(የመጨረሻ ክፍል)
“ዶክተር ሰው ይፈልግሻል?”
“ሲሳይ ነው? ትንሽ ታገሰኝ በይውና ተረኛ ታካሚ አስገቢልኝ።”
“ዶክተር ……… ባለቤትሽ ነው።”
“ባለቤትሽ? ኢሳያስ?…………”
“ቢሮዬ ድረስ እየመጣህ ለምን ትረብሸኛለህ ኢሳ?”
“ናፈቅሽኝ!! ከዚህ በላይ ሳላይሽ መቆየት አልችልም።”
ከዩንቨርስቲ ጀምሮ የማውቀው ሰው ነው ኢሳያስ ። ለ6 ዓመት አብሮኝ የቆየ የትዳር አጋሬም ነው። አብረን በኖርንባቸው ጊዜያት መጀመሪያዎቹ አመታት በፍቅር ያጌጡ ነበሩ። እየሰነባበተ ግን ሳንጨቃጨቅ ያለፉ ቀናት ውስን ሆኑ። የሁለት ዓመት ልጃችን በሞት ስትለየን ሰላማችን ይብስ ደፈረሰ። ልጃችን የሞተችው በምግብ መመረዝ ነው። ታማ ስትሰቃይ ሁለታችንም ልንደርስላት አልቻልንም ነበር። ሰራተኛዋ ስትደውልልኝ ስራ ላይ ነበርኩ። ስልኬን እየሰማሁት ቆይቼ ለመደወል አስቤ ተውኩት። ግን ቆይቼም አልደወልኩም። ሌላ ስራ ያዝኩ። እናም ልጄን ሳልደርስላት ሞተች። እሱም በተመሳሳይ ምክንያት ስልክ ሳይመልስ ቀረ። ቆይቼ ስደርስ ዘግይቼ ነበር። ለዚህ በደሌ አንድ ሚሊየን ጊዜ ራሴን ብቀጣውም በቂ አይሆንም። ከኢሳያስ ጋር መወቃቀሱ አቁሳይ ስለነበር በሆነው ባልሆነው ሰበብ እየፈለጉ መነታረክ ሆነ ምሽታችን። ቤቱን ለቆ ከወጣ ሶስት ወር አለፈው።
“ቁጭ ብለን እንድናወራ እፈልጋለሁ።” አለኝ አይን አይኔን በልመና እያየ።
ምንድነው ልለው የነበረው? ‘ውጣልኝ‘ ነበር ሌላ ጊዜ ቢሆን የምለው። አሁን የምትሸሸዋን ሴት አይደለሁም። ምንም ቢሆን የምትጋፈጠዋን ማህደር እየተለማመድኳት ነው።
“እደውልልሃለሁ።” ያልኩትን ያመነኝ አይመስልም። ተገርሞ እያየኝ ተሰናብቶኝ ወጣ። የገባኝ አንድ ነገር ሲሳይ በብዙ ፍጥነት ማንነቴን እያሾረው መሆኑ ነው።
ወደ ቤቴ ገብቼ ሲሳይ ያለኝን አደረግኩ።
«በህይወትሽ የምትሸሺው ነገር ምንድነው? መስታወት ፊት ቁሚና ለራስሽ ንገሪው። እመኚው!! መቀየር የማትችዪውን ነገር መቀበል ነው የሚፈውሰው።» ነበር ያለኝ
የልጄን ፎቶዎች ከደበቅኩበት አወጣኋቸው። በመጀመሪያው ቀን ቀላል አይሆንም ነበር ያለኝ። ቀላል አልነበረም። ሁሉንም ፎቶዎች በፊት የተሰቀሉበት መለስኳቸው። መሸሽም መደበቅም መድሃኒት አይሆንም። ስሸሽ የተጠራቀመው እንባዬ ገደቡን ጥሶ አይኔን አደፈራረሰው። ስልኬ መጥራቱን እንኳን የሰማሁት ብዙ ከጠራ በኋላ ነበር።
«ምን ሆነሻል? አልቅሰሽ አይደለምኣ?» ሲሳይ ነው።
«ነው! አልቅሼ ነው።» እያልኩት ጭራሽ መንፈቅፈቅ ጀመርኩ።
«እህህህ ምን ተፈጠረ ቆይ?» እቤቴ ደጅ ድረስ አድርሶኝ ነበር የተመለሰው። መልስ መመለስ እስኪያቅተኝ ሲቃዬ አነቀኝ።
« በቃ በቃ እሺ መጣሁ። ስልኩን አትዝጊው እያወራሁሽ እደርስልሻለሁ። እኔ አጠገብሽ ሆኜ እንደፈለግሽ እንድታለቅሺ ፈቅድልሻለሁ። እስከዛ ግን ስወድሽ አታልቅሺ?» ብሎኝ ሊያስቀኝ እየሞከረ ከቤቱ ሲወጣ፤ «ብርድ እንዳይመታህ በደንብ ልበስ» ስለው «አትስጊ ካልሲ አጥልቄለታለሁ» ሲለኝ
ታክሲ ሲያናግር
«የኔ እመቤት ደሞ ስስ ፒጃማ ፍለጋ ቁምሳጥኑን ዘረጋግፊው አሉሽ!» ሲለኝ ሲከፍል
«ስንቴ መስታወት አየሽ?» ሲለኝ
ሲደርስ እውነትም ማልቀሴን ትቼ ልቤ ተሰቅሎ እየጠበቅኩት ነበር። በሩን ከፍቼ ተጠመጠምኩበት። ሙሽራውን በሰርጓ እለት ወደ መኝታ ቤታቸው እንደሚያስገባ ሙሽራ አቅፎኝ ወደሳሎኑ ገባ! ማልቀሴን እረሳሁት። ሳሎኑ ውስጥ የተሰቀለውን የእኔንና የኢሳያስን የሰርግ ፎቶ አይቶታል። ግን አልጠየቀኝም። ሌላ ነገር እያወራ ሲያስቀኝ ቆየ።
«ሲስ?»
«ወዬ እመቤቴ?»
«ስለእኔ ማወቅ ያለብህ ነገር አለ።»
«ምኑን ትነግሪኝ? በፎቶ አሳየሽኝኮ አስጎበኘሽኝ።» አለ ወደፎቶው እየጠቆመኝ።
«እየቀለድኩ አይደለም ሲስ! ከምሬ ነው።»
« እሺ እመቤቴ ንገሪኝ! ይኸው! Am all yours!»
ስለኢሳያስ እና ስለልጄ ነገርኩት ብቻዬን ስለፈልፍ ሲያባብለኝ እና ሲደባብሰኝ ብቻ ቆየ። ብዙ ደቂቃ እቅፉ ውስጥ ካቆየኝ በኋላ
« ባንቺ ደረጃ ካሉ ሴቶች ይልቅ አንዲት ምንም የማታውቅ የቤት እመቤት የሰመረ ትዳር ለምን የሚኖራት ይመስልሻል?» አለኝ
« ጭራሽ እንደዛ ስለመሆኑም እንጃልህ! ምን ለማለት ፈልገህ ነው?»
«ይሄ ሀቅ ነው ብዙ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በጋራ ስምምነት ባስቀመጥነው ደረጃ ብዙዎቹ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያሉ ሴቶች በትዳራቸው ስኬታማ አይደሉም።»
«ምናልባት ከትዳራቸው ሌላ ትኩረታቸውን የሚሻ ሌላ ስራ ስላላቸው?»
«እኔ አይመስለኝም። እነዛ በትዳር ውስጥ ለፍቅር ወይ ለልጃቸው አልያም በሌላ ምክንያት ዝቅ ማለትን ያውቁበታል። እስኪ አንድ ጥያቄ ልጠይቅሽ? ክርስቶስ ለባል የሰጠው ትእዛዛ ሚስትህን ክርስቶስ ቤተክርስትያንን በወደደበት ፍቅር ውደድ የሚል ነው። ያ ማለት ነፍሱን እስከመስጠት። ለሚስት ያላት ግን ሚስት ለባሏ ትገዛ ነው። የቱ የሚከብድ ይመስልሻል?» ሳልመልስለት ራሱ ቀጠለ።
«ባትወጂም መገዛት ትችያለሽ። ወደሽ አለመገዛት ግን በፍፁም አትችዪም።» ዝም ነበር መልሴ። ከአንዱ ስሜት ወደሌላው መሻገር ምንም አይከብደውም። መከፋቴን አስረስቶኝ አመሸን።
«ያው እንደምታውቂው ድንግል ነኝ። በዛ ላይ ቁስሉ ራሱ ሰበብ አይፈልግም።» ብሎኝ እኩለ ለሊት አልፎ ወደ ቤቱ ሄደ።
★ ★ ★
በሚቀጥለው ቀን በስራ የደከመ ሰውነቴን እየጎተትኩ መኪናዬጋ ደረስኩ። መሽቷል። እቤቴ ገብቼ ማረፍ ነው ያማረኝ። ስልኬ ጠራ። ሲሳይ ነው።
“እራት በላሽ?”
“አልበላሁም። ግን ደክሞኛል በጣም።”
“እማ ቆንጆ እራት ነው የሰራችው። እየጠበቀችሽ ነው።”
“ትቀልዳለህ እንዴ? ማን ነኝ ብዬ ነው እናትህ ቤት እራት ልበላ የምመጣው?”
“ማንም መሆን አይጠበቅብሽም። ሰው መሆን የእማን እራት ለመብላት በቂ ነው።”
★ ★ ★
አመመኝ። የቤተሰቡ ፍቅር አሳመመኝ።
“ደህና ነሽ ግን?”
“ምነው ደስ አላለሽም?”
“ምነው ልጄ ከፋሽሳ?”
ይሉኛል እየተቀባበሉ ። አመመኝ። የሚታገለኝን እንባ እየዋጥኩ የደመቀ እራት በላሁ። የቤተሰብ ፍቅር ህመሜ፣ ንጭንጬ ፣ ሽንፈቴ፣ ድክመቴ……… መሆኑ አልገባቸውም። ይሄን ፍቅር በዘመኔ አይቼው አንጊንቼው እንደማላውቅ አያውቁም። የሲሳይ እናት ፊቴን እያገላበጡ፣ ፀጉሬን እየዳበሱ የሆንኩትን ሲጠይቁኝ እናት እንደማላውቅ አያውቁም። አባትየው እየደጋገሙ ‘ልጄ‘ ሲሉኝ። አይኑ ለማያይ ያአረጀ አያቴ እየተላላኩ እና ምርኩዝ ሆኜ እንዳደግኩ አልገባቸውም። እህቶቹ እግሬ ስር በርከክ እያሉ ‘ሲሳይ አስከፍቶሽ ነው? እሱ እኮ ክፍት አፍ ነው።” ሲሉኝ አያቴ ሞቶ የአክስቶቼ ልጆች እንደምናምንቴ እየቆጠሩኝ ተምሬ መጨረሴን አያውቁም። ብዙ አወሩኝ። እቤት ይዟት የመጣ ብቸኛ ሴት መሆኔን ነገሩኝ።
★ ★ ★
እንደምንም ያመቅኩትን እንባዬን መኪናዬ ውስጥ ሲሳይ እቅፍ ውስጥ ዘረገፍኩት። አላባበለኝም። እየደጋገመ እንባዬን እየጠረገ ፣ ፀጉሬን እያሻሸ ጠበቀኝ።
“አውሪኝ። የተሰማሽን ሁሉ አውሪኝ።” አለኝ። ሲቃዬ አላስወራ አለኝ።
ጣቶቹን ፀጉሬ ውስጥ ሰዶ ወደራሱ አስጠጋኝ። ይበልጥ ሲቀርበኝ ከመቃወም ይልቅ ልስመው ፈለግኩ። በሌላኛው እጁ እንባዬን ከጉንጬ ላይ ጠራረገው። ከንፈሩ ከንፈሬን የሚነካበት ሰዓት ረዘመብኝ። መጠበቅ አቃተኝ። ሳምኩት። ነፍስ በሚያሳርፍ መሳሙ ለደቂቃዎች ሳመኝ።
“ምንም ይሁን ንገሪኝ፣ አንድም ሳታስቀሪ የተሰማሽን ንገሪኝ፣ አንቺ ራስሽን ከምትረጂው በላይ እረዳሻለሁ። እንባሽ ከመጣ አልቅሺ ብቻ ልስማሽ!” አለኝ መረጋጋቴን ሲያይ
“አሁን እኮ መሽቷል። ሌላ ቀን ላውራህ?”
“ማደር ካለብኝ እየሰማሁሽ አድራለሁ።”
አውርቼ የማላውቃቸውን ብዙ ነገሮች ነገርኩት። ሳለቅስ አያባብለኝም። እጄን እየደባበሰ ይሰማኛል። ስለቤተሰቦቼ ሁሉንም ነገርኩት። አያቴ ሲሞት ከልጅነቴ ጀምሮ ምርኩዙ ሆኜ ስላደግኩ ያለውን ንብረት ሁሉ ተናዞልኝ ነበር የሞተው። በንብረቱ ሳቢያ ዘመዶቼ ሁሉ በፊት ይጠሉኝ ከነበረው በብዙ እጥፍ ጠሉኝ።
የደበቅኩት የለም ሁሉንም ነገርኩት። ያልሰማኝ የለም። ያለፍትን ውሳኔዎቼን በሙሉ ቆም ብዬ እንዳይ አደረገኝ። እቤቴ ስገባ እንደሌላው ቀን ኢሳያስ የሌለበት ወና ቤት አላስጠላኝም። አልጋዬ ላይ ጋደም ብዬ ከራሴ ጋር አወራሁ።
“በራስሽ መተማመን ካለብሽ ራስሽን እወቂው። ጠንካራ ጎንሽን እና ድክመትሽን ለዪ፣ ድክመትሽን በጠንካራው ነገርሽ ለመሸፈን አትሞክሪ፣ ተጋፈጪው ማሻሻል ያለብሽን አሻሽዪ፣ ያለፈ ቁስልሽን ተቀበዪው እመኚው እንጂ አትሽሺው።” ያለኝን የሲሳይ ንግግር አሰብኩት። ደስ ብሎኝ ተኛሁ።
★ ★ ★
በጠዋት ወደስራ ስገባ ሲስተር ቀለምን ቀድማኝ አገኘኋት ። ጠርቻት ለልጆቿ የሆነ ነገር እንድታደርግ የተወሰነ ገንዘብ ሰጠኋት። እጄን እያገላበጠች ስትስም እንባዋ ነካኝ። አቀፍኳት። እስከዛሬ ልረዳት ባለመቻሌ ራሴን ረገምኩት። እቤቷ ሄጄ ልጆቿን ላይላት ለሳምንቱ መጨረሻ ቀጥርያት ስራ ጀመርን።
በህይወቴ ከመቼውም ጊዜ በላይ ደስተኛ ነኝ። ግን ደግሞ መንታ መንገድ ላይም ነኝ። ሲሳይና ኢሳያስ!!
የብዙ ዓመት አለሁሽ ባዬ ግን በራሴ ትህምክትና ፍራቻ ያልተረዳሁት ኢሳያስ
ሳልነግረው የማስበው እና የሆንኩት የሚገባው ሲሳይ
መወሰን ነበረብኝ። ማናቸውንም መምረጥ ህመም አለው። ፈሪ ግን አይደለሁም። አልሸሽም።
★ ★ ★
ውሳኔዬን መጀመሪያ ለሲሳይ ማሳወቅ ፈለግኩና አገኘሁት። ነገርኩት።
“እርግጠኛ ነሽ?” አለኝ መጀመሪያ ግራ እየተጋባ
“አዎን። መቼም እንደዛሬ እርግጠኛ የሆንኩበት ውሳኔ የለም። ” መለስኩለት
“አሁን ነው የገረዝሽኝ። ያማል።” አለኝ ድምፁን ዝግ አድርጎ
“አዝናለሁ። አንተ በህይወቴ ፈጣሪ የላከልኝ መልዓክ ነህ። ባልጎዳህ በወደድኩ። ” አልመለሰልኝም። ግንባሬን ሳመኝ። ለመጀመሪያ ጊዜ ሲከፋው አየሁት። ሊሄድ መንገድ ከጀመረ በኋላ መለስ ብሎ እንዲህ አለኝ
“ኢሳያስን እድለኛ መሆኑን ንገሪው!!”
★ ★ ★
አሁን ጨረስን።
6 Comments
ልብ አንጠልጣይና ትኩረትን ደስ በሚል ሁኔታ የሚስብ !
እሱ ከተገረዘበት ይልቅ ዶ/ር የተገረዘችበት ቢላዋ ስል ነበር፡፡እናመሰግናለን በርቺ!
ኤሳያስ ምን አይነት ሰው ነው። ሆ
ሁሉም ፅሁፎችሽ ኣሪፍ ናቸው በጣም ወደናቸዋል እግዚሄር ይስጥልን….ግን ኣትዘግዪብን pleaseee
ውይ በእመቤቴ ባያልቅ ደስ ይለኝ ነበር ባትሰስቺ ምናለ ብታረዝሚው እንደዛ ነው የተሰማኝ ደስ ይላል በርቹ
በጣም ልብ የሚነካ , እራስን መሆን የሚያስመኝ ግሩም አቀራረብ አዘል ታሪክ ነበር። እጆችሽ ይባረኩ።