Tidarfelagi.com

የበላይ ዘለቀ እና የፋሺስት ኢጣሊያ ድርድር ታሪከ

በላይ ዘለቀ ከአባታቸው ከባሻ ዘለቀ ላቀው እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ጣይቱ አስኔ በወሎ ክፍለ ሐገር በቦረና ሳይንት አውራጃ በጫቃታ ወረዳ ልዩ ስሙ ጅሩ ጉጣ ከተባለው ቀበሌ በ1904 ዓ.ም ተወለዱ። ፋሺስት ኢጣሊያ በ1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን ሲወር በላይ ዘለቀ የ24 ዓመት ወጣት ነበር። ሀገርን የወረረውን የኢጣሊያን ጦር ለመውጋት ቆርጦ የተነሳውም በዚያ ወቅት ነበር። በወቅቱ ከ200 እስከ 300 ያህል ጦር በስሩ ነበሩት ። በወቅቱ ትግላቸውን ሲጀምሩ የአካባቢውን ሕዝብ ሰብስበው ለህዝብ እንዲህ ብለው ነበር ፡- “… እናት ሐገሬ ኢትዮጵያ ስትደፈር ከማየት ሞቴን እመርጣለሁ። የፈራህ ልቀቀኝ! ለውድ እናት ሀገርህ መስዋዕት ለመሆን የምትፈልግ ሁሉ እኔን ተከተለኝ።”

የመጀመሪያ ውጊያቸውን ለምጨን ከተባለ ቦታ በግንቦት ወር 1928 ዓ.ም ከኢጣሊያ ፋሽስት ጋር ገጥመው ሲዋጉ ከወገን በኩል በመጠኑ የቆሰለና የሞተ ቢኖርም ጠላትን ድባቅ መተው መደረሻ ኣሳጥተውት ነበር ። በላይ ዘለቀ ጐጃም ውስጥ የጠላት ጦር መቆሚያ እና መቀመጫ እንዳይኖረው በማድረግ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ውለታ ያበረከቱ ጀግና ናቸው። በላይ ዘለቀ ከውስጥም ከውጭም ጠላቶች ነበሩአቸው ለምሳሌ ቀኛዝማች ሰማነባዋ የተባሉት የኢጣሊያ የባንዳ አለቃ ስለነበሩ በቂ መሣሪያ እና 500 ወታደር ይዘው በቢቸና አውራጃ በሸበል በረንታ ወረዳ ልዩ ስሙ አባራ ጊዮርጊስ ከተባለው ቦታ ገጥመዋቸው ነበር ። በተደረገው ውጊያ ቀኛዝማች ሶማ ነገዎን ገድለው፣ ከሞት የተረፉትን ጀሌዎቻቸውን በሙሉ ከነመሣሪያዠው ማርከው ካስቀሩ በኋላ በላይ ዘለቀ እንዲህ አሉ፡- “እናንተ ከኢጣሊያ ታዛችሁ ከአገራችሁ በመክዳት በዛው ቀን በተደረገው ጦርነት ከሞት ተርፋችሁ የተማረካችሁ ኢትዮጵያዊ የሆናችሁ ወገኖቼ ሁሉ፣ አሁን በእኔ በኩል ምሬአችኋለሁ። እናት ሀገራችሁን የምትወዱ ተከተሉኝ። ወይም አርሳችሁ ብሉ። ነገር ግን ሁለተኛ ለጠላት ገብታችሁ ብትገኙ እኔ የዘለቀ ለጅ ነገ እመጣለሁ” በማለት መክረው አሰናበቷቸው።

በላይ ዘለቀ ሊወጋቸው የመጣውን የኢጣሊያ ጦር ከመመከት አልፈው ድልን መቀናጀት ዋናው መለያቸው እየሆነ መጣ። የኢጣሊያ ጦር ሁሌም እየተሸነፈ በመሄዱ ተስፋ በመቁረጥ የበላይ ዘለቀን ባለቤት ወ/ሮ ሸክሚቱ አለማየሁን እና የባለቤታቸውን እህት ወ/ሮ ዘውዲቱ አለማየሁን ገድሎ ልጃቸው ወ/ት የሻሽወርቅ በላይን ማርኮ ሄደ። ከዚህ በኋላም የበላይ ዘለቀ እልህም እያየለ በመምጣት ብዙ የኢጣሊያ ወታደሮችን ድል አደረጉ።

በመጨረሻም ጠላት ከበላይ ዘለቀ ጋር ታርቆ፣ ሠላም ፈጥሮ መኖር ፈለገና የሚከተለውን መልዕክት ላከላቸው።
“ይድረስ ለልጅ በላይ ዘለቀ። ለኢጣሊያ መንግስት ብትገባ ጥቅም እንጂ ጉዳት አያገኝህም። ጐጃምን በእንደራሴነት ይሰጥሃል። ስለዚህ በሰላም ግባ የኢጣሊያ መንግስት መሀሪ ነውና በአጠቃላይ ሙሉ ምህረት ያደርግልሃል” የሚል ነበር። በዚህ ግዜ ጀግናው በላይ ዘለቀም ይህንን የኢጣሊያ ደብዳቤ በሰሙ ጊዜ ለተፃፈው ደብዳቤ መልስ ሲፅፉ እንዲህ አሉ፡-
“ይድረስ ለኢጣሊያ መንግሥት፣ ከሁሉ አስቀድሜ ሁልጊዜ ሰላም ላንተ ይሁን እያልኩ የማክበር ሰላምታዬን አቀርባለሁ። ከሰላምታዬ ቀጥዬ የምገልፅልህ ነገር ቢኖር ከኢጣሊያ መንግሥት የተፃፈልኝ ደብዳቤ ደርሶኛል። በአክብሮት ተቀብያለሁ። ተመልክቸዋለሁ። በደብዳቤው ላይ ያለውን ቁም ነገር ያዘለ ቃል ስመለከተው እጅግ በጣም የሚያስደስት ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ስለዚህ ልጄን ከመለስክልኝ ጐጃምን ያህል ሀገር በእንደራሴነት ከሰጠኸኝ ከዚህ የበለጠ ሌላ ምን እፈልጋለሁ። ስለዚህ የኢጣሊያ መንግስት የሚያምናቸውን ታማኞቹን ይላክልኝና በእነሱ አማካኝነት አገባለሁ” የሚል ደብዳቤ መልሰው ፃፉለት። በዚህን ጊዜ የኢጣሊያን መንግስት የበላይ ዘለቀን ደብዳቤ እንደደረሰው ሲመለከተው አስደሳች ሆኖ ስለአገኘው በላይ ዘለቀን በእርቅ አታሎ በእጁ ለማስገባት የዘወትር ምኞቱ ስለነበር በጉጉት ይጠብቀው የነበረው ሃሳብ የተሳካ መስሎት የራሱ የፍርድ ቤት ዳኞች ሆነው በታማኝነት ሲያገለግሉት የነበሩትን፣ በኢትዮጵያዊያን ወገናቸው በአርበኛው ላይ ይሰቀል ይገረፍ እያሉ ሲፈርዱና አርበኛ ያለበትን ቦታ ሲጠቁሙና መርተው በማሳየት ይረዱ የነበሩትን ታማኞችን እነ ቀኛዝማች እጅጉ ለማንና እነ ቀኛዝማች አደራው የተባሉትን ከነ አስተርጓሚ ጭምር ሆነው በላይ ዘለቀን በእርቅ አታለውና አባብለው በእጁ እንዲያስገቡለት ላካቸው። በኢጣሊያ መንግሥትና በጀግናው በላይ ዘለቀ መካከል በእርቅ መልክ ለማስማማት የተላኩት ሽማግሌዎችም መድረስ አይቀርምና እንደ እመጫት ነብር ከሚያስፈራው ኮስትር ፊት ቀረቡ። በዚህ ግዜ ጀግናው በላይ ዘለቀም ከፊታቸው ለተሰለፈው ጀግና አርበኛ እንዲህ ሲሉ ስለ እንግዶቹ የሚከተለውን ንግግር አደረጉ።
“ጐበዝ ያገሬ ጀግና ሆይ፣ አንድ ግዜ አዳምጠኝ፤ እነዚህ እኔንና የኢጣሊያን መንግስት ለማስታረቅ የመጡ እነ ቀኛዝማች እጅጉ ለማ የተባሉት ሐገራቸውን ከድተው እዚሁ እላይዋ ላይ ሆነው ለኢጣሊያ ፋሽስት ለማያውቁት ለማይወለዱት፣ ለማይመሳሰላቸው በገንዘብ፣ በጊዜያዊ ጥቅም በመደለል ለጠላት መሣሪያ በመሆን በሐቅና በእውነት ለውድ እናት ሀገራቸው የሚዋደቁትን ንፁህ ኢትዮጵያዊያንን ሲያሰቅሉ፣ ሲያሳስሩ፣ ሲያንገላቱና ሲያስረሽኑ ከመቆየታቸው በላይ አሁን እኔንም በዕርቅ መልክ አስገብተው ለማስረሸንና አገሪቱ ተከላካይ ልጅ እንዳይኖራት የሚጥሩ ናቸው። ስለዚህ ምን ውሣኔ ማግኘት እንደሚገባቸው ጀግናው አርበኛ ሃሳብህን ስጥበት” ሲሉ ተናገሩ። በዚህ ጊዜ ጀግናው አርበኛም የመሪውን አነጋገር በጥሞና ካዳመጠ በኋላ እንዲገደሉ ተወሰነ። በዚህ ጊዜ በአስታራቂነት የመጡት እነ ቀኛዝማች እጅጉ ለማ እነሱ በሌላ ሲፈርዱ ኖረው በእነሱ ላይ ይግባኝ የሌለው የአርበኛ ፍርድ በማግኘት ፅዋው ስለደረሳቸው በጥይት ተረሽነው በዛፍ ላይ ተሰቀሉ።

ከዚያም በኋላ ጀግናው በላይ ዘለቀም እንዲህ የሚል ደብዳቤ ለኢጣሊያ መንግሥት ፃፈ፡-
“ይድረስ ለኢጣሊያ መንግሥት፤ ሰላም ለአንተ ይሁን፤ የላክልኝን እንግዶች እነ ቀኛዝማች እጅጉ ለማን በአክብሮት ተቀብዬ በማስተናገድ ሥፍራ ወይም ቦታ ሰጥቻቸዋለሁ። ላንተ ግን ትርጁማን (አስተርጓሚ) ብለህ የላከውን ሌላ ቦታ ስትልክ እንዳይቸግርህ ልኬልሃለሁ። ልጅህን እመልስልሃለሁ ለምትለው ለአንድ ልጅ ብዬ እናት ሀገሬን ኢትዮጵያን ከድቼ ከአንተ ጋር በእርቅ መልክ አልደራደርም። ከዛሬ ጀምረህ በእኔ በኩል ያለውን ምኞትህን አንሳ። እኔን ፈልገህ ማጥፋት እንጂ አንዲት ልጅ ወስዶ ማስጨነቅና ማጉላላት ደስ የሚልህ ከሆነ እንደፈለክ አድርጋት። ሲሆን ለሷም የፈጠራት አምላክ እግዚአብሔር ፍቃዱ ከሆነ ከአንተው እጅ ላመጣት እችል ይሆናል። ጐጃምን በእንደራሴነት ልስጥህ ለምትለው አንተ የሰው ሀገር ሰው ከምትሰጠኝ እኔው ሀገሬን በሥሬ አድርጌ አስተዳድረው የለም ወይ? የኢትዮጵያን አርበኛ እየቆማመጠ ለአሞራ በመስጠት በየዱር ገደሉ ወድቀህ ከመቅረት በመጣህበት መንገድ አገርህ ከመግባት በስተቀር አማራጭ የሌለህ መሆንህን በዚህ አጋጣሚ ልነግርህ እወዳለሁ” ሲሉ በላይ ዘለቀ ለኢጣሊያ መንግሥት ደብዳቤ ልከዋል።

በመጨረሻም የተማረከችውን ልጃቸውን የሻሽወርቅን እንደገና ተዋግተው ከኢጣሊያኖች እጅ ከነህይወቷ ለመማረክ ችለዋል። በአጠቃላይ በላይ ዘለቀ በአምስቱ ዓመት የነፃነት ተጋድሎ ውስጥ ከፊት የሚሰለፉ ታላቅ አርበኛ ናቸው።

ከ ሠንደቅ ጋዜጣ የተወሠደ

———
የበላይ ዘለቀ አባት (ባሻ ዘለቀ) ብቸና ውስጥ እያሉ እርሳቸውን የሚያስስ ልዩ ጦር በጥቆማ ወደ አካባቢው ተልኮ እርሳቸውን ለመያዝ ጥረት ተደርጎ ነበር ። ከዚህ ጦር ጋርም ከፍተኛ ውጊያ ተደርጏል። በዚህ ውጊያ ወቅት በላይ ዘለቀ እና ወድሙ እጅጉ ዘለቀ ልጆች ቢሆኑም ውጊያውን ተደብቀው ከርቀት ይከታተሉ ነበር። አባታቸው ግን በውጊያው ወቅት በጥይት ተመተው ይወድቃሉ ከዚያም ይሞታሉ። እነ በላይ ዘለቀም ካለ አባት ከእናታቸው ከወ/ሮ ጣይቱ አሰኔ ጋር ነበር ያደሩት።

One Comment

  • yonasbirhanu@17gmail.com'
    yonas birhanu commented on November 9, 2021 Reply

    ግሩም!!! እምነት ታደሰደሰ!!!!

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...