Tidarfelagi.com

ታሪክን የሁዋሊት 2

ዘመነ መሳፍንት በሚባለው የየጁዎች መንግስት ወቅት እንዲህ ሆነ፤ ራስ አሊ የተባለ ጎፈሬ መስፍን አገሪቱን ይመራ ነበር፤ ከእሱ በታች፤ ደጃች ውቤ የተባለ ባለሹርባ መስፍን፤ ከስሜን እስከ ምፅዋ ያለውን ግዛት ያስገብራል።

የሆነ ጊዜ ላይ ውቤ ደጃዝማችነቱ አላረካው አለ፤ ደጁን ብቻ ሳይሆን ሙሉውን ግቢ ፈለገው፤ ለመንገስ በጣም ሻፈደ፤ በምፅዋ በኩል ብዙ ጠመንጃ እየሰበሰበ አካማቸ፤ ብዙ ጭፍራ መለመለ፤ የሚቀማውን ስልጣን የተገባ Legitimate ለማድረግ አባ ሰላማ የተባለ የግብፅ ቅጥረኛ ጳጳስ አሰናዳ፤ የሚቀረው ምንድነው? ራስ አሊን ከስልጣን ማባረር።

ታሪኩን ላሳጥረውና፤ ራስ አሊና ውቤ ደብረታቦር ላይ ገጥመው ተፈሳፈሱ! በጦርነቱ ላይ የውቤ ባለነፍጥ ሰራዊት የራስ አሊን ፈረሰኛ እንደ ቅጠል ያረግፈው ጀመር ፤ ነገሩ ያላማረው ራስ አሊ ብረት-ለበሱን ማለቴ ፈረሱን የሁዋሊት አዞረና ቆሰቆሰው፤ አብዛኞቹም ወታደሮቹም ተከትለውት ሸሹ፤
ውቤ፤ ነገሩ አሸወይና እንደሆነ ሲመለከት ድንኩዋኑን ጥሎ አስደግሶ ወታደሮቹን የድል ምሳ ጋበዘ፤ ምሳው እየተበላ ጠጁ እየተጠጣ ወታደሮች እየመጡ ይፎክራሉ፤ ምርኮኞችም ደግሞ መሳርያቸውን እየጣሉ በውቤ ፊት ይንበረከካሉ፤ በዚህ መሀል፤ አሊጋዝ ብሩ የተባለ እውቅ፤ የየጁ ጀግና ወደ ደጃች ውቤ ቀረበ፤ ሌሎች ምርኮኞች እንደሚያደርጉት መሳርያውን የሚያስቀምጥ ይመስል በርከክ እንደማለት አለና” እጅ ወደላይ “ብሎ ጮኸ! ውቤ ቁጭ ባለበት ደርቆ ቀረ፤ ምንም ማድረግ አልቻለም፤ እየጋጠ የነበረውን የዶሮ ቅልጥም ማእዱ ላይ አስቀምጦ እጁን ወደ ላይ አነሳ፤ ( የቅልጥሙን ቀደዳ እንኩዋን እኔ ነኝ የጨመርኩት)

ራስ አሊ፤ ከሸሸበት ቦታ ሆኖ አንድ መልክት ደረሰው ፤
“ውቤ ተማርከዋልና ከሸሹበት ይመለሱ” ይላል መልእክቱ
ይህ በሆነ በማግስቱ አንዲት ባልቴትና እና አንድ ሰውየ መንገድ ላይ ተገናኙ፤
“እቴዋ ! የራስ አሊና የደጃች ውቤ ጦርነት እንዴት አለፈ?” አለ ሰውየው፤
“ራስ አሊ ሸሹ፤ ደጃች ውቤ አሸንፈው ተማረኩ” አሉ ባልቴቲቱ
“እረ ባክዎ በቅጡ በቅጡ አድርገው ያውጉኝ”
“ተወኝ ባክህ ! እነሱ በቅጡ ያልተዋጉትን እኔ እንዴት በቅጡ ላውጋው?”

ከዚህ አጭር የታሪክ ገጠመኝ በተሻለ መንገድ ዘመናዊ ኢትዮጵያን ፖለቲካ የሚያብራራ ንድፈ ሀሳብ ይኖራል?

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...