አምሽተን ከሬስቶራንቱ ልንወጣ አስተናጋጁን ጠርቸ ልከፍል ስል እህቴ ‹‹ተከፍሏል ዛሬ እኔ ነኝ ጋባዣችሁ ›› አለችኝ …..(ኧረ ሲስቱካ ….ምን ታያት ዛሬ ) ከሬስቶራንቱ በቀኝ እህቴ …በግራ ልእልት አጅበውኝ ስወጣ ምድረ ወንድ አይኑን እህቴና ልእልት ላይ እየተከለ ይነቅላል … በነገራችን ላይ የልእልት ቃል የማይገልፀው ቁንጅና ዋጥ ስልቅጥ አድርጎት እንጅ እህቴም ብትሆን በቁንጅናው አትታማም … እንግዲህ በዚህ ነፋሻ አየር በቆነጃጅት ታጅቦ በሚንጎማለል ጎረምሳ ያልተቀና በማን ይቀናል …ያውም በቀኝ ባለሽጉጥ በግራ ባለ ቢለዋ አጋር ያላቸው ቆነጃጅት መሃል ….ሃሃሃ
ደስ ብሎኛል ….ቢያንስ ናፍቆቱ ቀለል አለልኝ …ልእልት ጋር አብረን አምሸን እላለሁ ለራሴ …ልእልትን የኮንትራት ታክሲ አስይዘን ሸኘናት …ቆሜ ታክሲዋ ስትርቅ ስመለከት ‹‹ አቡቹ አብረሽ በሃሳብ ሄድሽኮ እንሂዳ ›› ብላ አባነነችኝ እህቴ ! በሃፍረት ፈገግ አልኩ … ደስ ብሎኝ ነበር …. ልእልት እዚህ ድረስ ለአይኔ እንደናፈቀችኝ በምናባቴ አውቄ ! የናፍቆት ልኩ ለካ የተናፈቀው ሰው ሲገኝ ነው የሚታወቀው ‹‹ነገ ረፍት ነህ እስቲ እኛ ጋር እቤት እደር ዛሬ … ባዶ ቤት ምን ትሰራለህ ›› አለችኝ እህቴ እንደፍቅረኛ ክንዴን ይዛ …… ውለታዋ ከብዶኝ (ባልናገረውም) እሽ ብየ አብረን ወደቤት መንገድ ጀመርን
‹‹ታክሲ እንያዛ ›› አልኳት
‹‹ወንድ ልጅ አይደለህ እንዴ ….ከዚች እዚች ታክሲ …እስቲ አንዳንዴ ዎክ ማድረግ ልመድ ….የሚስትህ ባል እንደሆነ እስር ቤት ነው ሂሂሂ››
‹‹ ኣኣ …ቢያመልጥስ ….››
‹‹መፋለም ነዋ …ሁለት ወዶ አይሆን ….ወይ ሚስቱን ለቀቅ ወይ …››
‹‹አንች ልጅ ግን እንዴት ነው የምታስቢው … ልእልት ጋር የሆነ ግንኙነት እንዳለን ታስቢያለሽ እንዴ ….ከምር ግራ እየገባሽኝ ነው እንደዛ ካሰብሽ ተሳስተሸል …ባለትዳርኮ ነች ….››
‹‹ ምንድነው ግንኙነት ማለት …..አስር ጊዜ እየተያያችሁ ስትሽኮረመሙብኝ አመሻችሁ ….ምንስ ታናሽ እህት ብሆን …. ትንሽ ብታፍሩኝ ብታከብሩኝ ምን አለበት …. መተፋፈር ወጉ ባህሉ ነበር …እኔን በመስኮት ወርውራችሁ መሳሳምኮ ነው የቀራችሁ …እና ከዚህ ወዲያ በሰው ሰማኒያ ላይ ሰማኒያ አታስር …›› አለችና በራሷ ቀልድ ከትከት ብላ ሳቀች !ላለመሳቅ እየታገልኩ …
‹‹ችግር አለብሽ ›› አልኳት …
‹‹ትክክል ! ችግርማ አለብኝ …ችግሬ አንተ ነህ አብርሽ ›› አለችኝ …. ክንዴን ለቀቅ አድርጋ እጆቿን ኪስና ኪሷ እየከተተች ..‹‹አቡቹ ›› ነው በሰላሙ ቀን የምትለኝ ‹‹አብርሽ›› ካለች መረር ያለ ነገር ሊከተል ነው ማለት ነው ….‹‹ስማ አብርሽ ›› አለች እንደፈራሁት
‹‹ እኔ እዚህ ድረስ ያለችኝን እረፍት አቃጥየ ልእልት ጋር ያገናኘኋችሁ የሰው ሚስት የማቃጥር ባለጌ ሁኘ አይደለም … አንተ እንዳልከው ችግር ስለሆንክብኝ ነው ….ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለማሚም ለቤተሰቡም ለራስህም ችግር ስለሆንክ ነው ….ዝም ብለህ እንደ ፊልም ትሟዘዛለህ ….እግዚአብሔርም በግነትህን አይቶ እንደፊልም ከቢላ አተረፈህ … ሁሌ መትረፍ ግን የለም አብርሽ ! ቢያንስ በእድሜ ትበልጠኛለህ … እያደረክ ያለኸው ነገር ሁሉ ግን የህፃን ነው … አንተ አታፍርም …ነገ እዛው ኮንዶሚኒየምህ ግቢ ቀጥርሃት አንዱ በረንዳ ላይ ተጎልታችሁ አይናይኗን ስታይ ትገኛለህ … እሷም ቀለበቷን አንተ ያደረክላት ሳይመስላት አልቀረም ….ተዋዳችኋል የጅል ፍቅር ››
‹‹ ምንድነው የምታወሪው ….አብደሻል እንዴ …ከተዋወቅን አንድ ወር እንኳን አልሞላንም …ዝምብሎ መዋደድ አለ ? ታበዝዋለሽ ›› አልኳት ውስጤ ግን ‹‹ተዋዳችኋል ›› ስትል ቢያንስ ለሶስተኛ ሰው እስከሚያስታውቅ ልእልት እኔን መውደዷን የሚያረጋግጥ ነገር ፊቷ ላይ መታየቱ ውስጤን አንዳች የንዝረት ስሜት ለቀቀበት ! እኔማ እንደወደድኳት ጥንቅቅ አድርጌ አውቃለሁ ! ሰው መቸስ ካለነገር በቢለዋ ተወግቶ የተኛበት ሆስፒታል ገነት መስሎ አይታየው ! እግዚአብሔር ይሁነኝ እንጅ የሰው ሚስትማ ወድጃለሁ !ልእልትን ወድጃታለሁ ! አእምሮየ እንደድሮ ካሴት የራሱን ደስታ የራሱን ትዝታ ሁሉ እደመሰሰ ልእልት የምትባል ዜማ እቀረፀበት ነው !!
‹‹እንኳን አንድ ወር አንድ ሰዓት ይሁናችሁ ….ሴቶችን አታውቀንም … መጠናናት ቅብርጥስ ስንል እውነት እንዳይመስልህ …ማንኛዋም ሴት ውስጥ ገና በአንድ እይታ ገና በአንድ ቃል ወንድን መዝኖ ማንነቱን ቁጭ የሚያደርግ ደመነፍስ ነው ያለን ….ስሜታችን ደመነፍሳችን የሚነግረንን አውነት ገፍትሮ ስለሚጥለው ነው እኛም በእናተ ተገፍትረን የትም የምንወድቀው ››
‹‹ጉረኛ ….እና የወንድን ልብ ብታውቁ ….በየቀኑ በሬዲዮ አይቀራችሁ በጋዜጣ አታለለኝ …የሚፈልገውን ሲያገኝ ….እሱን አምኘ ቢቢቢቢ …((በሽጉጥ አስፈራርቶኝ ))) የሚል ለቅሷችሁ ያደነቁረን ነበር ?››ብየ ከት ከት ብየ ሳኩ እህቴም የሽጉጧ ነገር አሳቀቻት !
‹‹ብዙ ‹ፋክተር› አለ … እኛ ሴቶች ውስጥ ተራራ የሚያክል በተፈጥሮ የተሰጠን ‹ራሽናል › የሆነ እውነት አለ …ብትፈልግ ደመነፍስ በለው ….ማንኛዋም ሴት ውስጥ አለ …የገጠር በላት የከተማ ….ይሄን እውነት ማንም ወንድ ሃቀኛ ፍቅር ይዞ ካልመጣ በስተቀር ሊገፋውም ሊያሳምነንም አይችልም ! ‹ እናተ ውስጥ ደግሞ በተፈጥሮ ይሁን በአስተዳደግ የተሰጣችሁ ማህበረሰቡ ያስታጠቃችሁ ‹ኢሞሽናል ፈንጅ ›› አለ ….የሀብት ማቀጣጠያ …የስልጣን ማቀጣጠያ የእውቅና ማቀጣጠያ ገመድ የተቀጠለበት …. (አጥፊና ጠፊ አድርጎን) ይሄንንም እናውቃለን ….
በቃ የሆነች ቦታችን ላይ የሆነች ስሜታችን ላይ ተራራ እምነታችንን ትቦረቡሩና ያንን ፈንጃችሁን ትቀብሩብናላችሁ ….ራቅ ብላችሁ መለኮስ ነው ….አየህ ሲቀጣጠል ብናየውም …የእሳቱን ከለር ሙቀቱን እያደነቅን ከመሸሽ ይልቅ ተገትረን እሳታችሁን ስንሞቅ …እንደውም ዙሪያውን እንደሳትራት እየዞርን እንደካምፋየር ስንጨፍር …..ቡምምምምምም ! እምነት የለ ምክንያት የለ ….ቤተሰብ የለ ሞራል የለ ክብር የለ ….ሁሉን ነገር ትተን በፍንዳታው የፈራረሰ ማንነታችንን እግራችሁ ስር እንቆልልላችኋለን ! እናተም ፍርስራሻችን ላይ ከነአፍራሽ ማንነታችሁ ቁማችሁ እንደጀግና መፎከር ማህበረሰቡ የፈቀደላችሁ ወንዳዊ ጀብዱ ነው !! ወንዴ ልእልት ላይ ያደረገው ያንን ነው … አልታወቀህም እንጅ ….ልእልት ድሮ ማንነቷን ስታወራህና ስታዳምጣት ….ለሁለት መልሳችሁ ‹‹ልእልት የምትባላዋን ልጅ እየገነባችኋት ነው›› ያውም የማትፈርስ ልእልት …..በዚህ ግንባታ መሰረት አጣጣልህን ብቻ ለማየት አንድ ወር ብዙ ነው …. ልእልት ደግሞ ስሜትህን አንብበዋለች …. በግን ማን ይጠላል …ስትፈልግ ታረበሃለች …ስትፈልግ ታርድሃለች !!
‹‹እና ልእልት በአንድ ወር መዝናህ ወድሃለች …በፍቅርህ ልብሷን ጥላልሃለች …ካላየችህ እህል አይበላላትም … ከና እንዳየችህ ልቧ ትርክክ ብሎባታል …እያልሽኝ ነው እህት አለም ›› አልኩ አገላለፅዋን ባደንቅም ትንሽ ነገሩን በቀልድ ላዋዛው ብየ
‹‹አላልኩም … ልእልት ከምታስባት በላይ ብልህ ናት እያልኩ ነው ….እስቲ አስበው ከ አስራ አንድ ነው ከአስራሁለተኛ ክፍል ትምህርቷን ያቋረጠች ልጅ … ያውም ከአንድ ወንድ በላይ ነክቷት የማያውቅ ሴት …እንዴት ህይዎትን እንዲህ አብጠርጥራ ልታውቅ ቻለች ?እሽ ይሄ አጋጣሚ ይሁን ….ባሏ ያን ያህል በደል ሲያደርስባት ለምን ትዳሯን መነቃቅራው ሌላ ወንድ ጋር አልሄደችም …እግሯን ስሞ የሚጠቀልላት ወንድ በሽ ነው ….ለእልት ውብ ናት …. እኔ ጋር እንኳን ቅድም ስንሄድ ብቻዋን ያለች ይመስል ወንዱ ሁሉ እሷ ላይ አይኑን ሲያጉረጠርጥና እኔን እህትህን እንደተበላ ቁብ ርስት አድርጎ ሞራሌን ሲነካው አይተሃል ሂሂሂሂሂ …››
‹‹አይዞሽ እህታለም የምንታይበት ጊዜ ይመጣል ›› ብየ በቀልድ አፅናናኋት
‹‹አመሰግናለሁ ወንድማለም…. ሴት በወንድ አይን ብቻ አትኖርም …. በራሷም አይነ ህሊናም ጭምር እንጅ ›› አለችና በማሾፍ እንባዋን በጣቷ ጠርጋ ወደሰማይ ረጨችው (ከምር ይች ልጅኮ ፊልም ምናምን ብትሰራ ያዋጣት ነበር )
እና አቡቹ …ነገሬን ሳሳርገው ….ተፈጥሮ አንዳንዴ ከምታስበው በላይ ጠንካራ ስብእናን በለስላሳና ቆንጆ መልክ ጠቅልላ መንገድህ ላይ ታስቀምጥልሃለች ….ልክ በህፃንነታችን ድንጋይ በካልሲ ጠቅልለው ጥፍራችን እስኪነቀል እንደሚያስጠልዙን ተንኮለኛ ልጆች ማለት ነው …. ከመጠለዝህ በፊት አስተውል …አብርሽ እውነቴን ነው አስተውል …. እወድሃለሁ ላጣህ አልፈልግም ….›› አለች ኮስተር ብላ ….አቀፍኳት ገድገድ ብላ ወደኔ ተጠጋችኝ …‹‹ በስርአት ሴትን ልጅ ማቀፍ እንኳን ሳትችል ነው ከሰው እቅፍ ሰው ሚስጥ ለመንተቅ የምትሮተው ›› አለች … ሃሃ ….እንዳቀፍኳት የሆኑ ወረቀቶች አስጨበጠችኝ …
‹‹ምንድነው ››
‹‹ቅድም ካፌ ውስጥ ላንተና ለሚስታችሁ የከፈልኩት ቢል ነዋ ››
‹‹እና ምን ላድርገው ››
‹‹እቤት ስንደርስ እንተሳሰባለን ›› ከምር አሳቀችኝ …ከምር !!
‹‹ታውቃለህ አቡቹ ….የልእልትን ታሪክ ስትነግረኝ በእያንዳንዷ ቃልህ ውስጥ ለሷ ያለህን ፍቅር በሁኔታህ ስትናገረው ነበርኮ ….›› አለችኝ
‹‹መስሎሽ ነው ባክሽ ››
‹‹የገረመኝ ደግሞ እሷም ስላንተ ስታወራኝ ልክ እንዳንተ ፊቷ በፈገግታ ቦግ ብሎ ነው ›› አለችኝ …ድንገት መንገዱ ላይ ቀጥ ብየ ቆምኩና
‹‹ ከምር ልእልት ስለኔ አወራችሽ …ምን አለችሽ ›› አልኩ በጉጉት
‹‹ ሂሂሂሂሂሂሂሂሂሂሂ ›› ብላ የሚያልፉት ሰዎች እየዞሩ እስከሚያዩን ሳቋን ለቀቀችውና ‹‹ አየሽ አቡቹ …እንዲህ ድንገት መንገድ ላይ ትንፋሽ አሳጥረውና ቀጥ አድርገው የሚያስቆሙ ሁለት ነገሮች ብቻ ናቸው ….አንዱ የፌዴራል ፖሊስ ሲሆን …ሌላው ፍቅር ነው ሂሂሂሂሂሂ ….ለማንኛውም ሚስታችሁ …የአንተ እህት በመሆኔ መታሌን ነገረችኝ … ›› ብላ እስከቤት እየሳቀች መንገዳችንን ቀጠልን …..
One Comment