ይህች መናጢ ግብፅ ከኤርትራ ጋር ተሞዳሙዳ፤ ‹‹አንድ ቀን ታርቀን ቤት ሰርተንበት በአብርሃም አፈወርቂ እና በቴዲ አፍሮ ዘፈን አብረን እንጨፍርበታለን›› ያልነው ዳህላክ ላይ የጦር ቤቷን መገንባት ጀመረች አይደል?
ግብፅም፣ አዲሷም ተኝተውልን አያውቁምና ነገሩ ብዙ ባይደንቅም ክፉኛ ያስተክዘኝ ገብቷል።
የሚያምሰን ነገር በዝቶ በተጨነቅንበት በዚህ ጊዜ ይሄም መጨመሩ፤‹‹በገጣጣ ላይ ወላቃ›› ሆኖብኛል።
‹‹እኔን ኢትዮጵያዬ!
መቼ ይሆን ‹‹ጥርስ የገባች ሀገር›› መባልሽ የሚያበቃው…?መቼ ይሆን ከየአቅጣጫው አሰፍስፈው በከበቡሽ ጥርሶች የመታኘክ ስጋትሽ ባይጠፋ እንኳን የሚቀንሰው? ›› ያስብለኝ ጀምሯል።
የፖለቲካ ሳይንስ ስማር ተደጋግመው ከሰማኋቸሁ ነገሮች አንዱ፤ ‹‹ሠላምን የምትፈልግ ሀገር ለጦርነት መዘጋጀት አለባት›› የሚል ነው።
ነገሩ ሳይንዛዛ ሲተረጎም ፤
‹‹አንድ ሀገር ሠላም ከፈለገች ፤ የክተት አዋጅ ባትሰጥም፣ ነጋሪት ባታስጎስምም፣ ስማ በለው ባታስለፍፍም፤ ጡንቻዋን ማዳበር፣ በውስጥ መደራጀቷን ለጠላቶቿ በሚገባ ማሳየት አለባት። ባስፈለገ ጊዜ ለክተት ዝግጁ መሆኗን፣ ነጋሪቷ ሩቅ አለመሆኑን፣ ለስማ በለው አቆብቁቦ የሚጠብቅ ህዝብ እንዳላት ማሳየቷ በማስፈራራት ሠላምን ያስገኝላታል ››ማለት ነው።
‹‹ዋ! አትሞክረው…ብትሞክረው ግን ይሄ ሁሉ አለኝ…እደቁስሃለሁ!›› እንደማለት ነገር…
በር ላይ ‹‹እዚህ ቤት ተናካሽ ውሻ አለ›› ብሎ እንደመለጠፍ ነገር ።
እኔ እንግዲህ ተማሪ ሆኜም፣ አሁንም በዚህ አምናለሁ። ለዲፕሎማሲ በቀኝ እጅ ከጠላት ጋር እየተጨባበጡ፣ በግራ እጅ ግን ዲፕሎማሲ ከከዳ የሚወረወር ድንጋይን በመሳል አምናለሁ።
ጦርነት ወዳጅ አታደርጉኝ።
የአለም ነባራዊ ሁኔታ አይፈቅድም እንጂ ፤‹‹ሠላምን ከፈለግህ ሠላም ተዘጋጅ›› በሚለው የየዋሆች ጥሪ ማመን እፈልጋለሁ። ላሁኑ ግን ‹‹ሠላምን ከፈለግህ፣ ለሠላም እየሰራህ ለጦርነትም ተዘጋጅ›› በሚለው ይበልጥ አምናለሁ።
ጓደኞቼ ግን ‹‹አንድ ሃገር ሠላም ከፈለገች በመዘጋጀት ፈንታ ጦርነት መሄድ አለባት›› ባዮች ናቸው። በተለይ ለኢትዮጵያ ሲሆን።
እንግዲህ የጭቅጭቃችን አስኳል ይሄ ነው።
እነሱ፤ በከባድ የቁጭት ስሜት ተናውጠው፤ ‹‹አንበሳ ሆነን ዝንብ ይጫወትብን ጀመር! የአድዋን ድል ባከበርን ማግሥት አረብ ይክበበን!? እኛ እዚህ ዲፕሎማሲ ምናምን ስንል ተከበብን እኮ…ጥርስ ውስጥ ገባን እኮ…መዋጋት አለብን…! ማንነታችንን ሄደን ማሳየት አለብን…!አሰብን ጠቅልለን..ምፅዋን ቀምተን፣ ግብፅን ማንጰርጰር አለብን ›› እያሉ ይሞግቱኛል።
እኔም ሀገሬን እወዳለሁ።
እንዳኳችሁ ለ‹‹ድንገት ቢያስፈልግ›› ፣
ለ‹ የሚሆነውን ማን ያውቃል?›› ግጭት በመዘጋጀት አምናለሁ። ግን ሠላምን ለማግኘት ለጦርነት በመዘጋጀት እንጂ ጦርነት በመሄድ ፈፅሞ አላምንም።
ለምን ቢባል ፤ የአለምም፣ የእኛም ሁኔታ ከአድዋ ወዲህ እጅግ ከመለወጡም ባሻገር ፤ በጦርነት ‹‹አሸነፍኩ›› ብሎ የደነፋ ሀገር እንኳን አሸንፎ እውነተኛ ዋጋው ሲሰላ አሸንፎ አይተን አናውቅም።
ለምን ቢባል፤ ‹‹ አሸነፍኩ›› ብሎ ‹‹ለምን ?›› ሲሉት ‹‹እኔ የገደልኩት ከሞተብኝ ይበልጣል›› ብሎ ድግስ ያብላ እንጂ የቱም ጦር ፍፁም ድልን መቀዳጀቱን ሰምተን አናውቅም።
ለምን ቢባል ፤ አሁን በዚህ ሰአት፤ ክተት ሳናውጅ፣ ነጋሪት ሳናጎስም፣ ስማ በለው ሳናስለፍፍ እየተዋጋናቸው ያሉ ብዙ ጦርነቶች አሉብን። (እነ እንትና..አደራችሁን፤ ‹‹ አንዱ ከድህነት ጋር ነው››ብላችሁ እንዳታጨሱኝ!)
….እናም ኢትዮጵያዬ…. ስሚኝ።
ተዘጋጂ፣ ግን አትሂጂ።
One Comment
አንድነት