Tidarfelagi.com

‹‹ ባይተዋር›› (ክፍል ሁለት)

ምንድነው የሚያደርገው?

ቀጥታ ወደ ኩሽና ሄዶ ከቢላዎች መሃል ትልቁን ቢላ መርጦ እየተምዘገዘገ አጠገቧ ደርሶ አትክልቶቿ ፊት እንደ አትክልት ይከትፋታል?
የኔ አንጀት እንዲህ ነው የተበጠሰው ብሎ በቢላው አንጀቷን በጥሶ ያሳያታል?
ልጆቿ /ልጆቻቸው ፊት ይገድላታል?

አያደርገውም፡፡

ፊትለፊቱ የተቀመጠውን ትልቅ መስኮት የሚያህል ቴሌቪዥን (ያ ሁሌ እንደ ጨዋ ሴት በጊዜ ቤቷ ተሰብስባ፣ ተጎልታ የምታየውን) ይከሰክሰዋል?
ልብሷን ሁሉ እያወጣ ፀያፍ ስድብ እየተሳደበ…‹‹አንቺ ሸርሙጣ›› ምናምን እያለ በረንዳ ላይ ይወረውረዋል?
እንደ ቆሰለ አውሬ ያጓራል?
እንዳበደ ውሻ ይጮሃል?

አያደርገውም፡፡

በዚህ ሁሉ ፈንታ ስልኳን አንስቶ ያነበበውን ሁሉ በስልኩ ፎቶ ያነሳል፡፡
ሊፈታት ጠበቃ ሲቀጥር፣ ህግ ፊት ሲቀርብ የማያዳደግም መረጃውን አደራጅቶ ያቀርባል፡፡
በቤተሰቧ ፊት ያሸማቅቃታል፡፡
በሚኮሩባት እናቷ ፊት ያዋርዳታል፡፡
በሚመኩባት አባቷ ፊት ፊት ይነሳታል፡፡

ያ-ሸ-ማ-ቅ-ቃ-ታ-ል፡፡

ከዚያ ልጆቹን ይወስዳል፡፡ ያሳድጋል፡፡
ሴት ከሚባል ፍጡር ይሸሻል፡፡ የመነኩሴ ኑሮ ይኖራል፡፡

ከዚያ ሁሉ በፊት ግን ያዋርዳታል!

ብልግናዋን ፎቶ አንስቶ ሲጨርስ በረንዳ ላይ በተቀመጠችበት ደግሞ አያት፡፡

ይህች ፒጃማ ቀሚሷን ሰብስባ፣ በርጩማ ላይ ጨዋኛ የተቀመጠችው ሴት ማናት? ማናባቷ ናት?

ጤነኛ አይደለሁም ይሆን ብሎ አሰበ፡፡ ማንም በኔ ቦታ የሚቀመጥ ወንድ፣ ማንም ጤነኛ ባል የሆንኩትን ሆኖ፣ ያየሁትን አይቶ፣ በደሌን ቀምሶ፣ ህመሜን ታሞ እዚህ ቁጭ ብሎ የመረጃ ፎቶ አይሰበስብም፡፡ ያ-ብ-ድ- ነበር፡፡

ጤነኛ አይደለሁም ይሆን እንዴ? ብሎ አሰበ፡፡

በነጋታው፣ እሁድ አንዱ ጠበቃ ወዳጁን አግኝቶ ሁሉንም ነገር ዝክዝክ አድርጎ ነገረው፡፡

የሚጠቅም የህግ ምክር ከመስጠት ይልቅ መላጣ ጭንቅላቱን በእምቢታ እየነቀነቀ፣ ‹‹አይታመንም…ሜላት…?ሜላት አንዲህ ታደርጋለች….አይሚን…ሜላት?›› ሲል አረፈደ፡፡

‹‹እሱን ተወውና ህጉን ንገረኝ…›› አለ ሰናይ ስሜት አልባ ሆኖ፡፡

‹‹ሜላት ካልታመነች ማን ይታመናል? የቤት ልጅ….ቤቴ ቤቴ የምትል ሴት ካልታመነች ማን ይታመናል….?››

‹‹…ያለንበት ዘመን እኮ ከባድ ነው፡፡ እኔም እስካሁን አላመንኩም…እኔም…እኔም ትዳሬ ይሄ ነው …ውሸት ነው ብዬ እስካሁን አልተቀበልኩም…በደመነፍስ ነው ያለሁ…ብቻ…››

‹‹አልፈርድብህም…ማንን ማመን ይቻላል?››

‹‹ብቻ ምን አስባለሁ….የዘንድሮ ነገር ሁሉም ውሸት ነው….እንዲሁ ዘመንህን ሁሉ ደፋ ቀና ትላለህ እንጂ ሁሉ ነገር ውሸት፣ ሁሉ ሰው ውሸታም ነው….››

‹‹ያስብላል››

‹‹ ውሸታም ብቻ ነው ሰው ሁሉ ….እዬውልህ…አንተ ብዙ ባለትዳር ትዳኛለህ አይደል….እስቲ የዘንድሮ ባለትዳሮችን ቀድመው ሳይዘጋጁበት ስልካቸውን ለሰላሳ ደቂቃ ሳይቀልፉ ለባለቤታቸው ትተው እንዲሄዱ ጠይቃቸው፡፡ ያቺ ሰላሳ ደቂቃ ስታልቅ ከመፍረስ የሚተርፍ ብዙ ትዳር አይኖርም›› አለ ሰናይ በደመነፍስ፡፡

‹‹እውነትህን ነው….ሜላት እንዲህ ካደረገች…..››

ሰናይ ዝም አለ፡፡

‹‹እኔ የምልህ….››
አለ ጠበቃው ግርምቱ ሳይለቀው፡
‹‹እ?››
‹‹የበደልካት ነገር አለ እንዴ??
‹‹ማ? እኔ?
‹‹እ….››
‹‹ምን እበድላታለሁ….?በርግጥ ስራ አበዛለሁ…ግን ብለፋ ለእሷ…ለልጆቼ፣ ለትዳሬ ነው….››
‹‹እሱማ አዎ…ግን እንደው…የባልነትህን አጉድለህባታል እንዴ?.. ጠበቃው መላጣውን እያሻሸ ጠየቀ፡፡
‹‹ምን ማለትህ ነው?››
‹‹ታውቃለህ››
‹‹ምን ማለትህ ነው….?ሶስት ልጆች አሉን እኮ!››
‹‹እ…ሶስት ልጆች አሉን ማለት ምን ማለት ነው…?››
‹‹ሶስት ልጆች አሉን ነዋ!›› ሰናይ ቱግ አለ፡፡
‹‹ሰናይ…ረጋ በል…ምን ለማለት እንደፈለግኩ ገብቶሃል….››
‹‹አስረስ ! ሶስት ልጆች አሉን!››
‹‹ምን አስሬ ሶስት ልጆች አሉን ሶስት ልጀች አሉን ትለኛለህ…?ያ እኮ የሚያጋግጠው ሶስት ጊዜ ግብረስጋ እንደፈፀማችሁ እንጂ ሚስትህ አልጋ ላይ ባንተ ደስተኛ እንደሆነች አይደለም! ››
‹‹ውጣ……ውጣልኝ….›› ሰናይ ጮኸ፡፡
‹‹ሰናይ…ልረዳህ እየሞከርኩ ነው….በኃላ ልታነሳው ትችላለች…›
‹‹ውጣልኝ አልኩህ!››
አስረስ መላጣው በላብ እያብረቀረቀ ሹክክ ብሎ ወጣ፡፡

ሰናይ ራሱን ካረጋጋ በኋላ አስረስ ስላነሳው ጉዳይ አሰበ፡፡

‹‹ ‹‹ምን አስሬ ሶስት ልጆች አሉን ሶስት ልጀች አሉን ትለኛለህ…››
ሰናይ ስለ ልጆቹ አሰበ፡፡
ስለ የበኩር ልጁ ፣ ስለ አስራ አንድ አመቱ ይትባረክ፡፡
የዋሁና ፍልቅልቁ ይትባረክ፡፡

ስለ ሁለተኛ ልጁ በአምላክ፡፡ የስምንት አመቱ በአምላክ፡፡
አይናፋሩ እና ጎበዝ ተማሪው በአምላክ፡፡

ስለ መጨረሻ እና ብቸኛ ሴት ልጁ በፍቅር፡፡ ተጠብቃ ተጠብቃ ፣ በስንት አሳር፣ በስንት መከራ፣ ዘግይታ የመጣቸው የአመት ተኩልዋ በፍቅር፡፡ ‹‹ሰው ሁለት ወልዶም መሃን ይሆናል እንዴ!›› ብለው የተጨነቁባት የዘገየችው በረከታቸው በፍቅር፡፡

ለሰው አይባልም እንጂ ..በአደባባይ አይነገርም እንጂ ፣ ከልጆቹ ሁሉ አብልጦ የሚወደው እሷን ነው፡፡ በምህላ ስለመጣች ብቻ አይደለም፤ ካገባ አንስቶ ሴት ልጅ እንደተመኘ ነበር፡፡
ሰናይ ስለ ልጆቹ አሰበ፡፡
ሰናይ ስለ ወስላታ ሚስቱ አሰበ፡፡
ሰናይ ከወስላታ ሚስቱ ስለወለዳቸው የሕይወቱ አምዶች፣ ስለ ልጆቹ አሰበ፡፡

በድንገት ላብ አጠመቀው፡፡
በድንገት ብርድ ብርድ አለው፡፡
አንቀጠቀጠው፡፡

ልጆቹ ልጆቹ ባይሆኑስ?

እ?

ሚስቱ ሚስቱ ካልሆነች፤ ታማኝ ሚስቱ አጭበርባሪ ከሆነች…ልጆቹ ልጆቹ ባይሆኑስ?

እ?

አባዬ የሚሉት ልጆቹ አባታቸው ሌላ ቢሆንስ?

ልጆቹ ልጆቹ ባይሆኑስ!?
እሪሪሪ ብሎ መጮህ፣ እንደ እንስሳ ማጓራት አሰኘው፡፡
በተለይ በፍቅርን አሰበ፡፡ በስንት ልመና፣ በስንት ምልጃ ፣ ከስምንት አመት በኋላ የተገኘችውን የወርቅ ዘለላ በፍቅርን አሰበ፡፡
በፍቅር…በፍቅር…

በፍቅር…
አንደኛ፣ ….ከእሱም ከሚስቱም የማይገጥም ቅላት አላት፡፡
ሁለተኛ፣ …..ከሁለቱም በተቃራኒ አይኖቿ ጠበብ ያሉ ናቸው፡፡
ሶስተኛ፣ ….ከሁለቱም በተቃራኒ አፍንጫዋ ደፍጠጥ ያለ ነው፡፡
ሰናይ እግሮቹ አልቆም አሉት፡፡
እጆቹ አልታዘዝ፣ አይኖቹ አልከፈት አሉት፡፡
ሁሉ ነገር ይሽከረከርበታል፡፡
ሁሉ ነገር ይዞርበታል፡፡
እንደምንም ያለ የሌለ ሃይሉን አስተባብሮ ከሚስቱ መልእክቶች ያነሳቸውን ፎቶዎች ስልኩ ላይ ከፈተ፡፡ የተበጠሰ አንጀቱን በእጁ ደግፎ፣ የተዛባ ሚዛኑን በግድ አስተካክሎ….ሚስቱን ያማገጠውን ሰው መልክ ለማየት፣ አይቶም ከልጆቹ ለማመሳከር፣ አመሳክሮም ልጆቹን፣ በተለይ በፍቅርን የራሱ ለማድረግ፤ የማይቻለውን ችሎ ቀጥ ብሎ ቆመ፡፡

ልጆቹን ልጆቹ አድርጎ ለማቆየት ችሎ ቆመ፡፡

ዋትስ አፕ ላይ በሚስቱ ‹‹ናፍቀኸኛል፣ ፎቶህን ላክልኝ›› ውትወታ በየቀኑ ከኤ ለሚስቱ የተላኩትን ፎቶዎች ማስቀመጡ ትዝ ይለዋል፡፡

ፈለገ፡፡አሰሰ፡፡
ፈለገ፡፡ አሰሰ፡፡

አንድም ፎቶ አጣ፡፡

እንደዞረበት፣ ለድጋፍ ጠረጴዛ ተደግፎ እንደቆመ፣ በሙሉ አይኑ ሳያያቸው፣ ሳያስተውላቸው፣ በደመነፍስ በመረጃነት ያስቀመጣቸው የ ኤ ፎቶዎች የት እንደሄዱ ለማሰብ ሞከረ፡፡

ትላንት ማታ ሁሉ ነገር ካቅሙ ሲበልጥበት እንዳጠፋቸው ትዝ አለው፡፡
በንዴት በጅምላ እንዳጨዳቸው አስታወሰ፡፡

ምን ይመስል ነበር?
ኤ መልኩ ምን አይነት ነበር?

በብዥታም አልታወስ አለው፡፡
ኤ ምን አይነት ነው?
ኤ…ኤ.. ምን ይመስላል? ማንን ይመስላል?
በፍቅርን ያየ ሰው ሁሉ፣ ‹‹ይህችኛዋስ አንዳችሁንም አትመስልም!››
‹‹ከቅላቷ የጎራዳነቷ….››
‹‹ በዛ ላይ አይኗ የቻይና ነው…ምንም አትመስላችሁም›› ሲል ታወሰው፡፡

ግን ደግሞ ቤተሰብ ሁሉ ‹‹ ቁርጥ ያንተን እናት ትመስላለች…አያቷን ትመስላለች›› ይለዋል፡፡

አዎ….ልክ ናቸው፡፡ እናቱን ነው የምትመስለው፡፡ በተለይ አፍንጫዋ፡፡ አይኗስ ቢሆን?

ግን ኤ…ኤ… በፍቅርን ይመስላል?
ኤ …ልጁን በፍቅርን ይመስላል? ወይስ በፍቅር መልኳ ከእናቱ ብቻ የተቀዳ ነው? ነው ወይ?
በመቅበዝበዝ እንደገና ስልኩን በረበረ፡፡ ለወሬ ነጋሪነት ያስቀመጠው አንድም ፎቶ፣ መልስ ለማግኘት የሚያስችለው አንዳችም ትውስታ አጣ፡፡

ፈፅሞ ተበጠበጠ፡፡
ኤ ምን ይመስላል?
ኤ ብስል ቀይ ነው?
ኤ አፍንጫ ደፍጣጣ ነው?
ኤ አይኖቹ ጠባብ ናቸው?
ናቸው ወይ?

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...