Tidarfelagi.com

ቂም የሸፈነው እውነት (ክፍል ሁለት)

“እሙዬ ነይ እስኪ……”

“ምን ፈለግክ?”

“አንቺን”

“ሸርሙጣ አይደለሁም።”

“ታዲያ እዚህ ምን ይገትርሻል?”

“ቤቴ ነዋ…..” ብዬ የላስቲክ ቤቴን በእጄ ጠቆምኩት።

“ስንት ዓመትሽ ነው?”

“አስራ አራት” ከመኪናው ወርዶ እየተንገዳገደ ተጠጋኝ።

“300 ብር እሰጥሻለሁ።”

“ሸርሙጣ አይደለሁም አልኩህ እኮ……”

“ሸርሙጣ ነሽ ማን አለሽ? ጎዳና እያደርሽ ምንም አልቀመስኩም ለማለት ነው?” እዚያ ጎዳና ላይ ስኖር ከዛ በላይ ፀያፍ ቃላቶች ሰምቼ አውቃለሁ። የዛን እለት ግን ሰውየው የተናገረው ንግግር ሰቀጠጠኝ። አጠገቤ ያገኘሁትን ድንጋይ አንስቼ ከፍ አደረግኩ

“በዚህ አናትህን ሳልከፍልህ ሂድ ከዚህ ጥፋ”

“ምንም የማታውቂ ከሆነ 1000 ብር እሰጥሻለሁ”

ደጋግሜ የብሩን መጠን ለራሴ አነበነብኩት። በህልሜ እንኳን አስቤው የማላውቅ ዓይነት ነበር። ምን ያህል ፍርሃት ቢያርደኝም ከብሩ መጠን ጋር ሲወዳደር ቀለለኝ። በዛው ቅፅበት ምን እንደማደርግ እቅድ አወጣሁ። ጭንቅላቴ እጄን አላዘዘውም። የመኪናውን በር ከፍቼ ገባሁ። ሲኦልን የዛን ምሽት አየኋት። በአለም ላይ ካሉ አስቀያሚ እና ጨካኝ ፍጥረታት መሃከል ዋነኞቹ ወንዶች መሆናቸውም የዛን እለት ገባኝ። ገና የ14 ዓመት ልጅ ነበርኩ፣ በችግር ሰውነቴ ደቆ የእድሜዬን ያህል ያላደግኩ፣ ምንም የማላውቅ………… ሰው እንዴት በህፃን ህመም ይደሰታል? እየተሰቃየሁ በፈሰሰኝ ደም እንዴት ድል እንዳደረገ ይፈነጫል? እሱ ወዙን ሲያዘንብ እኔ እንባዬ ሲዘንብ እንዴት ሰብዓዊነት አይሰማውም? እንዴት በ1000 ብሩ ስቃዬን ይገዛል? እንዴትስ ያ ደስተኛ ያደርገዋል? ይኼ ፍጡር ወንድ ነው።…… በስቃይና በተስፋ ተሰቅዤ ሊነጋ አካባቢ ወደ ላስቲክ ቤቴ ተመለስኩ። እነ አቢን ቀሰቀስኳቸው። …………… ርሃብ የለም። ልመናም የለም። ገበያ ይዣቸው ወጣሁ። ለብሰውት የማያውቁትን ልብስ ገዛሁላቸው። ካፌ ወስጄ ኬክ አበላኋቸው። ጠግበን ዋልን።

በዚያው ሰሞን በተረፈኝ ገንዘብ መንገድ ላይ ሲቆሙ የማያቸው ሴቶች የሚለብሷቸውን የመሳሰሉ አልባሳት ገዛሁ። ያደርጉታል ብዬ ያሰብኩትን አደረግኩ። ይመስላሉ ብዬ ያሰብኩትን መሰልኩ። ዘወትር ማታ ሲዖል ደርሶ መልስ የኑሮዬ አንድ ክፍል ሆነ። ገንዘብ እየተቀበልኩ ስቃዬን መጨጥ (ለወንዶቹ እርካታቸውን) የየቀን ስራዬ ሆነ። አሁን ገንዘብ ማግኘት ቻልኩ። እንዳቅማችን ቤት ተከራየን። እህትና ወንድሜ ትምህርት ቤት ገቡ።

ወንዶችን አልወድም ገንዘባቸውን እንጂ። ከወንድነታቸው የሚተርፈኝ ስቃይና ላባቸው ነው። ገንዘባቸው ግን የማልፈውን ሲኦል ያስረሳኛል። መንገድ መቆሙን ትቼ ትልልቅ ሆቴል ውስጥ መስራት ጀመርኩ። እንደዋዛ ትልቅ ሴት ሆንኩ። ሃያ አንድ ዓመት ሞላኝ። በዚህ ወቅት ነው ካሳሁንን ያገኘሁት። የሆቴሉ ደንበኛ ነው።

“ቆንጆ እኮ ነሽ እዚህ ቦታ መገኘት አልነበረብሽም::” አለኝ።

“አየህ ተፈጥሮ ቁንጅናን እንጂ የተደላደለ ህይወትን አብራ አልሰጠችኝም::” መለስኩለት።

“የዛሬ ገቢሽን ልስጥሽና እቤትሽ አርፈሽ ተኚ?”

“ይበዛብሃል::”

“እጥፍ ላድርግልሽ!!”

በራሱ መኪና እቤቴ አደረሰኝ።የጠየቅኩትን ገንዘብ ሳያቅማማ ሰጠኝ። በተደጋጋሚ እንዲህ አደረገ። ለዘመናት የሆቴሉ ደንበኛ ሲሆን ከሆቴሉ ሴቶች ጋር ስሙ ተነስቶ እንደማያውቅ ሰማሁ። ከአመታት በፊት ብቸኛ ወንድሙ ከእርሱ ጋር ተጣልቶ በባህር አቋርጦ ወደውጪ ሀገር ሊሄድ ሲሞክር የመሞቱን መርዶ ከሰማ ጀምሮ በየምሽቱ ይመጣል፣ እራቱን ይበላል፣ ይጠጣል፣ ለሴቶቹ ይጋብዛቸዋል፣… … ወደቤቱ ይሄዳል። ከቀናት በኋላ አብሬው እንዳድር በትህትና ጠየቀኝ። እቤቱ ነበር ይዞኝ የሄደው። ከሱ ጋር ካደርኩ በኋላ ወደ ሆቴል ተመልሼ መሄድ አላስፈለገኝም። በየእለቱ ማታ እቤቱ እጠብቀዋለሁ። ሲነጋ ወደቤቴ እመለሳለሁ።

እንዳገባው የጠየቀኝ ቀን እብደት የቀላቀለው ስሜት ነበር የተሰማኝ። ምክንያቱ ባል ማግኘቴ አይደለም። ባል ወንድ ነው ወንድ ደግሞ የገንዘብ ምንጭ ነው። ከዛ ያለፈ አይደለም ለኔ። ካሳሁን ብዙዎች የሚያውቁት ሀብታም ነጋዴ ነው። …… በቃ!! ብር አገኛለሁ። የትኛውም ወንድ እንደሸቀጥ የሚገዛት ሴት መሆኔ ይቀራል፣ እነ አቢዬ ያለስጋት ትምህርታቸውን ይማራሉ፣ በለውጥ ገላዬን እሰጠዋለሁ። ልቤ ያውቀዋል እንደምፈታው። ተጋባን። እህትና ወንድሜን ይዤ እኔ ገንዘብን እሱ ትዳሩን ስንጠብቅ ኖርን።
*********

ሳምንታት አለፉ። ሲመቸው ለቤቱ ፕሮሰስ እንደሚመጣ ቢነግረኝም ካሳሁን አልመጣም ። አልደወለም። በቤቱ ምክንያት ቢመጣና ባየው ተመኘሁ።ቤቱ አስክሬን የወጣበት ቤት መስሎ ረጭ አለ።

የቤቱ ድምቀት፡- ትልቅነቱ፣ የቀለማቱ ስብጥር፣ በውስጡ ያጨቀው ውድ እቃ አልነበረም። ሞገሱን ተገፏል። ካሳሁን የለበትም።

የምግቡ ጣዕም የሰራተኛዋ ጥበብ አልነበረም። ከካሳሁን ጋር የምግብ ጠረጴዛው ላይ መታደሙ እንጂ።

የእንቅልፉ መጣፈጥ የአልጋው ምቾት አልነበረም በካሳሁን እቅፍ ውስጥ ማደሩ እንጂ።

ይሄ ሁሉ የገባኝ አምስት ዓመታት ዘግይቶ ሆነ። የህይወት ዘመን ልምዴንና እውቀቴን ያስከነዳው እውነት ካሳሁን ‘ሴት ልጅ ለገንዘብህ ስትል ትወድሃለች’ ብለው እንደሚያስቡ ወንዶች አልነበረም። ገንዘቡን እንደወደድኩት እንጂ ለእሱ ግድ እንደሌለኝ ያውቃል። ራሱን እንድወደው ነበር አምስት ዓመት ሙሉ ሲጥር የነበረው። የፈለግኩትን ሁሉ እንኳን አጊንቼ እሱ ከሌለበት ባዶ መሆኑን ነበር ያሳየኝ። እድሜውን ካፈራው ንብረት እንደበለጥኩበት አሳይቶኝ እድሜዬን ሙሉ የጓጓሁለት ሀብታምነት ከንቱ መሆኑን ነገረኝ። አብሬው ስኖር ያላየሁት እውነት ያ ነበር።

“ ማንም የኔን ያህል አውቆሽ አያውቅም።” ይለኝ ነበር ሁሌም ሳበሳጨው። አሁን ነው ምን ያህል እንደሚያውቀኝ የገባኝ። ባዶነቴ በፍቅር እንጂ በገንዘብ እንደማይሞላ ያውቅ ነበር። እሱ ብቻ ይሄን ያውቅ ነበር።

ስልኬን አንስቼ ደወልኩለት።

“ሰብሊ ይቅርታ ደንበኞች እያናገርኩ ነው። ቆይቼ እደውላለሁ።” ብሎኝ ስልኩን ዘጋው። ‘ቆይቼ’ ያለው ሰዓት ዘላለም መሰለኝ። ሲሊፐር እንዳጠለቅኩ ተነስቼ ከቤት ወጣሁ። እንዲህ ላብድ የሚመስለኝ ሰዓት እብደቴን የማስታግሰው እህትና ወንድሜ ጋር ስሆን ነበር። አሁን እነሱ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ናቸው። እንድረብሻቸው አልፈልገኩም። ደግሞም ካሳሁንን የአባታቸው ያህል ነው የሚወዱት። በቀስታ እየተራመድኩ ማሰብ ጀመርኩ። አሁን ያለኝን ሁሉ አጥቼ ካሳሁንን ብቻ ማግኘት ተመኘሁ። እግሬን ጭንቅላቴ አላዘዘውም። ወደካሳሁን ቢሮ ሮጥኩ። ርቀቱ፣ አለባበሴ፣ የፀጉሬ መንጨፍረር…….. ምኑም ግድ አልሰጠኝም። ትንፍሼ ቁርጥ ቁርጥ እያለ በሩን ከፍቼ ገባሁ። ሁኔታዬ ያስደነገጣት ፀሃፊው መውጣቱን ነገረችኝ። በደከመ ነፍሴ ወደቤቴ ማዝገም ጀመርኩ። የመጣሁት መንገድ ርቀቱ የታወቀኝ ስመለስ ነው። ብዙ መንገድ ሮጫለሁ። መንገዱ ዳር ድንጋይ ላይ ተቀመጥኩ። ለብዙ ቀናት የረባ ምግብ ያለመብላቴን፣ እረፍት ያለው እንቅልፍ ያለመተኛቴን አሁን ነው ያስታወስኩት። ላዳ ይዤ ወደቤቴ ሄድኩኝ። በሩ ላይ የካሳሁንን መኪና ቆሞ ሳየው ‘እሪሪሪሪረ……’ ማለት አማረኝ። በሩጋ ስደርስ እሱ እየወጣ ነበር። ከላይ እስከታች እያስተዋለኝ

“ስደውልልሽ አታነሺም?”

“ስልኬን ጥዬው ነው የወጣሁት። ቢሮህ እኮ ሄጄ…..”

“አሁን መጥታ ነበር ሲሉኝ ነው ወደቤት የመጣሁት። ሰላም አይደለሽም?” ይዞኝ የመጣው ታክሲ ጥሩንባውን አስጮኸው።

“አልከፈልሽውም እንዴ?” ብሎ እጁን ኪሱ ውስጥ እየከተተ ወደታክሲው አመራ። በዛው የማይመለስ መሰለኝ። ድጋሚ ለሳምንታት የማላየው መሰለኝ። ምን እንዳደረግኩ የገባኝ ካደረግኩት በኋላ ነው። አፌን ጭንቅላቴ አላዘዘውም።

“እሪሪሪሪሪሪ…….” ብዬ አቀለጥኩት። በታክሲውና በኔ መሃከል ባለ እኩል እርቀት መሃል ደንግጦ ዞረ።

“ምን ሆንሽ?” አጠገቤ ዘሎ ደረሰ። ምን እንደምለው ግን ግራ ገባኝ። የእንባዬ ጠብታ መሬቱ ላይ ተከታተለ። ባለታክሲው በጩኸቴ ተደናግጦ መውረዱን ሳይ ደነገጥኩ።

“ምንም አልፈልግም። ሁሉም ይቅርብኝና አትሂድብኝ!!” እንባዬን እየታገልኩ ያወጣሁት ቃል ይሄ ነው።

“አልሄድኩም እኮ ታክሲውን ልሸኘው ነው::”

“አልፈልግም እኮ ነው የምልህ። ቤቱንም ብሩንም ምኑንም አልፈልግም። ሁሉንም አልፈልግም። አልፈልግም በቃ!!” በእንባዬ ታጅቤ አምባረቅኩኝ።

ያልኩት እንዳልገረመው ፤ እንዲህ እንደሚሆን እንደሚያውቅ ሁሉ ፈገግ እንደማለት ብሎ ወደታክሲው ሹፌር ፊቱን አዞረ። መሬት ላይ እየተንከባለልኩ መጮህ አማረኝ። ብሩን ሰጥቶት ሲመለስ በእንባ በተጋረደ ዓይኔ አየዋለሁ።

“ላቆሰልኩህ ቁስል በሌላ በፈለግከው ነገር ቅጣኝ እባክህ ትተኸኝ አት….” ያልኩትን የሰማ አይመስልም። አጠገቤ ከመድረሱ ከንፈሮቼን ጎረሳቸው።

አምስት ዓመት ሙሉ እንዲህ ነበር የሳመኝ?

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...