Tidarfelagi.com

‹‹በኤንጂኦ ስብሰባ ላይ ብልህና አርቆ አሳቢ የመምሰል ጥበብ ….››

 

ትላንት ዘ ጋርዲያን ላይ ከወጣ የከረመ አንድ ፅሁፍ ሳነብ ሁሌም የሚያስቀኝ፣ የሚያሳዝነኝ እና የሚያስገርመኝ ነገር ስለሆነ እሱን ተመርኩዤ በዚህ ጉዳይ ለምን አላወራም ብዬ አሰብኩ። ጌሪ ኦውን የጻፈው የጋርዲያኑ ፅሁፍ ርእስ 10 tricks to appear intelligent during development meetings ይሰኛል። እኛ ደግሞ ምን እንበለው….? በኤንጂኦ ስብሰባ ላይ ብልህና አርቆ አሳቢ የመምሰል ጥበብ ….?

እንግዲህ የትም እንደሚደረግ ብዙ ስብሰባ፣ የኤንጂኦ ስብሰባ በተለይ ብዙ ኤንጂኦዎች በህብረት ሆነው የሚገናኙበት ከሆነ አብዛኛውን ጊዜ ጉንጭ አልፋ፣ ከአንገት በላይና ፍሬ አልባ ነው።

ይሄን የሚታደሙ ሁሉ ያውቁታል፤ ግን ይመጣሉ። ይመስላሉ። ያስመስላሉ። ይበተናሉ። ደግሞ በሚቀጥለው ለዚህ ሊሰበር ላልቻለ የስብሰባ አዙሪት መለሰው ይሰበሰባሉ።

ከአብዛኛዎቹ የኤንጂኦ ስብሰባዎች መመሳሰልና ውጤት አልባነት የተነሳ ብዙ ሰዎች እጃቸውን አውጥተው በስሜት እየተወዘወዙ ሲያወሩ አይታዩም። ታላላቅ ፍልስፍና አዘል ክርክሮች አይካሄዱም።

የተለመዱት የኤንጂኦ ቃላት…እነ ታርጌት ቤኒፊሸሪ፣ እነ ቨልነረብል፣ እነ ኢንአክሰሰብል፣ ኤቪደንስ – ቤስድ፣ ኢምፓክት እና ኢንተርቬንሽን ኤሪያ፣ እነ ሰልፍ ኸልፕ ግሩፕ ከሁሉም ጥጎች እየተወረወሩ ከቆዩ በኃላ በፓወር ፖይንት ፕረዘንቴሽን የስራ ስሜትና የመኖር ፍላጎት ሞቶ ወደ ቢሮ መመለስ ነው። ይሄው ነው።

በዚህ ሁሉ የተሰላቸ ህዝብ መሃል ግን ለመስኩ አዲስ የሆኑ እና በኤንጂኦ የእድገት መሰላል ላይ ለመወጣጣት እንዲረዳቸው የሚለፉ፣ ለስራው መሳካት ተአምር ይዘው የመጡ በመመምሰል የእነ ዩኤን ቺፍ ኦፕሬቲንግ ኦፊሰሮችን ወይ የአንዱን ኤንጂኦ ካንትሪ ዳይሬክተር ቀልብ ለመሳብ የሚቅለበለቡ አይጠፉም። እዩኝ እዩኝ፣ ስሙኝ ስሙኝ የሚያበዙ፣ ብልህና ልበ ቀና፣ ገራገርና የዋህ መስለው ታይተው ሰፊ እንጀራ ለመጋገር የሚሮጡ አይጠፉም።

እነዚህ ናቸው የኤንጂኦ ስብሰባ ላይ የሚከተሉትን በቅደም ተከተል ደረጃ የሚጠየቁ ወይ የሚነሱ ነጥብና ጥያቄዎችን በውድ ቦርሳቸው ሸክፈው የሚገቡት።
ከዚህ ውስጥ አስቂኙ ነገር ሁሉም በኤንጂኦ ስራ ጥርሱን የነቀለ፣ በኤንጂኦ የሚጦር ሰው ሁሉ እነዚህን የማምታቻ ቃላት፣ እነዚህን መስሎ የመታያ ጥያቄዎች ብጥር-ብጥርጥር አድርጎ ያውቃቸዋል። ግን ተራቸው ነው በማለት እሰኪብርቶውን እያፍተለተለ፣ ላፕቶፑ ላይ ምናምን እየቸከቸከ፣ ስልኩን እየጎረጎረ በማያውቅ እና ባልነቃ ሰው ዘዬ ዝም ብሎ ያያቸዋል፣ ይሰማቸዋል።

ለመሆኑ እነዚህ በኤንጂኦ ስብሰባ ላይ ብልህ ሆኖ ለመታየት የሚቀርቡ የማምታቻ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች የትኞቹ ናቸው?

1ኛ- ስለ ማይልስቶኖች መጠየቅ

ማይልስቶኖች የኤንጂኦ ስብሰባዎች ቁልፍ ቃላት ናቸው። የኤንጂኦ እቅድ ካለ ማይልስቶን አይመጣም። የኤንጂኦ ቸበርቻቻ ካለማይልስቶን ወሬ አይደምቅም። የኤንጂኦ ጆብ ኢንተርቪው ካለማይልስቶን ጥያቄ አያልቅም። አስቂኙ ነገር ግን አንዱን ኤንጂኦን አቅንቶ በኤንጂኦ የሚኖር ጎልማሳ ሰው ጠርታችሁ ማይልስቶን ምንድነው ብትሉት ሊገልፅላችሁ አለመቻሉ ነው። የሚባል እንጂ የማይገባ፣ የሚለፈለፍ እንጂ የማይሰርግ ቃል ነው -ማይልስቶን። ሆኖም በሁሉም ስብሰባ አሰፍስፈው በሚመጡ አዳዲስ የኤንጂኦ ተስፈኞች ስሙ ይነሳል። ይጣላል። ይበለታል።
ለምሳሌ እንዲህ ተብሎ ሊጠየቅ ይችላል
‹‹የፕሮጀክቱ እቅድ አሪፍ ነው…ግን ማይልስቶኖቹ የት አሉ? ማይልስቶኖቹ ግልፅ ሆነው ካልተቀመጡ እና ካሁኑ ካልተስማማንባቸው የምናስበው ኢምፓክት በቤኒፊሸሪዎቹ ላይ ሊመጣ አይችልም። በተለይ ቨልነረብል ለሆኑት ግሩፖች ክሊር ማይልስቶን ያስፈልጋል። ለምሳሌ ምን ያህል ሰልፍ ኸልፕ ግሩፖችን እስከመቼ ሴት አፕ እናደርጋለን የሚለው ኢምፖርታንት ነው…››

2ኛ- ‹‹ሰስተኔቢሊቲ››ን የስብሰባው ርዝመት በፈቀደው ልክ ደጋግሞ መጠቀም

ይሄም ልክ እንደማይልስቶኑ ነው። ከማይልስቶኑ ጥያቄ ጋርም በብርቱ ይያያዛል። በሚከተለው መልክም ሊቀርብ ይችላል።

‹‹ቅድም እንዳልኩት ማይልስቶኖቹ ግልፅ ሆነው ሲቀመጡ ነው ሰስቴነቢሊቲ ኢንሹር የምናደርገው። ሰስቴኒቢሊቲ ፕላንም ተያይዞ ሊሰራ ይገባል…ሃው ዱ ዊ ኢንሹር የምንሰራው ስራ ሰስቴነብል ሆኖ እኛ ስንወጣ ያለምንም ሂካፕ እንደሚቀጥል…ሰስተነቢሊቲ ኢዝ ክሪቲካል ለኢምፓክት….››

3ኛ- ጄንደር ኮምፖነንቱ የታለ?

ኤንጂኦ ስብሰባ ላይ (በተለይ ለጋሾች ያሉበት ከሆነ )የሚናገር ሰው ስለጄንደር ያለውን የጋለ ስሜት ካልገለጸ የትም አይደርስም። ይህንን ወሳኝ ጥያቄ በብዙ መልኩ ማንሳት ቢቻልም የሚከተለው ጥሩ ምሳሌ ነው

‹‹ጄንደር ኮምፖነንቱ አይታየኝም…ከጄንደር አንግል ጭራሹን አላያችሁትም ለማለት ይቻላል…ይሄ በጣም ያሳዝናል…የፍየል እርባታ በአርቴፊሻል ኢንሲሚኔሽ ስናደርግ ይሄ ሴቶቹን ፍየሎች እንዴት አፌክት ያደርጋል ብለን መጠየቅ አለብን….ከጄንደር ፐርሰፔክቲቭ ፓርቲሲፓቶሪ በሆነ መልኩ ልናየው ይገባል…አለዛ ቨልነረብል ግሩፖችን አይጠቅምም…እንዳውም አውትካስት ያደርጋል….ሰስቴነብል አይሆንም ኢምፓክትም አይኖረውም…››

4ኛ- ማንኛውንም አስተያየት <<ስለዚህ ፕሮጀክት ያሳሰቡኝ ብዙ ነገሮች አሉ… ይሄ ነገር ያስጨንቀኛል>>ብሎ መጀመር።

ይህቺ በባዶ ሜዳም ቢሆን ሁሌም የሁሉንም ሰው ቀልብ የምትስብ አጀማመር ናት። ለምሳሌ እንደሚከተለው መጠቀም ይቻላል…
‹‹ስለዚህ ፕሮጀክት የሚያስጨንቀኝ ምንድነው መሰላችሁ….በዚህ መልኩ በቂ ቨልነረብል ህጻናት እና እናቶች ጋር ልንደርስ አንችልም..››
‹‹የፉድ ዲስትሪቢውሽን ፕላኑ ብዙ ሁኔታዎችን ኮንሲደር አላደረገም የሚል ስጋት አለኝ…በተለይ ጄንደር ኮምፖነንቱ ማይልድ ነው…››
‹‹ይሄ ፕሮጀክት እንዴት ሰስቴነብል በሆነ ኮንዲሽን ኢምፕሊመንት ይደረጋል የሚለው ያስጨንቀኛል››

5ኛ- ‹‹ለፎሎው አፕ ታስክ ፎርስ እናቋቁም›› ብሎ መወትወት

ይቺ የሁሉም ረጅም ኤንጂኦ ስብሰባ መደምደሚያ ብትሆንም ታስክ ፎርስ ሴት አፕ ይደረግ ብለህ ስትጠይቅ ግን ለስራው ያለህን ሲሪየስነስ ማሳያ መንገድ ስለሆነ ሰዎች ሁሉ ይደነቁብሃል…ይሄን የምትለው ስብሰባውን ቶሎ ጨርሶ ለመገላገል እንደሆነ እና እዚህ ታስክ ፎርስ ስብሰባ ላይ በተደራራቢ የጉዞ ፕሮግራሞች፣ የፊልድ ትሪፖች ምክንያት መገኘት ላለመቻል እንደወሰንክ ማንም አያውቅም…ቢያውቅም ግድ የለውም …

6ኛ- ‹‹ፊልድ ትሪፕ አለብኝ›› ብሎ ስብሰባው ሳያልቅ እየተጣደፉ መውጣት

ፊልድ አለብኝ ብሎ መውጣት ከአሰልቺ እና ዘልዛላ የኤንጂኦ ስብሰባ የማምለጫ ብቸኛው አማራጭ ባይሆንም ተቀባይነቱ ግን አቻ የለውም። ቁርስ ስላልበላሁ ምናምን ቀምሼ ልምጣ፣ ስብሰባ አለብኝ፣ አስቸኳይ ስራ ገጠመኝ ማለት ቢቻልም ፊልድ ልሄድ ነው ማለት ግን ወደ ቨልነረብል ቤኒፊሸሪስ ሄጄ ልረዳቸው ነውና አታቁሙኝ እንደማለት ስለሆነ ማንም አያኮርፍም። ማንም አይነጫነጭም…ሂድ ..ሂጅ ማለት እንጂ ክፉ ቃል አይወጣውም…ፊልድ ትሪፕ ሄጃለሁ ባልክ ቀን ሰአት በኋላ ስብሰባው ውስጥ ከነበሩት ሰዎች ጋር ጋርደን ኦፍ ኮፊ ቺል ስታደርግ ብትገናኝ እንኳን በፍፁም አትፈር…ለምን ቢባል ፊልድ ቪዚቱ በፀጥታ ችግር ምክንያት መሰረዙን መናገር ትችላለህና…

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...