በየነ ባልንጀራየ ነው፤ ጦርነቱ ሲጀመር “በዩማ ቲዩብ “ የሚል የዩቲዩብ አካውንት ከፍቶ መሸቀል ጀመረ፤ አንዳንዴ የድል ዜና ሲጠርርበት ሰለ አድዋ ወይም ስለዶጋሊ ድል በመተረክ ፕሮግራሙን ይሞላዋል፤ አንዳንዴ የኔን ግጥም ሳይቀር ከፌስቡኬ ላይ ወስዶ ይዶልበታል፤ ሳንቲም ማካፈሉ ይቅር ፤ ክሬዲት እንኳ ሊሰጠኝ አልፈለገም።
አንድ ቀን ንድድ ብሎኝ ፤
“ለምንድነው ግጥሜን አንብበህ ስሜን የዘለልከው? ”ብየ ጠየኩት።
“ለደህነነትህ ስለማስብ ነው” አለኝ ኮሰተር ብሎ።
“ስለፍቅር በጻፍኩት ግጥም ምን አይነት የደህንነት ችግር ሊገጥመኝ ይችላል?
“ህዝብ በየግንባሩ እየተዋደቀ ስለፎንቃ መፈላሰፍህ ያናደደው አንዱ ደብድቦ ሊገልህ ይችላል! ጊዜውን መምሰል ያልቻለ እድሜው ያጥራል”
“ጊዜውን መምሰል ያልቻለ እድሜው ያጥራል “ የሚለው የማን ጥቅስ ነው ?” አልኩት፤
“የኔው ነው! የተልባ ማሻው ሚካኤል ነው ያቀበለኝ”
ትናንት በየነ ቤቱ ምሳ ጋበዘኝ፤ በጨዋታችን መሀል አማርኛው እንዴት እንደ ተለወጠ ታዘብሁ።
ስንበላ “ ባይሆን ከጎረድጎረዱ ቅመስ ! ይሄ አደገኛ ትርክት የመሰለ ፊትህ የማይወዛው ስጋ ስለማትበላ ነው “ አለኝ፤
በየጉርሻው ጣልቃ “ ብላ እንጂ ፤ ሆድና ግንባር አይሸሸግም” እያለ ይጎተጉተኛል፤
“ቆይ! ግንባር የሚል ቃል ሳትጨምር ማውራት አትችልም?” አልሁት ።
“በገዛ ቤቴ የፈለገኝን ማውራት መብቴ መሰለኝ ፤ ሁለተኛ ልታርመኝ ብትሞክር በዚህ ጠርሙስ ነው ግንባርህን የምተረክከው ! ግንብአራም !”
ማእዱ ከተነሳ በሁዋላ፤
“ከእምብርቴ በታች ውጥረት ነግሷል “ ብሎ ወደ መጸጃ ቤት ሄደ።
ከተመለሰ በሁዋላ ብዙ ተቀምጦ አልቆየም።
“አሁንም ሽንት ቤት ልቴድ ባልሆነ” አልሁት፤
“አዎ! ተቆርጦ የቀረውን አራግፌ እመለሳለሁ”