Tidarfelagi.com

ታክሲው!

ታክሲው እየሄደ ነው። ወዴት እንደሚሄድ አናውቅም። ሾፌሩ ያውቀዋል ብለን እናምናለን። የኛ ስራ መሳፈር ነው። የሾፌሩ ደግሞ መንዳት። ሾፌሩ ይነዳል። እኛ እንነዳለን። መንገዱ ጭር ብሏል፣ ይህ ከታክሲዎች ሁሉ የዘገየው ሳይሆን አይቀርም። ከሾፌሮች ሁሉ ሰነፉ ጋር ተሳፍረን ሊሆን ይችላል።

መንገዱ ገጭ ገጭ ይበዛዋል። መኪናዋ በገጭ ገጩ ብዛት ታቃስታለች። የሹፌሩ ፊት አይፈታም። ከፊት ለፊቱ “ሾፌሩን ማነጋገር ክልክል ነው” የሚል ፅሁፍ በደማቁ ተፅፏል። ይህን ፅሁፍ በተሳፋሪዎቹ እና በሾፌሩ መካከል ያለውን ስምምነት ጥሶ ያፃፈው ሹፌሩ ነው። ታክሲው በጣም እየፈጠነ ነው። ብዙዎች እንዳይጋጩ የፈሩ ቢሆንም አስፈሪውን ሾፌር ፈርተው ዝም ብለዋል። የማን እንደሆነ ያልታወቀ ድምፅ፣

“ኸረ ሹፌር ቀስ በል!” ሲል ጮኸ

“ ቡዙ መኪኖች ቀድመውን ሄደዋል! ፊተኞቹ አለዚያ መሃለኞቹ ላይ ለመመድረስ ያለን አማራጭ መፍጠን ነው!” አለ ሹፌሩ ረገጥ ባለ ድምፅ
“ታዲያ ደህና መኪና እና መንገድ ተይዞ ነዋ! ለመድረስ ፉክክር ሲባል እኛ መንገድ ላይ እንለቅ?… በዛ ላይ በትክክለኛው መንገድ አይደለም የመጣነው!” አለ ከኋላ የተቀመጠ አንድ ጎልማሳ። አንዳንዴ በታኪሲዋ ውስጥ ሹፌሩን በድፍረት የሚናገሩ ሰዎች ያጋጥማሉ- ከላይ እንዳለው ጎልማሳ!
ሹፌሩ እንዳልሰማ ዝም አለ! ዝም ይበል እንጂ ሆነ ተንኮል እያሰበለት እንደሆነ ግልፅ ነው። “ባቄላዎች ማደር የለባቸውም፣ ካደሩ ጥርስ ይሰብራሉ፣ በጊዜ መብላት ነው” የምትል ፍልስፍና አለችው። ባቄላ አይንቅም! አንዳንዴ ግን ሃሜት ሲበዛበት ባቄላዎቹን ዝም ይላቸዋል። አድረው…. አድረው….. አድረው…… በጥርስ እንደማይሞከሩ ሲያውቅ በመዶሻ ወይም በትልቅ መራጃ ከሽሽሽሽ…. ያደርጋቸዋል! ግብዓተ ባቄላ!!

መሃል አካባቢ ቁጭ ብያለሁ። ብዙዎች መሃል መቀመጥን ይወዱታል። “ከኋላም ከፊትም ከሚመጣ አደጋ ለመዳን የተሻለው ቦታ ነው” ይሉታል። ከኋላ የተቀመጡት በኋላ መስታወት የመጡበትን መንገድ በመናፈቅ አይነት ትክ ብለው ያዩታል። ብዙዎቹ እድሜ ከአርባ በላይ ይገመታል። ከፊት የተቀመጡት በሹፌሩ ትከሻ ላይ አሻግረው አማራጭ መንገድ በትጋት ይፈልጋሉ። በሌላ መንገድ መሄድ ቢፈልጉም ሹፌሩን ደፍረው ተሳስተሃል ለማለት ፈርተዋል። ደፍረው ተናገሩ ተገደው ወርደዋል። መንገዱ ጭር ያለ ነው- ማንም እዚህ አውላላ መንገድ ላይ ተገዶ መውረድ አይፈልግም። መሄጃ የለም።
መሃል ላይ እኔና መሰሎቼ አለን። ፊተኞቹ የኋለኞቹን “የድሮ ናፋቂዎች” ሲሉ ይተቿቸዋል። ኋለኞቹ፣ ፊተኞቹን “ያልበሰሉ ችኩሎች” ይሏቸዋል። መሃል የተቀመጥነውን ከፊትም ከኋላም ያሉት መሃል ሰፋሪዎች ይሉናል። እኛ ግን ማንንም ምንም አንልም።

ታክሲው እየሄደ ነው! የታክሲው ገጭ ገጭ ደንታ ሳይሰጣቸው ያንቀላፉ አሉ። ቢቀሰቅሷቸው አይሰሙም። ድሮም “አውቆ የተኛ…” እያሉ ይተርቱባቸዋል። የተተረተባቸውንም የተረቱባቸውንም አይሰሙም።

ሁላችንም እዚህ ታክሲ ውስጥ የተሳፈርነው ካለመሰፋር እንደሚሻል አምነን አይደለም። ታክሲ ውስጥ ነው እራሳችንን ያገኘነው። የሹፌሩ ስራ መንዳት ነው፣ የኛ መነዳት። እየተነዳን ነው። የሹፌሩ አዝማሚያ ስላላማራቸው የወረዱ አሉ። ሹፌሩን ስላላማሩት ረዳቱ አንቆ ያወራደችም አሉ። ዘለው የወረዱም ነበሩ( ትክት ብሏቸው… እራሳቸውን ለማጥፋት የፈለጉ ዓይነት)

የሹፌር አገዛዝ የሰፈነባት ታክሲ ውስጥ ነን። ከተሳፋሪዎች ሁሉ ተለይቶ፣ ሹፌሩ ብቻ “ የደኸንነት ቀበቶ” ታጥቋል። የሹፌሩ በሕይወት መኖር ከሌሎቹ ተሽሎ ተፈልጓል ማለት ነው። “ብዙሃን ይመውኡ…” የሚል ፍልስፍና አይሰራም እዚህ። መንገዱን የሚመርጡት ተሳፋሪዎች አይደሉም፣ ሹፌሩ ነው። ዘመን ሲከዳ መንገድ መራጭ ሹፌር ላይ ይጥላል! …አንዳንድ ተሳፋሪዎች በመንገዱ ዙሪያ ከሹፌሩ ጋር ይጨቃጨቃሉ። ሹፌሩ ከራሱ ሃሳብ ውጪ የማንንም አይሰማም፣ “መንገዱን ለኔ ተዉልኝ” ያለ ይመስላል። “ከኔ በላይ ሹፌር…” የሚል ትምክህት እንደጨመደደው ያስታውቃል። ከሱ ቀደም ያሉትን ሹፌሮች ታሪክን እያጣጣለ ማውራት ይወዳል። “ሹፌራችሁ እኔ ባልሆን ገደል ገብታችሁ ታልቁ ነበር” ብሎናል ደጋግሞ….(አሁንስ ገደል ውስጥ አይደለንም?) ለዚህ ግራ የገባው ተሳፋሪ ራሱን መሲህ አድርጎ አቅርቧል። ከዚህ በፊት ባሉት ሹፌሮች ለተሰራባቸው ሃጢያት ስርየት ሊሰጥ እንደወረደ መልዕክተኛ….. ደንባራ በማንፃት ሰበብ አምጥቶ ያራገፈውን ሃጢያት አላየም። ቡዙዎች ያመኑት ይመስሉ እንጂ አለማመናቸውን ማወቅ አያዳግትም። ያመኑት ጥቂት ልበ-ስሶች ግን አልጠፉም።

ታክሲው መንገዱን ቀጥሏል። መንገዱ ገጭ ገጭ ይበዛዋል። የሹፌሩ ፊት ኩስታሬም ሌላ ገጭ ገጭ ነው። ታክሲዋ ከመንገዱ ጋር በምታደርገው ትግል ታቃስታለች። እኔ ሰልችቶኛል። መሃል ቁጭ ብዬ እንዲህ አስባለሁ፤
“ ኡፍፍፍ… ምናል እንደተሳፋሪ ሁሉ የሹፌርም ወራጅ በኖረ? ማነህ ሹፌር…ወራጅ በል እባክህ…. መሪው ላይ ተወልዶ መሪው ላይ ሞተ መባል ላንተስ ስም መልካም ነው? ወራጅ! ወራጅ! ወራጅ አለ ሹፌር?……………………ማን?…………… ሹፌሩ!!!”
ቢሆንም ታክሲው መንገዱን ቀጥሏል። ሹፌሩም በቦታው ነው።
****

አባሪ ፡)

ከዚህ ፅሁፍ ጋር በርዕስ እንጂ በታሪክ የማይመሳሰል ሌላም ፅሁፍ አለ።
(ስለዚህ ይቀጥላል ግን አይቀጥልም)

የራስ ናቸው፡፡ የማንንም ሃሳብ ለመፃፍ አልተከፈተም! የሚያስማሙንን ሃሳቦች እዚህ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ ለመስማማት አንፅፍም፣ ለመፃፍ አንስማማም፡፡ ወዘተ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...