ባሌን እንዲህ እፍፍፍ ያስደረገችውን ሴት ለማየት “የተለመደ” ቦታቸው ባሌን ተከተልኩት። ከስራ እኔን እቤት ካደረሰ በኋላ ነው የወጣው። የጀበኛ ቡና የሚሸጥበት ቤት? ይሄ ነው የተለመደ ቦታቸው? መኪናውን አቁሞ ወረደ። ታክሲውን አስቁሜ በዓይኔ ተከተልኩት።
ከተቃራኒ አቅጣጫ እየመጣች ከነበረች ሴት ጋር በፈገግታ ተጠባበቁ። የሚሉት አይሰማኝም። ተንጠለጠለችበት። ወገቧን ይዞ ወደላይ ተሸከማት። አነሳት አይደል? አዎ በትክክል! እግሮቿን አንጨፍርራ ተንጠለጠለችበትኮ! ምን ዓይነቷ ቀለብላባ ናት? ለወትሮ እሱስ ቢሆን ቅልብልብ ሴት አይወድም አልነበር እንዴ?
ሁለት ቀን ነው ያልተገናኙት ምንድነው ባህር አቋርጠው ከርመው የሚመጡ የሚያስመስሉት? ወደመሬት ከመለሳት በኋላ ሳመችው። ከንፈሩን ሳመችው። እጅ ለእጅ ተቋልፈው ትንሿ የጀበና ቡና መሸጫ ቤት ውስጥ ገቡ።
ይሄ ሁሉ አልጎረበጠኝም። ባሌ ማመንዘሩን ማረጋገጤ ደስ ብሎኛልኮ! ደስታዬን ምን ሸረፈው ታድያ? ቆንጆ ናት! የባሌ ወሽማ ቆንጆ ናት! የባሌ ወሽማ ባትሆን ኖሮ መንገድ ባገኛት “ስታምሪኮ!” የምላት ዓይነት ቆንጆ ናት
የባል ወሽማ ቆንጆ ስትሆን ደስ የማይል ስሜት አለው። 😜
“እዚህ ነው የምትወርጂው? ምንድነው?” ሲለኝ ባለታክሲው እንደመባነን አደረገኝ። የእናቴን ቤት አድራሻ ሰጠሁት።
“እማ ባሌ ከሌላ ሴት ጋር ግንኙነት አለው!” አልኳት አባዬ እስኪወጣ የባጥ የቆጡን ስቀባጥር ቆይቼ
“እርግጠኛ ነሽ?”
“አዎን ”
“በይ ስሚኝ ልጄ ሴት ልጅ የተለየች የሚያደርጋት ብልሃትዋ ነው። ባልሽን ልቡ ወደቤቱ የሚመለስበትን ጥበብ ዘይጂ ..” አላስጨረስኳትም!
“እህህ እማ ….አጥፍቼም የኔ ሃላፊነት ነው! አጥፍቶም የኔ ሀላፊነት ነው? ምንም አልገባኝም! የቱ ነው የሚያሳስብሽ? የኔ ያለባል መቅረት ነው የሚያሳስብሽ ወይስ የኔ ደስተኛ መሆን? እኔ ስለሚሰማኝ ስሜት አንድም ቀን ግድ ሰጥቶሽ አያውቅም። ግድ የሚሰጥሽ ትዳር ውስጥ መቆየቴ ብቻ ነው!! እየኖርሽ ካልሆነ በትዳር መኖር ትርጉሙ ምንድነው? ”
“አይ ልጄ እኔና አባትሽ 40 ዓመት በትዳር ስንቆይ ለመለያየት ምክንያት የሚሆን ፈተና ስላልገጠመን ይመስልሻል? በብልሃትና በትዕግስት አልፈነው ነው”
“እማ እስኪ ዛሬ እንኳን በጭንቅላትሽ ሳይሆን በልብሽ ስሚኝ? ደስተኛ አይደለሁም እኮ ነው የምልሽ! ሌላ ሴት ጋር ሲሄድ የመገላገል ስሜት ነው የተሰማኝ! የኔ ደስተኛ መሆን አያሳስብሽም? ”
ዝም አለች! ደነገጠች። ለወትሮው የምትለው የማታጣው እናቴ ዝም አለች።
“እሺ ትዳርሽን አስመልክቶ እንዲህ አድርጊ እንዲህ አታድርጊ አልልሽም። አንድ ልጄ ነሽ! ከምንም በላይ ደስታሽ ያሳስበኛል። ደስታ ግን አንቺ እንደምትዪው ባል ወይም ሌላ ሰው የሚሰጥሽ ነገር አይደለም። ደስታን ውስጥሽ ፈልጊው። የቱጋ እንዳጣሽው አስቢና። ፍለጋሽን ከዛ ጀምሪ!” አለችኝ በመጨረሻ! አልገባኝም! ወይም እንዲገባኝ አልፈለግኩም።
“ተይው በቃ ሲጀመርም ላንቺ መንገር አልነበረብኝም!” ብያት ወደቤቴ ተመለስኩ። ስደርስ ባሌ እቤት ነበረ። እኚህ ደግሞ እንደዛ ሲንጠላጠሉ ሁለት ቀን የሚበቃቸው አይመስሉምኮ ለሁለት ሰዓት ነው እንዲያ ሚመሳቀሉት?
“የት ሄደሽ ነው? የምትሄጂበት ቦታ እንዳለሽ ባውቅኮ አደርስሽ ነበር።” አለኝ
“እናቴጋ ሄጄ ነው” አልኩት ከንፈሬን ሊስመኝ ሲጠጋ ጉንጬን አቀብዬው
“ምነው ደህና አይደለሽም? ”
“እናቴጋ ለመሄድ የሆነ ነገር መሆን አለብኝ? ”
“ከዓመት በዓል ውጪ እናትሽጋ የምትሄጂው ሲከፋሽ ነው ብዬ ነው።” (ነግሬው አውቃለሁ? አላውቅም! እኔ ራሴ ያስተዋልኩት አሁን እሱ ሲለኝ ነው። በምን አወቀ?) ዝም አልኩ። ምንም እንዳልተፈጠረ እራት ያሰናዳልኝ ገባ! የእውነቱን ነው? እንዴት ነው እየበደለም እየተበደለም ያው ራሱ ሰውዬ መሆን የሚችልበት? ነውስ እሱም እንደእኔ እኩል ለኩል ነን ብሎ ነው የሚያስበው?
“እኔ በልቻለሁ” አልኩት። …..ብቻውን በላ
“ደክሞኛል ዛሬ!” ብዬ የጀመርነውን ተከታታይ ፊልም ሳላይ ወደመኝታ ቤት ገባሁ። እኔ ካላየሁ እንደማይቀጥለው አውቃለሁ። ተከትሎኝ ወደአልጋ መጣ። ጀርባዬን ሰጥቼው ትንፋሼን ሰብስቤ አንሶላውን ገልጦ ሲገባ ሰማዋለሁ። ከጀርባዬ አቀፈኝ። አንገቴ ስር በስሱ ሳመኝ። ሁሌም እንደሚያደርገው አንድ እግሩን ታፋዬ ላይ ጭኖ እጆቹን በጡቶቼ ዙሪያ አቆላልፎ አቅፎኝ ተኛ። 1 ደቂቃ …….2 ደቂቃ ……3 ……5 ……10 …..20 … ተኝቷል።
ዛሬ ምን ተገኝቶ ነው ያልነካካኸኝ ይባላል?