Tidarfelagi.com

በርበሬ

“አንድ ወዳጄ . . . በርበሬ ኢትዮጵያዊ ቅመም እንዳልሆነና ሲጀመር በአስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን በግራኝ ወረራ ጊዜ ፖርቹጋሎች ወደዚህ ሀገር እንዳመጡት ተናገረ . . .

ነገሩ እየከበደ ውይይቱ አስደሳች ገፅ አበጀ። ጓደኛዬን ‘በርበሬ ከፖርቹጋል እንደመጣ፤ ምን ማስረጃ አለህ?’ አልኩት።
እሱም ጀነን ብሎ ‘በርበሬ’ የሚለው ቃል እኮ ‘ፔፐር’ ከሚለው የፖርቹጊዝ ቃል የመጣ ነው አለ። ፖርቹጊዝ ስለማልችል፣ ይሄን መከራከርያ ያመጣው ራሱ ወንድሜም ስለማይችል፣ ውይይቱ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍና ሁላችንም መረጃችንን እንድናቀርብ ተስማማን።
ይሄ ከዚህ በታች የምታነቡት፤ ወዳጄን የተቀናቀንኩበት መረጃ ነው። በመረጃው ካላመናችሁ፤ እንደ መላምት ብትወስዱትና ብትመራመሩበት መልካም ነው።

#አንደኛ
በፖርቹጊዝ ቋንቋ በርበሬ ‘ፔፐር’ አይባልም። ‘ፒሜንታኦ’ (pimentão) ነው።
ከዚህ ጀምሮ የወዳጄ መከራከርያ ይፈርሳል። በርበሬን ፖርቹጊዞች እዚህ ሀገር ይዘውት መጡ የተባለው እንደ እውነት የተቆጠረው ሃሳብ ተናደ። (ወይስ እንግሊዝኛ ተናጋሪ ፖርቹጊዞች ነበሩ?) ወንድሜ በአንድ ትንሽ መረጃ ስለተረታ፤ የምናደርገው ነገር፤ እርሱን መርሳት ነው።
ከፖርቹጋሎች ብናላቅቀውም፤ የቃሎቹን (የ’ፔፐር’ና በርበሬን) መመሳሰል ግን ልንዘነጋ አይገባም። እንደውም መከታተል ያስፈልጋል።
‘ፔፐር’ እንግሊዝኛ ነው። በ ‘አመጡልን’ ሃሳብ የተጠመዱትን ልጠይቅ። መቼ ነው እንግሊዞች መጥተው ይሄንን የነገሩን?
ከዚህ በኋላ የእንግሊዝኛው ቃል ከየት እንደፈለቀ እንከታተላለን። ወይም አውሮፓ ውስጥ ይሄን ቃል የሚጠቀሙት እነማን እንደሆኑ እናስሳለን።
በተጨማሪ፤ በትንሽ ምርምር፤ በርበሬ በስፓኛና በፈረንሳይ ወሰን ላይ የሚገኙ የባስክ ሕዝቦች የምግባቸው መሰረት እንደሆነ እንረዳለን። የዚህን ተክል ስም ‘ኤዝፔሌታኮ ቢፔራ’ ይሉታል። እንደውም በአመት ውስጥ ‘የበርበሬ በዓል’ ተብሎ የተሰየመ ቀን አላቸው። ‘ቢፔራ’ የተባለው ቃል ለእኛ ‘በርበሬ’ ለተሰኘው ቃል ትንሽ ይቀርባል። መላምቴን ባስኮች ላይ አደርጋለሁ።
ከወንድሜ መላምት ወደ ሌላ ወደተያያዘ መላምት መምጣት ዐሠሣ ስለሆነ ክፋት የለውም።

#ሁለተኛ
የባስኮች ቋንቋ ባስክ ይባላል። ባስክ በአውሮፓ የሚገኝ ብቸኛ የሃማቲክ ሴሜቲክ ቋንቋ ነው። ይሄም በምድቡ በአገራችን ያለውን ኦሞቲክ የተባለውንም ይጨምራል። ይሄ ኢትዮጵያዊ ቋንቋ አውሮፓ ውስጥ ምን ሊያደርግ ገባ? የቋንቋ ጠበብት የባስኮች ቋንቋ ከግዕዝ፣ ከቋራ፣ ከቅማንት፣ ከሽናሻ፣ ከማኦ፣ ከሳሆ፣ ከጉራጌ፣ ከሐዲያ፣ ወዘተ የሚመሳሰልባቸው ቦታዎች አሉ ይላሉ። እንዴት ሆነ?
#ሦስተኛ
ሮበርት ኤሊስ የተባለ የቋንቋ ተመራማሪ በአንድ ፅሑፉ ይህን ብሏል፤
‘በጥንቷ ስፓኛ ሶስት የሕዝብ ዘሮች ጎን ለጎን አብረው ይኖሩ ነበር። ሁሉም እዛ አካባቢ ይኖሩ እንደነበረ ምልክት ትተው ሄደዋል (በቋንቋ ማለቱ ነው)። እነዚህም ሕዝቦች ሁለቱ ኬልቶችና አይቤርያን የሚባሉ ሲሆኑ ሶስተኛዎቹ ሲንቴ ይባላሉ። በቋንቋቸው ምክኒያት ሲንቴ የሚባሉት ሕዝቦች ኢትዮጵያውያን ናቸው ይባላል። ወይም ቢያንስ ስፓኛ ውስጥ ኢትዮጵያውያን ነበሩ።
(“In ancient Spain, there coexisted three races of nations, all of which may have left their mark…. there were Celts,… there were Iberians. The following resemblances … in favour of the hypothesis that the Cyntae were Ethiopians, or at least, there was an Ethiopian race in ancient Spain”. Robert Ellis, On numerals as signs of primeval unity among mankind: 1873)

#አራተኛ
አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፤ በእኛ ሀገር በርበሬ በብዛት የሚበቅልበትና ብዙውን የሚያመርተው አገር የት ጋ ነው? ማን ይባላል?

#አምስተኛ
መልስ – ባስኬቶ ይባላል።

#ስድስተኛ
ይሄ ቃል ሃሳባችሁ ውስጥ ምን ያጭራል?

#ሰባተኛ
የስፓኛውን ባስክ?

#ስምንተኛ
ኢትዮጵያ ውስጥ (በወጥ፣ እንጀራ በመተምተም፣ በቆሎ፣ በዳቦ፣ ወዘተ) በርበሬ ማዕከላዊ ቅመም ነው። የቅመማት መሰባሰቢያ ነው። የቅመማት አያያዥ ነው። ውህድ ነው። ስንጠራው ግን ራሱን እንደቻለ ወጥ’ ነገር ነው።

#ዘጠነኛ
በርበሬ እንዲህ እየተቀመመ የሚሰራው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው። እዚህ ደረጃ ለመድረስ የብዙ ዘመን ማሕበራዊ ተሳትፎ ይጠይቃል። ከነዚህ ቅመማት ጥቂቶቹ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ እንደሚገኙ ማስረጃ አለ። እንዴት ይሄ ልዩ የሆነ ነገር ኮፒ ሊሆን ይችላል?
ብዙ ጊዜ የወዳጅ ጠላቶች በማሞካሸት ጋርደው እንዲህ ይላሉ፤
‘ኢትዮጵያውያን ከባዕድ ይወርሱና በሚገርም መልክ የራሳቸው ያደርጉታል።’
‘በሚገርም’ የምትለዋ ቃል የውሸት አሞጋሽ ናት። ለመሆኑ ባዕዳን ኮርጀው ‘በሚገርም’ መልክ ለራሳቸው ማድረግ አይችሉም?
የባዕዳን ታሪክ ፀሀፊዎችና አዋቂዎችን በጣም አደንቃለሁ። ለወገናቸው፤ ውሸትም ቢሆን የሚጠቅም ያደርጋሉ። በርበሬን ከ ‘ፔፐር’ መጣ ያሉትን የእኛ ሰዎች ግን በምን ሂሳብ እንደሆነ ብናፋጥጣቸው መግቢያ አላቸው።
መውጫ ግን የላቸውም።
ወደ ሆዳቸው የሚገባው በርበሬ እንኳን ከሌላ የተቀዳ ነው። የሚበሉትን በርበሬ እንኳን ነጥቆ ሲወስድባቸው አፍጠው የሚያዩ አሉ (እየተቁለጨለጩ አይደለም)።
በሌላ አነጋገር ጥንት በርበሬ ሰፍረንልሃል ዛሬም ስንዴ እንሰፍርልሃለን። ድሮም አትረባም ዛሬም አትረባም ማለት ነው። ታዲያ ይሄን ማያያዝ እየተሳናቸው ዝም ከሚሉ ሰዎች የበለጠ ደካማ አለ?

መደምደሚያ፡
ሀ/ ከየት እንደመጣ የማይታወቅ እምነት ይዛችሁ ሙጭጭ አትበሉ። ፈትሹት። ልክ ልትሆኑም፣ ላትሆኑም ትችላላችሁ። እኔ ያለኝን ወርውሬአለሁ። እናንተም ወርውሩ።

ለ/ ሰዎች ታሪክ የሚነጠቁት በጦርነት ብቻ አይደለም። በጨዋታ መሃልም ነው። እና አብረህ ስትደንስ፤ ከአዳናሽህም ተጠንቀቅ።
‘እኛ እኛ እኛ’ የሚያበዛ ጠመም ያለ ሃሳብ ካጋጠመህ፤ ጠይቅ። ምን ‘እኛ እኛ እኛ እያለ ጠመም ይላል?’ በል።
የተከራከሩኝ ወንድሞቼ ምሑራን ቢሆኑም፣ አንድ ምሁር ማድረግ የሚገባውን ግን አላደረጉም። ያም፤ ጠርጥሮ መጠየቅ ነው። ይኼም ባለመሆኑ የተማሩት ሳይንስ ሁሉ ሜዳ ቀረ።
እንዲህ እንዲህ ሲሆን የብሩህነት እጥረት ይባላል።”
***
#የስንብት_ቀለማት

አዳም ረታ አንጋፋ የሀገራችን ደራሲ ነው፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...