Tidarfelagi.com

‹‹ቆንጅዬ›› (ክፍል ሁለት)

– ወይኔ….ወይኔ! አረ በማርያም ቀስ በይ…ሰጋዬን እንዳትቦጭቂው! አልኩ በጩኸት።
ከዚያ ቁንጅናውን ይዞ ከአዲሱ መስሪያ ቤቴ ሊለቅ ለተዘጋጀው- ቀሚሽ ያምራል- ሽሮ ልጋብዝሽ ምናምን ብሎ ላሽኮመመኝ የመጀመሪያው ወንድ ልጅ እራት እየተዘጋጀሁ ነው። የእግሮቼን ጠጉሮች በሞቀ ሰም እያስላጨሁ ነው።

ከብስጭት የተሰራ የሚመስል ፊት ያላት ሴትዮ ናት ያለርህራሄ የምትላጨኝ። ህመሙን መግለፅ አይቻልም። መጀመሪያ ለፕላስተርነት ከሚቀርብ ነገር የተሰራውን በአራት አራት መአዘን የተቆራረጠ ነገር ታመጣለች። ከዚያ ምድጃ ላይ የተጣደው ሰም ውስጥ ትከተዋለች። ደቂቃ ቆይታ ታወጣዋለች። ፀጉራሙን ቦታ እየመረጠች አንዴ ባቴ፣ አንዴ ቁርጭምጭሚቴ አካባቢ፣ ሲላት ጉልበቴ ጋር ትለጥፈዋለች። ይይዛል። ይሄን ጊዜ ይሞቃል እንጂ አያምም። ከዛ ግን የጭቃ ጅራፏን ታመጣዋለች። በአንድ ምት ጫፉን ይዛ ላጥ አድርጋ ስታነሳው ፀጉሬን ይዞ ሲነሳ ከነ ቆዳዬ፣ ከነስጋዬ የተነሳ ይመስል ነፍሴን ከስጋዬ የሚያላቅቅ ህመም ይሰማኛል። ከዚያ ይሄንኑ አስሬ- አስራ አንዴ- አስራ ሁለቴ ትደጋግመዋለች። ህመሙን መግለፅ አይቻልም። በትንሹ ሊገልፀው የሚችለው ነገር እሳት በተነከረ አለንጋ እንደመገርፍ ነው ብላችሁ ነው።

አንዱን የለጠፈችውን ላ—-ጥ አድርጋ ባነሳች ቁጥር
– ወይኔ ወይኔ አረ ቀስ! ብዬ እጮሃለሁ።
– የመጀመሪያሽ ነው? አለችኝ ፊቷን እንዳቀጨመች።
– አዎ….!
ዝም አለች።
– ስጋዬም አብሮ የተነሳ ያህል ነው ሚያመኝ….አልኩ ሰውነቴ እየተንቀጠቀጠ። ቀጥላ የምታነሳው የትኛውን ይሆን በሚል ስጋት ተወጥሬ
– ሲያጌጡ ይመላለጡ ነው እንግዲህ…..አለችና ላ—–ጥ!

ቀላል እየተላላጥኩ ነው?

ሴቶች ግን ምን ሆነው ራሳቸው ላይ እንዲህ አይነት ስቃይ የሚያበዙት? ቅንድብ ሲቀነደቡ ህመም፣ ካስክ ሲገቡ መቃጠል፣ ዋክስ ሲደረጉ ስቃይ…..ምን ሆነን ነው?

ቁርጭምጭሚቴ ጋር ላ—-ጥ! አደረገችኝ።
– ወይኔ…አረ ይሄ ነገር ማደንዘዣ ያስፈልገዋል….! አልኩ
– ሃሃ…አለች ፊቷ ሳይፈታ። ጥርሷ ሳይታይ። ምን አይነት ሳቅ ነው? ማእከላዊ ገራፊ የነበረችና በሰው ስቃይ የምትደሰት አይነት ሰው ትመስላለች።
ላ….ጥ!

– አይዞሽ ጨርሻለሁ አሁን….
ጥርሶቼን እንደበረደው ሰው እያንገጫገጭኩ፣ አይኖቼን ጨፍኜ እንድትጨርስ ተመኘሁ።
– አሁን ይሻላል…ሌላ ጊዜ እንደዚህ አትቆይ…ባደገ ቁጥር ይባስ ያማል…አለችኝ ፎጣዬን ያለ ፈቃዴ እስከ እንትኔ ድረስ ከፍ አድርጋ። ሱሪሽ አይመችም ብለው አስወልቀውኝ የእነሱን ፎጣ አገልድሜ በውስጥ ሱሪ ነው ያለሁት።
ክው ብዬ ፎጣውን በእጆቼ ልመለስ ስል
– እንዴ….ምንድነው የሚታየኝ እዛ ጋር…..ደን እያለማሽ ነውእንዴ? አለቸኝ
(ገራፊዋ ቀልድም ትችላለች።) ሳቅኩ።
– እውነት ምንድነው እንዲህ መዝረክረክ…አንድ በይው እንጂ…አለችኝ እንደተኮሳተረች።
– እህ…አልኩ (እሱም አለ ለካ ብዬ እያሰብኩ)
– ብራዚሊያን አትፈልጊም? አለችኝ በተኛሁበት ቁልቁል እያየችኝ።
– ብራዚሊያን ደሞ ምንድነው? አልኳት በፍርሃት እያየኋት
– ሆ…ያዲሳባ ልጅ አይደለሽም እንዴ?
– ነኝ….ግን ሰምቼው አላውቅም።
ነገረችኝ።
– እንዴ! ሴቱ እሱንም ከፍሎ ያስላጫል እንዴ? አልኩኝ ከልክ በላይ ደንግጬም ተገርሜም፡
– ድብን አርጎ ነዋ…እንኳን ሴቱ ወንዱም ጀምሯል አሁንማ…
ማመን አላቻልኩም።

(ወንድ ልጅ እዛ ጋር ያለውን ፀጉር ያስላጫል? ለምን? ታየኝ አንዴ ወደ ግራ…አንዴ ወደ ቀኝ እያደረጉ ሲላጩዋቸው… የፈጣሪ ያለ! )
– እኛ ግን ወንድ አንሰራም…ሴት ግን እንሰራለን…. አለችኝ
– እ…. አልኩ እያቅማማሁ። እግሬን እንደህ ያመመኝ ስስ ‹‹ብልቴ›› ቢነካ ምን ልሆን እንደምችል አስቤ።
– ከእግር ብዙ አያምም….አለችኝ ሃሳቤን የሰማች ይመስል
– ግን…ለምን ይላጫል ሴቱ…ማለቴ ቤት ራሳቸው ነካ ነካ አያደርጉትም?

በዚያ ፊቷ ፈገግ ማለት የምትችለውን ያህል ፈገግ ብላ
– አይ…በምላጭ ለዛውም ራስሽ አይመችም እኮ….ሴቱ ደግሞ እየወፈረ ቦርጩ ከልሎት እንትናቸውን ካዩ ዘመን ያለፈባቸውም ስንት አሉ እኮ….አለቸ
(ይህች ሴትዮ ቀላል ትቀልዳለች እንዴ…?) በጣም ሳቅኩ።

– የዛሬ ወንዶች እዛ ጋር ፀጉር ሲበዛ አይወዱም አሉ….እኔ ምን አውቃለሁ…ሴቶቹ እንደዛ ይሉኛል…በወር ወር እየመጡ ዋክስ የሚደረጉ ካስተመሮች አሉኝ….

(የዛሬ ወንዶች እዛ ጋር ፀጉር አይወዱም? …እና…ለሽሮ እራት እንትኔን በሞቀ ሰም ላስላጭ?)
– ለምንድነው ማይወዱት አልኳት
– እንጃ…ስንፍና ይሆናላ!…ፈልጎ ላለማግኘት….ሃሃሃ
(ሆሆይ…ምን ጣጣ ውስጥ ገባሁ ….?)
– ስንት ብር ነው? አልኩ በተኛሁበት እያየኋት
– ከላይ ከላይ ከሆነ 300 ብር…ብራዚሊያን ደግሞ 500 ነው። እንደኔ ግን ብራዚሊያኑ ይሻልሻል….ጥርት ያለ ነው…በዛ ላይ ይቆይልሻል….

(ከላይ ከላይ የቱ ጋር ነው? ….ብራዚሊያንስ ምን ምንን ነው ሚያካትተው ብዬ ለመጠየቅ ፈለግኩ)

– ብራዚሊያን ሲሆን አንዲት ፀጉር አትቀርም…በየትም በኩል….አለችኝ
(ሃሳቤን ትሰማለች ልበል?)
– እሺ…ብራዚሊያን ይሁንልኝ…አልኩኝ እየፈራሁም፣ አዲስ ነገር ለማድረግ በመዘጋጀቴም በራሴ እየኮራሁ።
እሷ አዳዲስ ፕላስተሮች ሰፋ ያለ ድስት ውስጥ የሚንተከተክ ሰም ውስጥ ስትነክር እኔ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፀጉር ነፃ የሆኑ እግሮቼን እርስ በርስ አነካካሁ። አወይ መለስለሳቸው። ያማርኩ መሰለኝ።

– እሺ…እንጀመር……..(ከመቼው ሞቀላት…)
– እሺ…አልኩ ደንበር ብዬ…
– እ….ፓንትሽን አውልቂያ…›!
አወለቅኩ።

– እግርሽን ወደ ላይ! አዘዘችኝ።
የፈጣሪ ያለህ!

ከእኔ በቀር ማንም ነክቶት የማያውቅ ጓዳ ጎድጓዳዬን በርብራ አንዲት ፀጉር እንኳን ለወሬ ነጋሪነት ሳታስቀር ላጭታ ጨረሰችኝ።

በረደኝ።

– እይ.ው….! አለችና የፊት መስታወት ሰጠችኝ።
– እ? አልኩ ደንግጬ
– እይው…ቅር ያለሽ ቦታ ካለ…

(ወይ ጉድ! ምኑ ቅር ይለኛል?)

አየሁት። ሞልጫኝ የለ እንዴ!
አዲስ የተወለደች ሴት ልጅ መስያለሁ።

– አሪፍ ነው? አለችኝ መስታወቱን ልትቀበለኝ እየተዘጋጀች
– እ…አዎ….. መስታወቱን እየመለስኩላት
– በሚቀጥለው ስትመጪ ዲዛይን እሰራልሻለሁ….
– እ?
– ዲዛይን…የልብ ቅርፅ ምናምን….

ወይ ጉድ!

– እሺ…አልኩ እየተነሳሁ። ገላዬ የኔ አልመስል አለኝ። የተከፋፈትኩ መሰለኝ። መስኮቱም በሩም እንደተከፈተ ቤት ንፋስ ተመላለሰብኝ…
ሱሪዬን ፍለጋ ዞር ስል-
– በይ ይልመድብሽሽ..እርግጠኛ ነኝ ይወደዋል….አለችና ትታኝ ሄደች
የሚያየው ወንድ እንደሌለና በምናልባት ከታየ- በዚህ ሁሉ ስቃይ እንዳፍኩ ብታውቅ ታዝንልኝ ይሆን?

– – –
– ውይ ዛሬ ደግሞ ሌላ ሆነሻል…..እንዴት እንዳማረብሽ…አለኝ ገና እንደተገናኘን። ቀድሞ ደርሶ እየጠበቀኝ ነበር። ግርግር የበዛበት ምግብ ቤቱ ደንገዝገዝ ያለ ነው። እንደውም ለጭለማ የቀረበ ነው። ተበሳጨሁ። ይሄን ሁሉ ተሰቃይቼ ውጤቱን ማሳየት የማልችልበት ቤት ይቀጥረኛል?ስቃዬ የባከነ መሰለኝ።
– እውነት ልዩ ሆነሻል ዛሬ….
(ህእ! ያለፍኩትን ስቃይ ባየህ!)

እንደነገሩ ጉንጭ ለጉንጭ ተሳሳምንና እግሮቼን አነባብሬ ቁጭ አልኩ። አወይ አለሳለስ! አጭር ቀሚሴ ይበልጥ አጥሮ ስንት ያየሁባቸው እግሮቼ እና ግማሽ ጭኖቼ ተጋለጡ።
– ቤቱን ወደድሽው? አለ ጭኖቼን ያላየ ለመምሰል እየሞከረ
– አዎ….ደስ ይላል
(ግን በጣም ጨለማ ነው….ምን ዋጋ አለው…..)

– እሺ…ስራ እንዴት ነው?
– ደህና ነው…
– እየለመድሽ ነው?
– ምንም አልል…
የተነባበሩ እግሮቼን ስነጣጥላቸው ከየት መጣ ያላልኩት ብርድ ቀጥ ብሎ ማህፀኔ ውስጥ የገባ መሰለኝ። መልሼ አነባበርኳቸው።

የተወራለት ሽሮ መጥቶ መብላት ጀመርን።
– ሽሮው እንዴት ነው?
– በጣም አሪፍ ነው…
– አላገናንኩም አይደል? እንጀራ ጠቅልሎ እየጎረሰ…
– በጭራሽ …በጣም ይጣፍጣል… አልኩ አንድ ጎርሼ እየተቅለሰለስኩ…
– ከኔ ግን አይበልጥም…
ዛሬም ትን ሊለኝ ነበር።

(አረ ፍጥነት…በዚህ አይነት እዚያ ጋር መላጨቴ ደግ አድረጌያለሁ። )
ዝም ብዬ ጉርሻዬን ማላመጥ ቀጠልኩ።
– ምነው? አለኝ…
– ምነው? መለስኩ
– አጠፋሁ እንዴ?

(አረ አላጠፋህም የኔ ሰፈፍ የሌለው ማር….የኔ ጌታ….)

– አይ…
በልተን ጨረስን እና ወጣን።

– – –
ዛሬም እንደወትሮ ተቀጣጥረን ተገናኝተናል። ከተገናኘን ጀምሮ በሳምንት ቢያንስ ሶስት ጊዜ እንገናኛለን። ፀጉሬ አልበቀለም። ቀሚሴም አጭር ነው። ፀጉሬም ይተኮሳል። ከንፈሬም ቀለም ይቀባል። ግን ከዛሬ አምሮብሻልና አንዳንድ ገፋ ያሉ ቁሌታምነቶች ውጪ ምንም አልተፈጠረም። ምንም አልሆነም።
እስከዛሬ ለምን አልተሳሳምንም?
አልወደደኝም?
– ምንድነው ምታስቢው? አለኝ
– ምንም…..
– ካንቺ በጣም የምወደው ነገር ምን እንደሆነ ታውቂያለሽ?
(ምን የኔ ጌታ….ምን? )
– በጣም ስማርት ነሽ….
(ስማርት ፊት….ካልጠፋ ነገር ማንም የሚለኝን ነገር ይለኛል….? ይሄን ሁሉ ሆኜለት ጎበዝ ብቻ ብሎኝ ያልፋል?
መላ ሰውነቴ ኩምሽሽ አለ።
– ታንክስ…አልኩ የግዴን
– ዛሬ ምሽቱ ደስ ይላል…ለምን ትንሽ ወክ አናደርግም? አለኝ ብርጭቆው ውስጥ የቀረችውን እንጥፍጣፌ ማኪያቶ ጨልጦ

ተነስተን ወጣን። ሚገርም ምሽት ነበር እውነትም። ለመሳሳም የተሰራ ምሽት። ትልቅ ጨረቃ፣ ንፋስ የሌለው ግን ቀዝቀዝም ለብም ያለ ውብ አየር። ሰው ያልበዛበት ዛፋም መንገድ።

(አረ ሳመኝ በናትህ!)
– ሴት ልጅ ሰማርት ስትሆን ደስ ይለኛል….
(እግሬን አላየም? ቅርፄን አያይም? …ይሄንን ኬክ ወጥቄ ወጥቄ ሆዴ ተንቀርፍፏል እንዴ? )
– ቀስ በል…በሂል መሄድ አልለመድኩም አልኩት ወሬውን ከስማርትነቴ ለመቀየር…
– ደከመሽ?
– እ…ትንሽ…
– ኡፍ ግን በጣም አምሮብሻል…አለበበስ ደግሞ ስታውቂበት
(እንዲህ ነው ወሬ…!…)
– እውነት? አልኩት ዞር ብዬ እያየሁት
(ጎበዝ ነሽ ከመባል ውጪ ከወንድ ያገኘሁት የመጀመሪያ አድናቆት ነው….)
– እና ደግሞ ይሄ ቀሚስ…ይቅርታ ግን ሰውነትሽ….
(አረ ይቅርታ አያስፈልግም…አወድሰኝ የኔ ጌታ….እስኪነጋ…ክርስቶስ እስኪመጣ አቁመህ አወድሰኝ…አድናቆት የተጠማች የሴት ነፍሴን ደግመህ ደጋግመህ እያወደስክ አረስርሳት…)
– ሰውነትሽ በጣም ያምራል…
(የቱ ጋ የኔ ጌታ? ዘርዘር አድርገዋ..እግሬ ነው..ቂጤ ነው…አይኔ ነው…ወይስ ፀጉሬ…በትንልኛ የኔ ጌታ…ቅኔ ተቀኝልኝ…)
– አውነት? አልኩኝ
– በጣም…በተለይ እግሮችሽ….
– እግሬ ብቻ ነው ደስ የሚልህ? እጁን ጨብጬ ጠየቅኩት። አልቦታል።
– አረ…ኖ…ፊትሽሽ..ፀጉርሽ…በጣም ቆንጆ ነሽ…
ልቤ ምንጃርኛ ጨፈረ።
(በጣም ቆንጆ ነሽ ነው ያለው ወይስ ጆሮዬ ነው? )

እጁን የበለጠ አጥብቄ ያዝኩት።
(የቅንድቤና የእግሮቼ ውበት እመቤት….ያቺ ባለዋክስ ሴትዮ ትመስገን። ባለችበት ትመስገን። ደሞዝ ይጨመርላት። ካስተመር ይብዛላት። አሜን።)

– ብዙ ሰው ግን እህቴን ነው ቆንጆ ናት የሚለው…
– አላምንም….እህትሽ ሰላም ተስፋዬ ምናምን ካልሆነች አላንም…ብትሆንም አንቺ ጥግ አትደርስም
(ሰዎች…ሰከርኩ። በቃላት ብስብስ ብዬ ሰከርኩ….)
– ፎቶዋን ብታይ አንዲህ አትልም…እጆቹን ጭምቅ እንዳደረኩ
– አሳይኛ!
ቆምኩና ስልኬን ከፈትኩ።

የእህቴን ፎቶዎች አሳየሁት።
– አረ በናትሽ…ጫፍሽ አትደርስም! …አለ
– ባክህ አትፎግረኝ…በጣም ታምራለች ….ስልኬን ቦርሳዬ እየከተትኩ መለስኩለት
– በርግጥ ቆንጆ ናት…ማለት ሁሉ ነገሯ ለየብቻው ሲታይ ጥሩ ነው ግን…እንዳንቺ ደም ግባት የላትም..አንቺ እኮ…አንቺ እኮ በጣም ሴክሲ ነሽ….
ፀጉር አልባ እግሮቼ ተንቀጠቀጡ። ሙልጭ ተደርጋ ከተላጨችው የሴትነት ሽንቁሬ ወንዝ ቢጤ መፍሰስ ጀመረ።
ቆም አልኩና ተጠጋሁት።

ሳምኩት።

ከንፈሩን ግጥም አድርጌ ሳምኩት።

(ይቀጥላል)

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

2 Comments

  • dbtjw1968@gmail.com'
    Salehuderes Rega commented on January 30, 2021 Reply

    በጣም አሰተማሪ ነው

  • dbtjw1968@gmail.com'
    Salehuderes Rega commented on January 30, 2021 Reply

    verigood

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...