ባትሄጂ ኖሮ፣ ብትሆኝ ከኔ እቅፍ
እዚህ ከፃፍኩት ላይ፣አንድም መስመር አልፅፍ፡፡
አቤት ባትሄጂ!
ግን አንቺ አልቆምሽም
መጓዝ አልደከምሽም፡፡
ይሄዋ፡-
ከሄድሽ በኋላ ዐይኔም አይታየው፣ ጆሮዬም አይሰማ
ልቤም ደም የሚረጭ፣ ባንቺ ስለደማ፡፡
አንቺ በመሄድሽ፤
ያለህይወት በህይወት ተነጥላኝ ነብሴ፣
ያው አለሁ ሙት ሆኜ፣ ለሰዉም ለራሴ፡፡
ባትሄጂ እኮ ኖሮ፣ ይህ ሁላ አይሆንም
በቀን አይጨልምም፣ በሌት አላፈጥም፡፡
የፈተልነው መውደድ፣ ያደራነው ፍቅር
ማልበስ እየቻለ፣ ሶስትና አራት አገር
እንዴት አልታመም፣ እንዴት አልሰበር
ደርሶ ላንቺ ሲያጥር?!
ካጣሁሽ ኋላ ነው፤
ወጣች ያልኳት ፀሀይ የተደበቀችው
ተስፋ ማጣት፣ ልቤን ውስጤን የሞላችው
ድህነቴ መስሎኝ፣ አንቺን ከኔ ያሸሸ
እየሰራሁ ነግቶ፣ እየሰራሁ መሸ
ግን አልተመለሽም፣
እዚህ ነኝ አላልሽም፡፡
ላትመጭ መሄድሽን፣ ውስጠቴ እያወቀው
ከብዙ ሴቶች ጋር፣ አብዝቼ የምታየው
ቅናት ሸንቆጥ አርጎሽ፣ ብትመጪ ብዬ ነው፡፡
ግን አይከሉት ፍቅርሽ፣
እየተዋለደ፣ ስር እየሰደደ
ብዙ ዓመት ነጎደ፣ ውስጤ እየነደደ፡፡
ባትሄጂ ኖሮ….
በመብራትና በመጥፋት
በመጨለምና በመታየት
መሃል ሆኜ፣ መሀል ቆሜ
ስሽከረከር፣ ስንፈራፈር
መች ታገኚኝ ነበር?!
አንቺ በመሄድሽ፤
እየሳኩ አነባሁ፣ እያነባሁ ሳኩኝ
ሀዘን ልቤ ገባ፣ ደስታ ቤቴን ናድኩኝ
አንቺ በመሄድሽ፤
ሙላቴ ጎደለ፣ ጉድለቴም አየለ
ጣፋጭ ልቤ መሀል፣ ምሬት ተጨመረ
ቀኑና ጨለማው ባንድ ተቋጠረ፡፡
በሰዎች ጫካ ውስጥ ብቸኝነት ዋጠኝ
ከሰውነት ወጣሁ፣ ሰው መሆን ናፈቀኝ፡፡
እውነት ግን ሄደሻል?
ብርሃን ዐይኖችሽ ጨልመውብኛል?
አጫዋች ጡቶችሽ፣ አኩርፈውባኛል?
ሳቂታ ጥርሶችሽ፣ ተጋርደውብኛል?
ወይን ሴትነትሽን አቆምጠሸዋል?
ያ ባህር ዳሌሽን አድርቀሽብኛል?
እውነት ነው አትበይኝ፣
ቢሆን እንኳ አቢይኝ፡፡
ግን ካጥንቴ ሰርፀሽ፣ ተዋህደሽ ከደሜ
እውነት ይመስልሻል ሄድሽ ቢል አዳሜ!?
ግንማ ባትሄጂ(2x)
መች እንዲህ ይከብዳል፣
መች እንዲህ ይበርዳል፡፡
በእርግጥ እሱ ጠርቶሽ፣ እንዴት ትቀሪያለሽ
መሄድሽ ነው መልካም፣ እሱን አስበልጠሸ
መጓዝሽ ነው ጥሩ ከኔ ተደብቀሽ፡፡
ይሁን ሂጂ መልካም
አይነኩትን ነገር፣ ሄድሽ ብዬ አልነካም፡፡
አንቺን ቢወስድሽም በህጋዊ መንገድ፣
ህገወጥም ሆኜ ካንቺው እመጣለሁ፤ ተሳፍሬ ገመድ፡፡
ባትሄጂ ኖሮ፣ ሳትወጂ ሳትፈቅጂ
ፊቴ ያለው ገመድ፣የተንጠለጠለው፤
ከደቂቃ ኋላ የምሰቀልበት
ለሰርጋችን ነበር፣ በሬ የሚሳብበት
ለድግስ ለሰርጉ. ስለሌለሽ በህይወት
ገመዱን ብቻ ነው ተስፋ ያደረኩት፡፡
መ
ጣ
ሁ
!
2 Comments
የታሻላ መረጀ
አቤት ግጥም ውውውውውው