Tidarfelagi.com

ስንቴ ገረዝኩት (ክፍል ሁለት)

“ዶክተር? ያው ሰውዬ ነው የላከልሽ………” ሲስተር ቀለም በፈገግታ በደመቀ ፊት ጠረጴዛዬ ላይ በፎይል የተጠቀለለውን ምሳ አስቀምጣው ወደ በሩ ተመለሰች

“ሲስተር ከዛሬ በኋላ የሚያመጣውን ምሳ እንዳትቀበሉት።” አልኳት

ለሁለተኛ ጊዜ ታክሞ ከሄደ ጀምሮ ሶስት ቀኑ ነው። የምሳ ሰዓት እየጠበቀ ምሳ ይልካል። ጠዋት ፅዳቶቹ አፅድተው ሲጨርሱ አበባ ይልካል።

“አበባውንም ነው ዶክተር?”

“አዎን። ምንም ነገር!!”

“እሺ!!” ብላኝ ወጣች

ሲስተር ለምንድነው የምትሽቆጠቆጥልኝ? ስለምታከብረኝ? ደሞዝዋን ስለምከፍላት? አለቃዋ ስለሆንኩ? እንጂ አትወደኝም…………… ትጠላኝም ይሆናል። ይሄ የተረገመ ሰው ምን እንዳስብ እያደረገኝ ነው?

★ ★ ★

ሆዴ ምግብ አስፈልጎታል። ሆስፒታሉ አቅራቢያ ያለ ሬስቶራንት እራቴን ለመብላት አዝዤ ተቀምጫለሁ። ከየት መጣ ሳልል ከፊቴ ያለውን ወንበር ስቦ ተቀመጠ።

“ማሂ……ዬ……… ?” አለ በተሟዘዘ አጠራር

“አንተ ሰው ለምን አትተወኝም?”

“አቶ ሲሳይ ታፈሰ። ማዕረግ ያለኝ ሰው ነኝ እሺ።”

“Whatever አቶ ሲሳይ ምን እያሰብክ እንደሆነ አልገባኝም። እኔና አንተ ግን ምንም መሆን የምንችል ሰዎች አይደለንም።”

“ምክንያት? በእድሜ ስለምትበልጪኝ?”

“አቤት? ”

“በ18 ዓመትሽ ዩንቨርስቲ ብትገቢ፣ 7 ዓመት ዶክተር ለመባል ብትማሪ……”

“ዶክተር ለመሆን ” አቋረጥኩት

“ስፔሻሊስት ለመባል የሆነ ዓመት… …… ይሄን ሆስፒታል ከከፈትሽ 6 ዓመት… …… በስሱ 37 የግልሽ ነው። ”

እንዲያውቅብኝ ባልፈልግም ተናድጃለሁ። ለምን ተናደድኩ? ትክክለኛ እድሜዬን ስለነገረኝ። እና ምን አናደደኝ? ምክንያት እንኳን የለኝም።

“ቁስልህ ዳነልህ?” ወሬውን መቀየር ነው ፍላጎቴ

“እየደረቀ ነው። ላሳይሽ?” ከመቀመጫው ብድግ አለ

“ኸረ አንተ ሰው?” ለመቀመጥም ለመነሳትም በቀረበ አኳኋን አየሩ ላይ ተንሳፈፍኩ

“አየር ላይ ነሽ! አረፍ ትዪ……” ብሎኝ ተመልሶ ተቀመጠ

ያዘዝኩት ምግብ መጣ። ተነስቶ እጁን ታጥቦ እስኪመጣ ጠብቂኝ ባይለኝም ጠበቅኩት። የጠቀለለውን ሊያጎርሰኝ ዘረጋ
“ጉርሻ አልወድም።” አልኩት

“እንዴ? በሞቴ? በፍቅራችን?” ሆነ ብሎ ሬስቶራንት ውስጥ ያለው ሰው እንዲሰማ ጮክ ብሎ ነው የሚናገረው። ሰዎች እየዞሩ ያዩናል። ግማሾቹም ፈገግ እንደማለት ይላሉ። ጎረስኩለት።

“ማሂዬ ለክብርሽ ይሄን ያህል አትጨነቂ። ……” አለ የተናገረው ተራ ነገር እንደሆነ ሁሉ ለሌላ ጉርሻ እየተሰናዳ። ተበሳጭቻለሁ። ይበልጥ ያበሳጨኝ ደግሞ ያለው እውነት መሆኑ ነው።

“ክብር አንጃ ግራንጃህን ተወኝ። ባለትዳር ነኝ ለባለቤቴ …………”

ሳቁ አቋረጠኝ። አስቂኝ ተረት እንደነገሩት ህፃን ተንፈቀፈቀ::

“ምን ያስቅሃል?”

“ባለቤትሽ ነዋ ያሳቀኝ ሃሃሃሃ ”

“ምን ለማለት ፈልገህ ነው?”

” እንዳንቺ አይነት ሴቶች ወይ አላገቡም፣ ወይ አግብተው ፈተዋል፣ ወይ ከባላቸው ጋር ሰላም አይደሉም።”

“እኔ ምን ዓይነት ሴት ነኝ?”

“ካልኳቸው ምድብ ውስጥ ከሌለሽ ልቀጣ? እ?” መልሴን ጠበቀ

መልስ አልነበረኝም። ተነስቼ ጥዬው መሄድ ነበር ፍላጎቴ እግሮቼን ማዘዝ አቃተኝ። ሽንፈቴን መቀበልም መሰለኝ። ልከራከረውም አቅሙ አልነበረኝም።

“እኔ ምን አይነት ሴት ነኝ? ” ድምፄ የቅድሙ ጥንካሬ የለው

“እውቀትና ደረጃዋን ድክመትና ሽንፈቷን ለመሸፈን የምትጠቀም ዓይነት ሴት”

ከዚህ በላይ መስማት የሚያሳምመኝ መሰለኝ። ተነስቼ ስወጣ ድምፁ ተከትሎኛል።

“አየሽ አንቺ ይህቺ ነሽ። ትፈረጥጫለሽ።”

እኔ ምን አይነት ሴት ነኝ? የትኛውን ሽንፈቴን ነው በደረጃዬ የሸፈንኩት?
★ ★ ★

ወትሮም ለእንቅልፍ እምብዛም የሆነው ዓይኔ ጭራሽ አልከደን አለ። እቤቴን ጠላሁት። ልብሴን ለመቀየር ካልሆነ በቀር አዳሬም ሆስፒታል ከሆነ ሰነባበትኩ። ምግቤንም የምመገበው እዛው እያስመጣሁ ሆነ። ከዛ ቀን በኋላ ሲሳይን አላገኘሁትም። ከዛ ቀን በኋላ ግን ስላወራናቸው ነገሮች አለማሰብ አቃተኝ። ሁኔታዬን ይብስ ያባባሰው ደግሞ ከቀናት በፊት የገጠመኝ ነገር ነው። ዶክተር ሰይፈ!!! በግምት የ12 አመት ልጅ የምትሆን ህፃን በዊልቸር እየገፋ ሲያልፍ ነበር ያየሁት። ደሜ ሰውነቴ ውስጥ ሲቀዘቅዝ ታውቆኝ ነበር።

«ሲስተር? ዶክተር ሰይፈ ልጅ አለው እንዴ? » ቢሮ እንደገባሁ ጠየቅኳት። ጥያቄዬ ይሁን ሰይፈ የትኛው መሆኑ ግራ ያጋባት አልገባኝም። « ዶክተር ሰይፈ የህፃናት……………»

«እኮ ገብቶኛል። መጠየቅሽ ገርሞኝ ነው። አዎን ሁለት ሴት ልጆች አሉት። አንዷ ልጁ የመኪና አደጋ ደርሶባት she is totally paralyzed እሱ ነው የሚንከባከባት። አይኗም የማየት አቅሙ እየተዳከመ ነው።» አነጋገሯ ውስጥ ያለው ድምፀት ያሳምማል። አንቺ ምን ግድ አለሽ አይነት ነው።

« ሚስቱስ?»

«ህምምም……. ሚስቱ እኮ ሞታለች ዶክተር!»

« ለምን አልነገራችሁኝም? እንዴት አንድ ሰው አይነግረኝም?» ፀፀቴን ማራገፊያ አጥቼ እንጂ እሷ ላይ የምጮህበት ምክንያትም መብትም የለኝም።

« ምን ብለን? ዶክተር አንቺ ልብ ስለማትዪ እንጂ እኮ ለህክምና እዚህ ትመላለሳለች።» ብላኝ በመገረም እያየችኝ ወጣች።

ኡፍፍፍፍፍፍፍ በየሱስ ስም ምንድነው የሰራሁት? ዶክተር ሰይፈ በሙያው ማንም እንከን የማያወጣለት ጎበዝ ነው። በተደጋጋሚ እያረፈደ እና እየቀረ ስላስቸገረ ቦርዱን ሰብስቤ ከስራው እንዲባረር ያደረግኩት ቀን ያሳየኝን ፊት ትርጉም የምረዳው አሁን ነው። ምክንያቱን እንኳን ሊነግረኝ የደከመው ነበር የሚመስለው። እሺ ብቻ ነበር ያለኝ። ከቦርድ አባላቱ አንዱ ምክንያቱን እንድሰማው ጠይቆኝ ነበር። «ተውት ምክንያቴን ለእናንተ እያስረዳሁ ህመሜን አላበዛም። ለእስከዛሬው ቆይታችን አመሰግናለሁ!» ያለው በሰአቱ ምን ያለ መስሎኝ ነው ከምንም ያልቆጠርኩት? እንዴት ግን አንዳቸው እንኳን ልጁን እያስታመመ ነው አይሉኝም? ይሄን ያህል ድንጋይ ልብ ያለኝ ነው የምመስላቸው? ይጠሉኛል ማለት ነው አይደል?
ማሰብ ይደክማል እንዴ? ማሰብ ደከመኝ:: ስልኬ መልዕክት መቀበሉን ነገረኝ። ከፈትኩት። የማላውቀው ቁጥር ነው።

“ሁሉም ሰው የራሱ የሆነ አይነኬ የህይወት ክፍል አለው። ያን ሽሽት የሆነ ነገር ውስጥ ይደበቃል። ሌት ተቀን ህሙማንን ማገልገልሽ ለብዙዎች ታታሪነትሽን ይነግራቸዋል። ስራሽ መደበቂያሽ መሆኑን ግን አሳምረሽ ታውቂዋለሽ።”

ከሱ ውጪ ማንም አይሆንም። ቁጥሩን ደወልኩበት። ይሄ ደግሞ ሊያሳብደኝ ነው እንዴ ሀሳቡ?

“ምንድነው ከኔ የምትፈልገው? ምንድነው ግን ችግርህ?”

“ደህና እግዜአብሄር ይመስገን!! ምሳ እንኳን አይመቸኝም። እራት ቢሆንልኝ እመርጣለሁ።” አለኝ ዘና ብሎ።

ምን ልለው ነበር የደወልኩት? ቁጣዬን ምላሴ ላይ ምን ያልከሰክሰዋል?
“እራት ልጋብዝሽ?” አለኝ ዝምታዬን ተከትሎ። ምን እንደምመልስለት ግራ ገባኝ።

“ማሂ ፕሊስ?……… እኔ ደስ ብቻ ነው የሚለኝ። ዶክተር ማህደር እራት ተጋበዘችልኝ ብዬ ቀላል ሴት የሆንሽ አይመስለኝም።” የማስበውን እኔ ከስቤ ሳልጨርሰው ከሱ አፍ እሰማዋለሁ።

“የባለፈው ሬስቶራንት 12 ሰዓት ላይ ላግኝሽ! ውብ ቀን ዋዩ!!” ብሎኝ እንቢም እሺም ሳልለው ስልኩን ዘጋው።

ስንቴ ገረዝኩት (ክፍል ሦስት)

3 Comments

  • Sifenmamo@gmail.com'
    ሲፈን ማሞ commented on December 6, 2017 Reply

    በእውነት ግሩም ነው ቀጣዬን ክፍል እስካነበው ቸኮልኩ !

  • dagimdiriba586@gmail.com'
    ዳግም commented on December 8, 2017 Reply

    ኧረ በጣም ደስ ይላል ቀጣዩን ክፍል በጉጉት እንጠብቃለን

  • ጽጌ ብርሃኑ commented on December 25, 2017 Reply

    ጐበዝ በርቺ በጣም ደስ የሚል ጽሁፍ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...