያ በሬ ሸኮና ቀድሞ ይበስላል፤ ቤት ጠርጌ ፤ምንጣፍ ቀይሬ፤ ኮርኔስ ራሱ ቀይሬ ተመልሼ መጥቼ ሳየው፤ አልበሰለም፤ ምን ጉድ ነው! ከዛ ገላየን ተታጥቤ፤ ብብቴንና በስተራስጌ የሚገኘውን ሁሉ ተላጭቼ ለባብሼ ሳበቃ ብረትድስቱን ከፈትኩት፤ ድንቼ መብሰሉን ለማረጋገጥ በሹካየ ወጋ አደረግሁት፤ እንዴየየየየ! 😳 የሹካው ጥርስ ተጣመመ፤ በጣም ተናደድሁና አውጥቼ በመስኮት በኩል ወረወርኩት፤ ድው! የሆነ ሰውየ oh Fuck! ብሎ ሲወድቅ አየሁት፤ ልጅ እያለሁ እናቴ “ ምግብ መወርወር ጡር ነው “ ትለኝ ነበር፤ እረ ጦርም ነው እማየ ፤ ይሄው አንድ ምስኪን ፖስታ አመላላሽ ፈረንጅ ለትንሽ ገድየ ነበር!

በክቡር ዳኛ Frank Caprio ፊት ቀርቤ ፤የፈነከትኩት ሰውየ እስኪሻለው ድረስ አልጋው አጠገብ ተቀምጨ በእንግሊዝኛ እንዳስታምመው ፈረዱብኝ! ሁለት ወር ሙሉ ተጎድቼ እንደከረምኩ ያወቅሁት በሆስፒታሉ ውስጥ የሚቀርበልኝን መኖ ሳይ ነው-ቆስጣ፤ የወይን ዘለላ፤ በማር የተጠበሰ ዳቦ! ግሪክ ሳላድ! እረ ወገን! ላስታማሚው እንዲህ አይነት ምግብ ከቀረበ ለታማሚው ምን እንደሚቀርብ ኢማጂን እንግዲህ!

ባልተያያዘ ዜና ፤

እንደ ዶክተር አቢይ አህመድ ያለ ብልጥ ሰው ግን አለ? ፤ ሰልስትና (ከሶስት ቀን በፊት) ተቃዋሚዎችን ፓርላማ ውስጥ ሰብስቦ ሲያወራ ማስኩን ካፍንጫው ሸርተት አድርጎ ከንፈሩ ላይ አስቀምጦት አየሁ ፤ ብዙ ሰው ስትራቴጂ መሆኑ የገባው አልመሰለኝም ፤የተፎካካሪ ፓርቲ ሊቀመንበሮች ” አንተ ብቻ ነህ እንዴ አፍንጫህን የማናፈስ ነፃነት ያለህ ?ብለው በእልህ ማሳካቸውን ገለቡት ፤ አብቹየም ሁሉም አፍንጫውን ማጋለጡን ከተመለከተ በሁዋላ ፈገግ ብሎ በልቡ፤ “ጎበዝ! እንግዲህ ይቺን ቫይረስ እንቃመሳታ ፤ እኔ ጎልማሳ ስለሆንኩ አገግሜ እነሳለሁ ፤ ለእናንተም ደግሞ አካላዊ ርቀቱን ያስጠበቀ ቀብር አስከባሪ ይዘጋጃል” ካለ በሁዋላ የምትከተለዋን ዘለሰኛ ማስታወሻው ላይ አሰፈረ፤

ጎልማሶች ከመከራ ስንማር ፤
ለሼባዎች ነፍስ ይማር !

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

One Comment

  • Anonymous commented on September 8, 2022 Reply

    ኤልያስ አሕመድ ነኝ
    ደረሳው
    ሐያት ብያለሑ ለ ፀሐፊው{ B£ውQ€Tu} Long life for you

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...