Tidarfelagi.com

ባሌ እንዳመነዘረብኝ ባወቅኩ ጊዜ… (ክፍል ስድስት)

“እስክትወስን እጠብቃታለሁ።” ይለኛል። ሁሌም የምንገናኝበት ቦታችን ‘የምናውራው አለ’ ብሎኝ ተገናኝተኝ የጀበና ቡናችንን እየጠጣን።

“እኔስ? በፍቅርህ የነሆለለ ጅል ልቤስ? ምን ላድርገው? እስከመቼ ጠብቅ ልበለው? ከሚስቱ እስኪታረቅ ልበለው እስኪለያይ? ንገረኝ የቱን ነው የምጠብቀው?” እንባዬ የአይኔን ድንበር አልፎ ተንዠቀዠቀ። ይሄን ያልኩት ብዙ ስለሷ እና ስላወሩት ከነገረኝ በኋላ ነው።

ሚስት ያለው ሰው ወድጄ ለምን ታረቁ የማለት መብት አለኝ? እሱስ የጠላችው ሲመስለው እኔጋ የወደደችው ሲመስለው እሷጋ እየሄደ በልቤ የመቀለድ መብት አለው? ማናችን ነን ልክ? ወይስ ማናችን ነን ትንሽ የተሳሳትን?

የሆነ ቀን እዝችው ቤት ቁጭ ብለን የተሰነጣጠቀ ስኒ ረከቦቱ ላይ አይቼ ተነስቼ አመጣሁት። አሳየሁት።

“ይሄን ስኒ አየኸው ውዴ ብዙ ተሰነጣጥቋል። ግን አልፈረሰም። አንዴ ብቻ ቢወድቅ ግን ይፈረካከሳል።” ብዬው ስኒውን ለቀቅኩት እንክትክቱ ወጣ። “የኔ ልብ ይሄ ስኒ እንደነበረው ነው። የምታነካክተው ከሆነ ከነስብራቱ ይቆይ ተወው።” ብዬው ነበር። የዛን ቀን ነው ለመጀመሪያ ጊዜ የሳመኝ። አልሰብረውም እጠብቀዋለሁ እንደማለት ያለ መሳም።

ከቀናት በፊት
“ለሚስቴ ካንቺጋር ያለኝን ነገር ልነግራት ወስኛለሁ። ከርሷ ጋር ያለኝኝ ነገር ጨርሼ ልምጣልሽ። እያደረግነው ያለነው ነገር ልክ አይደለም። ካንቺ ጋር ቆይቼ እቤት ስገባ ልፈነዳ ነው የምደርሰው።” አለኝ።

ዛሬ መጥቶ
“እስክትወስን እጠብቃታለሁ።” ይለኛል። ከቃሉ ይልቅ ውሳኔዋ መመለስ(አብሮ መኖር) እንዲሆን ተስፋ ማድረጉ። ለማሰብ መዘጋጀቷ እንዴት እንዳስቦረቀው ሳየው ልቤ ደረቴ ስር እንደዛ ስኒ እንክት ስትል ታወቀኝ። ተነስቼ ሮጥኩ። እየጠራኝ ተከተለኝ። ሮጥኩ ታክሲ እስካገኝ ሮጥኩ።
“አየህልኝ? ካልጠፋ ሰው ….ካልጠፋ ወንድ ባለትዳር? ‘አላገባም! ካሁን በኋላ መውደድ አልችልም’ ስልህ …….’ጊዜ ሀዘንሽን ያደበዝዘዋል። … የሆነ ቀን የሆነ ሰው ወደ ህይወትሽ ይመጣል። … ልብሽ ተሰብሮ እንደነበር ያስረሳሻል። …. ትወጃለሽ። ልብሽ እንደገና ሙሉ ይሆናል። ..’ ያልከኝ። ”

ሆስፒታል አልጋ ላይ ከተኛ ወራት ላለፉት ይስማኝ አይስማኝ እርግጠኛ ላልሆንኩት አባቴ ነው የምለፈልፈው።
“መጣ! … ያ ሰው ወደ ህይወቴ መጣ … ወደድኩት። …. ባለትዳር ነው አባ! … ይሄን ዘመን ሁሉ ቆይቼ ካልጠፋ ሰው ልቤን የሰጠሁት የሚወዳት ሚስት ላለችው ሰው ነው። … አንተ እንዳልከኝ ልቤን ሙሉ አላደረገውም። አነከተው።” ተንፈቀፈቅኩ።
በራሴ ተናደድኩ። በፈጣሪ ተናደድኩ። በዓለም ተናደድኩ። በማላውቃት ሚስቱ ተበሳጨሁ። በሱ በራሱ ተናደድኩ። በአባዬም ስለማይሰማኝ ስለማያባብለኝ ተናደድኩ። ለሁሉም መልሴ እናባ ነው። ከአንጀቴ እየተሳበ የሚያንፈቀፍቀኝ እንባ።

“ለምን እንድወደው አደረገኝ? ሳለቅስኮ ነው ያገኘኝ? እንባዬን ጠርጎ አባብሎኝኮ ነው የተዋወቀኝ …… አላሳዝነውም? …. እዛው እንባዬ ላይ መልሶኝ ይሄዳል?”

የህፃናት ማጫወቻ ቦታ ልጄን እያጫወትኩ ነበር።
“እማ እዛኛው ላይ መጫወት እፈልጋለሁ?” አለኝ ልጄ መጥቶ
“ባባዬ እኔኮ ከፍታ ያመኛል።” አልኩት የከፍታ ፍርሃቴን ለ6 ዓመት ልጄ ማስረዳት እየቸገረኝ። ቀና ብዬ መጫወቻው ላይ ልጆቹን አየኋቸው። አብዛኛዎቹ ከአባታቸው ጋር ነው መጫወቻ ላይ የወጡት ። ጉድለቴን ሊነግሩኝ …… የልጄ አባት ምን ያህል እንዳጎደለኝ ሹክ ሲሉኝ ….. እንባዬ አይኔን ሞልቶ ደፈራረሰ።

“ይቅር በቃ ሌላ ጨዋታ እጫወታለሁ።” አለኝ የኔ የልጅ አዋቂ ጭንቀቴ ገብቶት።

“እኔ ይዤልሽ ልውጣ?” አለኝ የሚያባብል ድምፅ ከጀርባዬ …….. እሱ ነበር። ምንድነው የሆንኩት? የተሰማኝን ያወቀልኝ መሰለኝ። ውስጤ ያለውን የሰማኝ። አዎ ማለት አቃተኝ። በጭንቅላቴ ንቅናቄ እየነገርኩት እንባዬ ተከታተለ። ልጄ እንዳያየኝ እያቻኮለ ብድግ አድርጎ ትከሻው ላይ ሰቅሎት ይዞት ሄደ። ተንፈቀፈቅኩ።

“ከሞተ አራት ዓመቱ ነው።” አልኩት ሳይጠይቀኝ። “እንዴት ነው የማይመለስን ሰው መጠበቅ ማቆም የሚቻለው? እንዴት አድርጌ ነው መናፈቅ ማቆም የምችለው። እንዴት ነው ከርሱ ውጪ ህይወቴን መቀጠል የምለምደው? ” እያልኩት እነፋረቅ ጀመር። አባበለኝ። እንደህፃን አባበለኝ። … ብዙ ጊዜ እንደሚያውቀኝ። …. … አልቃሻ ብሆንም ለማላውቀው ሰው አላለቅስም ነበር። እሱ ግን ባልገባኝ ምክንያት ቀለለኝ።

“የታል ያንተ ልጅ?” አልኩት
“ብቻዬን ነው የመጣሁት። ልጅ የለኝም ከነጭራሹ ….. ህም …. መውለድም አልችልም።” አለኝ መተንፈስ የፈለገ ይመስል ነበር። ልጄ እየተጫወተ እኔና እሱ ብዙ አወራን።

“ሚስቴ ትጠላኛለች። ልጅ ልሰጣት ስለማልችል ትጠላኛለች። …..ልጅ መውለድ እንደማልችል ሳልነግራት ስላገባኋት ትጠላኛለች። ….ለምን እዚህ እንደምመጣም አላውቅም። …..ልጆች ሲጫወቱ አይቼ እመለሳሉሁ። ” እያለ ዝብርቅ ያለ ወሬ አወራኝ።

እዚህ ቀን ላይ ነው የመለሰኝ። ለቅሶዬ ላይ። እሱን ካወቅኩት በኃላ አላለቀስኩም ነበራ። …

“እዚህ ነሽ እንዴ?” እያለች ታላቅ እህቴ ወደአባዬ ክፍል ስትገባ እየተነፋረቅኩ እንደሆነ አየችኝ።
በሩን ዘግታ የአባዬ አልጋ ጠርዝ ላይ እየተቀመጠች። ያለኝን ነገርኳት።

“ያንቺ ካለውኮ ተመልሶ ይመጣል።” አለችኝ።
የምትለው ግራ ገብቷት እንጂ ያለችው ምን ማለት እንደሆነ አልመነዘረችውም።

ለኔ ካለው? ለኔ ካለው አማራጩ እሆናለሁ። የመጀመሪያ ምርጫው እሷ ናት። እሷን ካጣ እኔጋ ይመለሳል? ለኔ ካለው ትርጉሙ ይሄ አይደል? ለኔ እንዲለው እሷ እንድትጠላው ቁጭ ብሎ መመኘት? ለኔ ካለው እንዲፋቱ መፀለይ? ትርጉሙ ይሄ አይደል? ቢለያዩና በቃ ጨርሻለሁ ብሎኝ ቢመጣ ስለወደደኝ ነው ወይስ አማራጭ ስላጣ ብዬ የምቀበለው?….. ለኔ ካለው የሚባል ነገር ምንድነው? እጣዬ ከሆነ ማለት ነው?

ከወራት በፊት የህፃናት መጫወቻው ቦታ ስንለያይ ስልክ ሳንለዋወጥ … ስማችንን እንኳን ሳንተዋወቅ ቻው የተባባልን ሰዎች ከሱቄ ባሻግር ያለ የጀበና ቡና መጠጫ ቤት ቁጭ ብዬ ቡና ስጠጣ ሲገባ ሳየው … እንደዛ አስቤ ነበር። ምናልባት እጣ ፈንታ ነው። ተዋወቅን … አወራን .. በተደጋጋሚ ቡና ጠጣን…. የሆነ ቀን እኔም ስለባሌ እሱም ስለሚስቱ ማውራት ትተን ስለራሳችን ስናወራ ራሳችንን አገኘነው። ….

ምኑጋ ነው የወደድኩት? ምኑጋ ነው ልቤን የከፈትኩት? ልክ እንዳይደለ አውቅ አልነበር? እያወቅኩ የቱጋ ነው የተረታሁት?
……… …… እንክትክት ያለ ነሆለል ልቤን ከየት ወዴት ልሰብስበው? ሚስቱን ፈቶ እስኪመጣ ጠብቅ ልበለው?

ክፍል ሰባት

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...