Tidarfelagi.com

በውቄ እንዴት እንደተፈነከተ!

አባቴ በጣም ትግስተኛና ደመበራድ ስለሆነ ባመት አንድ ቀን ቢናደድ ነው፤ የተናደደ ቀን ግን ምድር አትበቃውም፤ ከደመኞቹ ጋር ሲደባደብ ጣልቃ የገቡ ገላጋዮች “እጁ ላይ ሰው አይበረክትም” እያሉ ያደንቁት ሰምቻለሁ፤

ዘጠነኛ ክፍል እያለሁ፤ በገና በዐል ዋዜማ፤አባየ ከባለንጀራው፤ ከጋሽ ፋኑኤል ጋር አንድ ሁለት ብለው ወደ ቤት ሲመለሱ ተነቁዋቆሩ፤ አባየ የሆነ ጊዜ ላይ ፤የጉዋደኛው ነቆራ ክብረነክ ሆኖ ስላገኘው ደሙ ፈላ፤ደሙ ፈልቶም አልቀረ፤እጁን ቀለል አርጎ ሰነዘረ፤ ዝንብ ለማባረር የፈለገ ይመስል አይበሉባውን ወንጨፍ አደረገ ማለት ይሻላል፤ ያባቴ መዳፍ፤ ታጥሮ የኖረ ያላሙዲን መሬት በሚመስለው የጋሽ ፋኑኤል ፊት ላይ ሲያርፍ የተሰማው ድምፅ የወጨፎ ድምፅ ያስንቃል ፤ ጋሽ ፋኑኤል በራሱ ዛቢያ ላይ ትንሽ ሲሽከረከር ከቆየ፤ በሁዋላ ነፋስ እንደነካው ያሜሪካ ዛፍ ተገርስሶ ወደቀ፤ አይ አባየ ! አንበሳ እኮ ነው!

አባታችን እቤት እንደተመለሰ፤ ጋሽ ፋኑኤልን ባመርቂ ሁኔታ እንደደበደበው ለናቴ አበሰራትና ኮቱን አውልቆ የሰርጋቸው ፎቶ አጠገብ ሰቀለው፤ከዚያ በርካታ ተንፍሶ አልጋው ላይ ጋደም አለ፤ እናታችን እና እኛ ልጆች፤ቀጥሎ የሚመጣውን የመልስ ምት በማሰብ ፤ በጭንቀት መንቆራጠጥ ጀመርን፤ ብዙ አልቆየንም፤ የቤታችን ጣርያ ድውውውው ሲል ሰማን፤ የብራ መብረቅ ወይም ደብተራ የወረወረው አንደርቢ አልነበረም የወደቀብን፤ የጋሽ ፋኑኤል ጎረምሳ ልጅ የወረወረው ሚሳይል የሚያስንቅ ድንጋይ ነው፡

አባየ “ይቺን ይወዳል” ብሎ ካልጋው ተፈናጥሮ ተነሳ፤(ባልጋው እና በቁምሳጥኑ መሀል አክሮባት ሰርቶ ተነሳ ብል ማንም አያምነኝም ብየ ነው) ፤ ወድያው፤ ባልጋው ራስጌ የሚያስቀምጠውን ከቡዋንቡዋ ውጅሞ የተሰራ ከዘራውን መዞ ወደ በሩ ሲሄድ እናቴ ልታስቆመው ሞክራ ነበር፤ ገፍትሩዋት ወጣ፤

እናቴ ባንድ በኩል የልጆችዋን አባት ወደ አደጋ ሲሄድ ስታይ ሰግታለች፤ ባንድ በኩል ጀግነቱን ስላሳያት ኩራት ተስምቱዋታል፤ በኩራትና በስጋት የተሞሉ አይኖቹዋን ስታዞር ጥግ ላይ ቆሜ ሳመነታ አየችኝ፤ “አባትህን ተከተል” የሚል ምልክት አሳየችኝ፤ ወይ ሌሊቴ! ምነው ባልተፈጠርኩ! ከተፈጠርኩ እንኩዋ ምነው የዚያን ቀን የክርስትና አባቴን ጥየቃ ወደ ገጠር ሂጄ ባደርሁ! ፤ቡካቴን በልቤ ይዤ፤ ደፋርና ፤ያባቴ መከታ መስየ ለመታየት ሞከርኩ፤ የጀጠባቤን እጅጌ በዝግታ ስሰበስብ ለክትባት እንጂ ለጠብ የምዘጋጅ አልመስልም፤ ለምሳር እጄታነት የታጨ ዱላ በረንዳ ላይ ወድቆ ስላገኘሁ፤አንስቼ አባቴን እያመነታሁ ተከተልኩት፤ በጥሞና ለተመለከተኝ ሰው፤ ጌታውን የተከተለ ኣዝማሪ እንጂ ጋሻ ጃግሬ አልመስልም፤ የዱላ አያያዜ ራሱ እንደ ማሲንቆ ነው፤

አባቴ የድመኛው ቤት አጥር ላይ እንደ ደረሰ፤ ቆም አለና የቆርቆሮ አጥሩን በር በከዘራው ይወቃው ጀመር፤ ፊቱ ላይ ያለውን መረጋጋት ለተመለከተ፤ የገጠር ቤተክስያን ደወል የሚደውል እንጂ የሰው ቤት አጥር የሚደበድብ አይመስልም፤

የጋሽ ፋኑኤል ትንንሽ ልጆች ከግቢ ሆነው የሚወረውሩት ድንጋይ አባቴን ለጥቂት እየሳተ እኔ አጠገብ ይወድቃል፤ ለማፈግፈግ መንገድ ባይኔ ሳማርጥ ከጀርባየ ኮቴ ሰማሁ፤ዞርሁ፤ የጋሽ ፋኑኤል ጎረምሳ ልጅ ፊት ከጨለማው ውስጥ እየተመዘዘ ሲወጣ እንደ ህልም ትዝ ይለኛል፤በርግጥ፤ በዱላ ነው የመታኝ ወይስ በሲኖትራክ ነው የገጨኝ የሚለውን እስካሁን ርግጠኛ አይደለሁም፤

በማግስቱ ፤ የገና ፍሪዳ ተጥሎ፤ የሰፈራችን አባዎራዎችና እማዎራዎች አለማቸውን ያያሉ፤ እኔ ፤እንደ አሮጌ ብር ፊቴ በፕላስተር ተሞልቶ፤ በየማእዘኑ ቆስየ፤ የታከመ እንስራ መስየ፤ የቅርጫ ዘንቢሌን አንጠልጥየ ፤ አሻግሬ ስሾፍ፤አባቴ እና ጋሽ ፋኑኤል፤ እየተሳሳቁ ጥሬ ስጋ ሲጎራረሱ አየሁዋቸው፤

ይህን አስተካዥ ገጠመኝ ያነሳሁት ምን ለማስተላለፍ ነው?🙂

ሰሞኑን ራሳቸውን የህዝብ አለቃ አድርገው የሾሙ አለቆች ፤ በየሚድያው ጎራ ለይተው በቃል ሲደባደቡ ሳይ ትዝ የሚለኝ ይሄ ገጠመኝ ነው፤እነሱ ዛሬ፤ ለግል ክብራቸውና ለግል ብራቸው ተጣልተው ነገ ባንድ መድረክ ላይ ይተቃቀፋሉ፤ ሰፊው ህዝብ ሆይ ! እዳቸው እንጂ በረከታቸው በማይደርስህ ልሂቃን አምባጉዋሮ ከመሳተፍ ተቆጥበህ በሰላም እንድትኖር እመኝልሃለሁ፤

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...