Tidarfelagi.com

በአልጋው ትክክል (ክፍል አራት )

አንዲት መልከመልካም ነርስ ነበረች እየተመላለሰች የምትንከባከበኝ … ከስራዋ በተጨማሪ በመጣች ቁጥር የምታገኛቸው ወጣት ጓደኞቸ ጋር አንድ ሁለት ቃላት (አለ አይደል እንደማሽኮርመም የሚያደርጉ) ስለምትወራወር የእኔን ክፍል ከስራ ቦታነት በተጨማሪ እንደመዝናኛ ቦታ ሳታያት አልቀረችም … ታዲያ ይች ነርስ እናቴም ጋር ከመግባባቷ ብዛት በቬርሙዝ የመጣ ቡና ሁሉ ካልጠጣሽ ብላ ስትለምናት ነበር ….አንድ ቀልቡ ያረፈባት የስራ ባልደረባየ ታዲያ ከእናቴ አፍ ላፍ አድርጎ እንዲህ አለ ‹‹ማዙ ተያት ስንወጣ እኔ እጋብዛታለሁ›› የኔ የዋህ እናት በአንድ እጇ ቬርሙዝ በአንድ እጇ የቡና ስኒ እንደያዘች ‹‹ይሻላል ?…እሽ እንዳትረሳ ባይሆን ….ጥሩ ልጅ ናት አደራህን ጋብዝልኝ ›› ትልልኛለቻ … ነርስየ ከሳቅ ጋር እሽኩርምም ….በለው ! በኔ ውድቀት ግማሹ ጀግንነቱን ሲያሳይ ….ግማሹ ነርስ ሲያሽኮረምም …ተኝቸ አያለሁ ! እናቴ …ጠያቂውን እያስተናገደች … ሰው ጋፕ ሲል ትመክረኛለች ‹‹ አቡቹ ጀግና ማለት ደረቱን ነፍቶ ችግር ላይ የሚጣድ አይደለም …. አዎ ጀግና ማለት የሚፈራበትን ጊዜ የሚየውቅ ነው ››

በነገራችን ላይ ነርሷን የሚያሽኮረምመው ታዲዮስ ነው …ታዲዮስን ታውቁት የለ ? …የሆነች ትንሽ መኪና ያለችው የስራ ባልደረባየ ብየ የነገርኳችሁ …እንደውም የሆነ ጊዜ አንድ መኪና መንገድ ይዘጋበትና በብስጭት እጁን በመስኮት አውጥቶ አጉል የብልግና ምልክት መንገዱን ለዘጋበት መኪና ሹፌር ያሳያል ….ወዲያው ስልኩ ውስጥ ‹ቴክስት› ሲገባ ሰማ… ከፍቶ ሲመለከት ‹‹ጣትህን ይቁረጠው ስድ ዘልዛላ አሳዳጊ የበደለህ ›› የሚል እርግማን … መኪናው ፈጠን ብሎ ከጎኑ ሲቆም በመስኮቱ ቀና ብሎ ያያል አዲስ የጠበሳት ልጅ አባት ናቸው …ደግሞ ለክፋቱ እሷም ከጎናቸው ቁጭ ብላለች….ቀይ ፊቷ እሳት ለብሶ …‹‹እና ምን አደረክ›› ስንለው …እንዲህ አለን ‹‹ነዳጁን ሰጠ……ሁት›› በቃ!! ይባስ ብሎ ይሄን እየነገረኝ የእኔ ስልክም ውስጥ ቴክስት ገባ እንዲህ ይላል ‹‹አንድ አይነት ክንፍ ያላቸው ወፎች በአንድ ላይ ይበራሉ›› የታዲዮስ ፍቅረኛ ናት ! ያሰድበን ምናለ … ከዛ በኋላ ልጅት ጋር አይንና ናጫ ሆኑ !! እንግዲህ ለዛች ወፍ እግር ጓደኛው አሰደበኝ…. አሁን ደግሞ በስርዓት እንዳታስታምመኝ ይሄው ይችን ነርስ ልቧን ያጠፋልኛል ! እሷም ቀልቧ ሳይከጅለው አልቀረም … እግዜር ይጠብቀኝ እንግዲህ ለሌላ የታዘዘ መርፌ …

ወንድየ አንበሳው በቢለዋ ከወጋኝ ዛሬ ሰባት ቀን ሞላኝ …. ጥሩ ጤንነት ቢሰማኝም ዶክተሩ መራመድና መንቀሳቀስ የለብህብም ብሎ ሆስፒታል አልጋ ላይ እንዳጣበቀኝ አለሁ ! ላይጠግን አይሰብርም እንዲሉ ሰባትኑም ቀን ል እ ል ት ሰባተኛው ሰማይ ድረስ መዓዛው የሚያውድ ሾርባ እያመጣች(የጠላቴን ገንዘብ ከወዳጀ እጅ ፉት እያልኩት እንደማለት) እንዲሁም እኔን ራሴን በደስታ ሰባተኛው ሰማይ የሚያደርስ ፈገግታዋን ይዛ እየመጣች አስታመመችኝ … እንግዲህ እግዜሩ ባልን ወጊ ሚስትን አስታማሚ አድርጎ ሲሰጥ ቁስሉም የውሻ ቁስል ይሆናል መሰል ቶሎ ደረቀ !!(በነገራችን ላይ ያች እማማ ቁንጥሬ መቸለታ ነው መጡና አፋቸውን ሸርመም አድርገው ‹የውሻ ቁስል ቶሎ ይድናል ›› ብለው ሄዱ ….እናቴ ምርቃት መስሏት ‹‹አሚን›› አለች እኔ ግን ቅኔዋ ገብታኛላች …የሰው ሚስት ጋር የምትልከሰከስ ውሻ ማለታቸው ነው …ከምር ነቅቻለሁ …እና ‹‹የውሻ ቁስል ያድርግልህ›› እንጅ ‹‹የውሻ ቁስል ቶሎ ይድናል ›› ይባላል ? ደግነቱ እንደገና ትላንት መጥተው ማዘርን ቀልቧን ገፈፏት …ከምር ጠላቻቸው …!!
‹‹ማነህ አቡቹ ተሻለኝ ብለህ እንዳትንቀለቀል… ይሄ የቻይና ቢላ ለሌላ ነገር ሲሉት አይነቃም እንጅ ሰው ላይ ሲያርፍ መርዝ ነው …›› አሉ
‹‹እንዴት ማለት እማማ ›› አለች እናቴ ተጨንቃ››
አፋቸውን ጠራርገው ለወሬ ተዘጋጁና ‹‹እንዴት ማለት መልካም ….የዛሬ አመት እዚህ ቢሸፍቱ የሚኖር አንድ የአጎቴ ልጅ እንዲህ እንዳንተ በቢላ ተወግቶ ….እሱ እንኳን በሴት ተጣልቶ አይደለም …ዘራፊዎች ናቸው ..(እዩልኝ ይችን እሾህ የሆኑ ሴት)….. እና ዳንኩ ብሎ ፈንጠር ፈንጠር ሲል …. ምን የመሰለ ሸበላ በዲብሎማ ከተመረቀ ገና መንፈቅ ያልሆነው ልጅ አጣጥሞ እንኳን ደሞዙን ሳይበላ … ቁስሉ አመርቅዞ ገደለው›› አላሉም?! ….እናቴ ፊቷ ተቀያየረ …ወጣ ሲሉ ገና በብስጭት እየተብከነከነች ብቻዋን ማውራት ጀመረች ‹‹ምን ያሉት ክፉ ናቸው …የታመመ ሰው ፊት እንዲህ ይባላል?›› ብላ ሙሉ ቀን ሸክኳት ‹‹ወቸ ጉድ ስንት አይነት ሰው አለ›› ስትል ዋለች …ጭራሽ እንደውም እኔ ላይ ወረደችብኝ ‹‹ስንት ደህና ጎረቤት ባለበት አገር እንዲች ያሉት አባርሰኛ ሴት ጎን ሂደህ መከራየት ….ተሸሎህ ውጣ እንጅ እዛች ግድም አትሄዳትም›› ብላ ተቆላጨች ! ወደማታ እኔ ረሳችው ብየ ነርሷ ስትመጣ ‹‹ቁስሉ ያመረቅዝ ይሆን እንዴ ሲስተርየ ›› ብላ በስጋት ጠየቀቻት ….ይች ሽብርተኛ ሴትዮ እናቴን አሸበሯት !
*** **** ****
‹‹ወንዴ አንበሳው›› ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀረበ አሉ …ጓደኛየ ታዲዮስ እንዳወራልኝ ከሆነ(መቸም የሱ ነገር እውነት ይሁን ቀልድ እግዜር ነው የሚያውቀው )
የወንድየ የምርመራ ፋይል እንደሚያሳየው ከሆነ…. በዛ ቀን ከቀኑ አስር ሰዓት ጀምሮ ብቻውን ግጨው ግሮሰሪ የሚባል ነበር ያመሸው (ግጨው ግሮሰሪ እዛው ኮንዶሚኒየማችን ግቢ ውስጥ ነው ያለው…. ግሮሰሪው እንኳን ‹‹ብስራት›› የሚል ስም ነው የተለጠፈበት ….ግን ባለቤቱ በቮልስ መኪናው ብዙ ሰው ስለገጨ ግጨው ይሉታል ….በተለይ ወደኋላ ሲሄድ የሆነ ነገር ካልገጨ አይቆምም እያሉ ያሙታል ) እንግዲህ ወንድየ አንበሳው ብዙ ድራማዎችና ፊልሞች ላይ እንደሚታየው ወንድ ልጅ ‹‹ሚስቴ ከዳችኝ ብሎ›› ሲያስብ እንደሚያደርገው ግሮሰሪው ውስጥ ጅን የሚባል መጠጥ እየጠጣ ሲጋራ ሲያጨስ እግረ ጭሰቱንና እግረ መጠጡን ሚስቱን እና እኔን እያሰበ ሲበሳጭ ድንገት ‹‹ሰይጣን›› በሙዚቃ አስመስሎ ምን ማድረግ እንዳለበት ሹክ አለው (የሰይጣንን ስራ ተመልከቱ)
ግሮሰሪው ውስጥ ከተከፈተው የባህል ሙዚቃ አንዷ ግጥም ከዛ ሁሉ የሰካራም ጫጫታና የዘፈን ግጥም ተለይታ ወንድየ ጆሮ ውስጥ ጥልቅ አለች !
ሚስቴን ነካ ብለህ ሚስቱን አትንካበት
በ ‹ቻይና› ቢለዋ አንጀቱን ግባበት….
(አሁን በነፍሬው ሃይሉ ….በነጥላሁን …. በነሜሪ አርሜዲ ….በነአስቴር …በነጅጅ… በነባህሩ ቀኘ …በነማሪቱ ለገሰ …በነቴዲ አፍሮ… በነግራጫው መሰንቆ በነስንቱ ዘፋኝ አገር እንዲህ ያለ ዘፈን ይዘፈናል?? ….ይሄ ግልፅ የጦርነት አዋጅ እንጅ ዘፈን ነው …?)አሁን ይሄን ዘፈን የሰማ ሰው ማን ይሙት ፍቅረኛውን ወላ ሚስቱን ይዞ ወደክለብ ይሄዳል? …በባለሁለት ክፋይ አገልግል በግማሹ ቋንጣውን በግማሹ ሰነፍ ቆሎውን ሰንቆ ወደጠላቱ እንጅ …
ወንዴ ተገለጠለት …ወደቴፑ ዙሮ ‹‹ልክነህ ..ባትለውስ ምን ሚስት አለው ይሄ ነጠላ ጥላቢስ ወንደላጤ›› …እያለ ጮኸ
ልክ በዚች ቅፅበት ደግሞ ሲያገጣጥም እኔ ደውየ የሚስቱን ስም ጠየኩታ !! ሰኔና ሰኞ ገጠመ ! ወንዴ ተነስቶ ሲገሰግስ ወደቤቱ ሄደ ….ደረጃውን ባንዴ ሁለት ሁለቱን እየዘለለ በሩን ከፍቶ ሊገባ ሲል ሌላ ብሎክ ላይ በስህተት እንደወጣ አወቀ ተመልሶ ቁልቁልና ሽቅብ ተምዘግዝጎና ተተኩሶ የራሱን ቤት አገኘው ከፈተ …. ኪችን ገባ …ጭራሽ ኪችኑን ሲመለከት የሚስቱ ናፍቆት ተቀሰቀሰበት …ጠረኗ ጠረነው አጭር ቀሚስ ለብሳ ጉድ ጉድ ስትል ሶፋው ላይ ተጎልቶ የሚያያቸው …እነዛ እንደሰም አእማድ የተዋቡ እግሮቿ ታወሱት ….እንደማር ሰፈፍ በኪችኑ ስትንሳፈፍበት ….ጠረኗ ከምትሰራው ምግብ ጠረን ጋር ተዳምሮ ሲጠርነው …ፍርፍሯ ጨጨብሰዋ ገንፎዋ …ሽሮዋ ..ክትፎዋ ታወሰው …በተለይ‹‹አፈር ስሆን ወንዴ ›› እያለች ባፍ ባፉ አጉርሳው … እራት ከበሉ በኋላ እንደአንቦውሃ ጥጋቡን ብትንትኑን የሚያወጣው እቅፏ ትዝ አለው … ባንዴ ሆዱም ልቡም ጮኸበት …ይሄን ሁሉ እህል ታችኛው ፎቅ ላይ የሚኖረው ‹አብርሃም› የሚባል ጠላቱ ሲያግበሰብሰውና ቆንጆ ሚስቱን ያውም በሱ አልጋ ትክክል የተዘረጋ አልጋ ላይ ሲያቅፋት ታየው እና አቅፎ አድሮ አይደል ጧት ሻንጣዋን ይዞ የሸኛት ሲል አሰበ ….ቢለዋውን መዥረጥ አድርጎ ተመልሶ ወደኔ ቤት ተንደረደረ !
‹‹ጠላትማ ምን ጊዜም ጠላት ነው
አስቀድሞ መውጋት ሚስት አስኮብላዩን ነው ›› ከሚል ፉከራ እና ሽለላ ጋር ….
የአብራሃምን በር አንኳኳ …አብርሃም የዋሁ… የብሎኬት ድንኳኑን መግቢያ ከፈተለታ ….አገኘኛ ….!! እንካ ቅመስ …!! ወንዴ በዚች ቅፅበት ከንዴቱ ነቃ! ከግሮሰሪ ጃስ ብሎ ያስሮተው ዘፋኙ የማይኩን ገመድ ጠቅልሎ ከአካባቢው ድምፄ አውጭኝ ብሏል ! ወንዴን ውሃ በላት አለ ! ጥበቃወቹ እንደበርበሬ እየደለዙ ወደህግ ወፍጮ ሲወስዱት ‹‹እጀን በጀ›› ሳይል አልቀረም …. ምን ዋጋ አለው መጠጥ …ጎርፍ ነው ማደሪያ ሳይኖረው ግንድ ይዞ የሚዞር …ደግሞኮ ግንዱን እያሳሳቀ ነው የሚወስደው ‹‹አፈር ስሆን እኔ ቤት እደር ቤተ መንግስት የመሰለ ቤት አለኝ›› እያለ ….ከዛ አምነው ሲጨልጡትና ራስን ሲጥሉበት አውላላ ሜዳ ላይ እንደግሳንግስ ዘርግፎ እብስ !! …ወንዴ አንበሳው ራሱን አውላላው ላይ አገኘው …ሸቤ !!
ይሄን የምርመራ ፋይል እያስታወስኩ እንደተቀመጥኩ ..በሩ ተከፈተ … ል እ ል ት!! … ደግሞ አጋጣሚው እናተ ….ክፍሉ ውስጥ ማንም አልነበረም እናቴም እቤት ደርሸ ልምጣ ብላ ወጥታለች… እህቶቸም የሉም ( በሽጉጥ ታጅበው ማኪያቶ ለመጠጣት ወጣ ብለው ይሆናል …) ማንም የለም …ልእልት ገብታ ፈገግ አለች … ነጭ ቱታ ሱሪ ወገቡ ላይ በራሱ ማሰሪያ ሸብ የተደረገ ለብሳለች አቤት እንዴት እንዳሸነቀጣት ….ይች ልጅ ግን ጡቶቿ እና ዳሌዋ የተያያዙት በአስማት ነው እንዴ ….ከምር ቦርጭ ይቅርና ሆድ ራሱ የላትም …በአየር ላይ የቆሙ ጡቶቿን አይቶ በቃ ወደታች ካለምንም ማያያዣ ረዘም ካለ ክፍተት በኋላ ሰፋ ያለ ዳሌ በቃ !! ደገፍ ብየ ወደተቀመጥኩበት መጥታ ሰሞኑን እንደጀመርነው ጉንጭ ለጉንጭ ተሳሳምን …ያ ነብስ የሚያስት ጠረን ውጭ ባለው ፀሃይ ምክንያት መጠኑ ከፍ ብሎ …እንደዳመና ሲከበኝ ልእልት የሚባል ብራንድ ሽቶ እላለሁ ለራሴ !! (ዘ ፐርፊውም የተባለው ፊልም ላይ ሽቶ ቀማሚው የቆንጆ ሴት ጠረን ለሽቶ መስሪያ ይሆነው ዘንድ ስንቷን ቆንጆ የጨፈጨፈው ወዶ ነው እንዴ)
ፌስታሏን መደርደሪያው ላይ አስቀመጠች …ደረጃው አድክሟት ነው መሰል ትንፋሸዋ ቁርጥ ቁርጥ ይላል …ከምር አሁን ያ ጦረኛ ባሏ በዚች ቅፅበት ቢደርስ ‹‹ምናባታችሁ አድርጋችሁ ነው እንዲህ ትንፋሽሽ ቁርጥ ቁርጥ የሚለው ›› ብሎ ገጀራ መምዘዙ አይቀርም ነበር ….
‹‹አብርሽ ….እንዴት ነህ አሁን ›› አለችኝ በፈገግታ አይን አይኔን እያየችኝ
እንዴት ነህ አትበሉኝ መልሴ ሊሆን ደህና
ህይወት ተጠያቂ ጠያቂም ናትና ….እንዲል ባለቅኔው ዝም ብየ አየ አየኋት ….ምናልባት ፈገግ ብየ ይሆናል ! ስታምር …..የሰው ሚስት የሰው ሚስት ይሉኛል ….ምንድነው የሰው ሚስት? …..ያ ሁሉንም ነገር ‹‹አለ›› የሚባለው የእንግሊዙ ደራሲ ሸክስፒር እንዴት ስለሰው ሚስት ምንም ሳይል ቀረ ? ለምሳሌ ‹‹ አንዲት ሴት የሰው ሚስት ከመሆኗ በፊት ሰው ነበረች›› ለማለት አፉን ምን ሰይጣን ያዘው??
ል እ ል ት ወንበር ሳበችና ወደአልጋው ጠ…..ጋ ብላ ተቀመጠች …ወንበሩ እሷ ስትቀመጥበት ዙፋን መሰለኝ !!
‹‹የዛሬውን አቀማመጧን ከትላንትናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሳነፃፅረው ››… አስራ አንድ ነጥብ ዘጠኝ በመቶ ከንፈሯ ቀርቦኛል !!

በአልጋው ትክክል (ክፍል አምስት) 

One Comment

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...