Tidarfelagi.com

‹‹ስቀና….››

የታሪክ ሃሳብ፡ ዶርቲ ፓርከር ‹‹The Sexes› (1926)

አኩርፌዋለሁ።

ሳሎኔ እንደገባ ‹‹ተቀመጥ›› ብለውም ሶፋዬ ላይ አኩርፌ በተቀመጥኩበት ቁልቁል ያየኛል።ፈራ ተባ ይላል፣ አይኑ አይኔን ይሸሻል። ከገባ ከሁለት ቃል በላይ ደፍሮ ማውጣት ተስኖታል። ፈርቶኛል። ይሄንን ታላቅ የኩርፊያ ደመና በምን እንደሚበትነው ስለጨነቀው ፈርቶኛል። የልብ ልብ ተሰማኝ።

ቁጭ ሳይል፣ ‹‹ማስቲካ ትፈልጊያሽ?›› አለኝ። የማስቲካ ነገር ስለማይሆንልኝ ማባበሉ ነው።
ሞኝህን ፈልግ።
‹‹አልፈልግም…አመሰግናለሁ›› አልኩ ቀና ብዬ ማስቲካውንም፣ እሱንም አፈራርቄ እያየሁ።
‹‹ውይ …ለካ አንቺ የምትወጂው ፖፖቲን ነው….ይቅርታ…ረስቼው የገዛሁት ፋይቭ ብቻ ነው…አንቺ ደግሞ ፋይቭ ጋዝ ጋዝ ይለኛል ትያለሽ….አይደል?›› አለ ቀስ ብሎ ሶፋው ላይ፣ አጠገቤ እየተቀመጠ። በመሃከላችን ያለውን ክፍተት በማስቲካ ልስጥሽ አጥብቦ ኩርፊያየን እንዳያተነው፣ንዴቴን እንዳያበርደው ሳላስጠጣ ፈ…ቅ አልኩና ዝም አልኩት።
‹‹ፖፖቲን አለሽ?….›› ራቅ ብዬ መቀመጤን እንዳስተዋለ እያስታወቀበት ጠየቀኝ።
‹እ…?››
‹‹ፖፖቲን አለሽ ወይ….››
‹‹እንጃ…››
‹‹ማለቴ…ካለቀብሽ..ወይ ከሌለሽ ሮጥ ብዬ ገዝቼ ላመጣልሽ እችላለሁ….እ?››
‹‹አመሰግናለሁ ግን ይሄን ያህል ምን አስጨነቀህ…ደሞ ለማስቲካ….ግን በጣም አመሰግናለሁ…ማለቴ ለሃሳቡ…አመሰግናለሁ…›› የማወራው ግድግዳውን እያየሁ ነው።
‹‹ናፍቆትዬ…በናትሽ አመሰግናለሁ አመሰግናለሁ አትበይኝ….!›› ሊጠጋኝ እየሞከረ ተናገረ። ሶፋው ጠረፍ ላይ ጠልጠል ብዬ እስክቀመጥ ሸሸሁት።
‹‹አውቀሽ ልታናድጂኝ ነው እንደ እንግዳ አመሰግናለሁ አመሰግናለሁ የምትይኝ አይደል…?በናትሽ ተይ…›› ድምፁ ከፍ አለ።
እየጮኸ ነው? እየጮኸብኝ ነው?
‹ምን አድርጌህ ነው የምትጮህብኝ? ተው እንጂ…! ሆሆ….ረጋ በል …. አመሰግናለሁ መባል እንዲህ የሚያናድድ ነገር ነው እንዴ? ሆ….አይመስለኝም ነበር….ለማንኛውም….ይቅርታ ስላስቀየምኩህ…..ግን አመሰግናለሁ ማለት ስድብ መሆኑን አላውቅም ነበር…..ለማንኛውም አትጩህብኝ!››

. ‹‹እንዴ…መች ጮህኩ? ….ቀላል ነገር ነው እኮ ያልኩት….የምትወጂውን ማስቲካ ሄጄ ልግዛልሽ ማለት…..እስቲ አሁን ምኑ ነው እንዲህ የሚያስቆጣው?…››
‹‹ማነው የተቆጣው?›› ዞሬ እያየሁት ተናገርኩ። ዝም አለ።
‹‹እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ሰውን ለማይረባ ነገር…ያውም ለማስቲካ በዚህ ምሽት ወደ ውጪ ሄደህ ግዛልኝ ብሎ መላክ ተገቢ አይደለም….ላለማስቸገር ነበር ተው ያልኩት….ባንተ ቤት ወንጀል ከሆነ አላውቅም…ምናልባት ምንም የማይገባኝ ደደብ ሴት ስለሆንኩ ይሆናል…እንዲህ አይነት ነገር አይገባኝም…››

ከልክ በላይ ሲበሳጭ እንደሚያደርገው በረጅሙ ተነፈሰና፣
‹‹ናፍቆት፣ ወጥቼ ማስቲካውን እንድገዛልሽ ትፈልጊያለሽ አትፈልጊም?›› አለኝ።
‹‹ወይ አምላኬ…! እዚህ ከእኔ ጋር መቆየት ይሄን ያህል ከደበረህ ለምን በግልፅ አትናገርም…?መውጣት ፈልገህ ከሆነ ውጣ…በማስቲካ አታሳብ!››
‹‹ናፍቆትዬ በናትሽ…ስወድሽ እንዲህ አትሁኚ…›› እጆቹን ወደ ትከሻዬ ሰደደ። ሊነካኝ እየሞከረ ነው።
‹‹እንዴት አልሁን? እንዴት ስሆን አየኸኝ?››
‹‹ይሄው ቀኑን ሙሉ እንዲሁ ስታስጨንቂኝ ነው የዋልሽው…ዛሬ ስንቴ ደውዬልሽ አንስተሸ በግድ ከሁለት ቃል በላይ አልወጣሽም…ከሄሎ እና ቻው ውጪ ምን ብለሽኛል..?…ጭንቅ አለኝ እኮ የኔ ማር…››

የኔ ማር ሲለኝ አንደ ሰም ስለምቀልጥ ሊያባባኝ እየሞከረ ነው። ሰምህን ፈልግ።

‹‹እንዲህ ደስታ እንዲርቅህ በማድረጌ አዝናለሁ….›› አልኩት። ‹‹ማለቴ…ከእኔ ጋር ጊዜ ማሳለፍ የሚጨንቅህ ከሆነ እዚህ ምን ታደርጋለህ…ከምትደበር ለምን ሌላ ቦታ አትሄድም….? እርግጠኛ ነኝ….መሆን የምትፈልግባቸው ብዙ ቦታዎች ይኖሩሃል….የማትደበርባቸው….ችግር የለውም….ሂድ….እኔ የሚያሳዝነኝ ዛሬ ማታ ቤት እመጣለሁ ስትለኝ ሁሉን ነገር ትቼ…ጓደኞቼን ፈንግዬ አንተን ስጠብቅ መዋሌ ነው…..ፊልም ልንገባ ነበር….ቢሆንም ግድ የለም….እዚህ ከሚደብርህ ደስ የሚልህ ቦታ ብትሄድ እመርጣለሁ…..ማለቴ…እዚህ ቁጭ ብለህ ከምትደበር….››

‹‹አልደበረኝም!›› ብሎ ጮኸ። ድምፁ ውስጥ መማረር ሰማሁ። እያበሳጨሁት ነው።
‹‹አልደበረኝም…የትም መሄድ አልፈልግም….የኔ ማር…በናትሽ…በናትሽ ምንድነው ያጠፋሁት….? ንገሪኝ በናትሽ…››
‹‹ስለምን እንደምታወራ አልገባኝም….››
‹‹ገብቶሻል…በሆነ ነገር አናድጄሻለሁ…ንገሪኝ…ንገሪኝና ይቅርታ ልጠይቅሽ…በናትሽ….››
‹‹ምንም የለም…ቢኖርም ልነዘንዝህ አልፈልግም…›› አልኩ አይኖቹን እያየሁ። ይለማመጡኛል።

‹‹ልነዘንዝህ አልፈልግም ማለት ምንድነው? ለምንድነው እንደዚህ የምታወሪኝ….በናትሽ ተይ…››
‹‹እንዴት አወራሁህ ደግሞ?››
‹‹ታውቂያለሽ….የማወራውን ነገር ሁሉ እንቅፋት እያደረግሽ እያዋራሽኝ እንደሆነ ታውቂያለሽ…..
‹‹ማነው እንቅፋት ያደረገው…? ››
‹‹አንቺ ነሻ!››
‹‹ለምንድነው እንደዛ ማደረግው…?››
‹‹እኔ ምን አውቄ….!››

‹‹ካላወቅህ ዝም በላ….ሆ….ቤቴ ድረስ መጥተህ እንቅፋት ብለህ ትሰድበኛለህ? ትንሽ አይከብድህም?››
‹‹ማሬ አልሰደብኩሽም….እንዴት አንቺን እሰድባለሁ? ››
‹‹አይ ቅቤ ቀባኸኝ እንጂ!››
‹‹እሺ ይቅርታ…እንደዛ ማለቴ አልነበረም….ይቅርታ አድርጊልኝ በቃ…አታደርጊልኝም?…››
‹‹አረኩልህ አላረኩልህ ለውጥ የለውም…››አልኩት ተለማማጭ ፊቱን ሽሽት አንዲት ከሶፋው ጨርቅ አፈንግጣ የወጣች ክር መዝዤ እያፍተለተልኩ።
‹‹ለነገሩ ላንቺ ምንም ለውጥ የለውም….ጠልተሽኛል….ስለጠላሽኝ ምንም አይመስልሽም….››

ቀና ብዬ አየሁት። ካንጀቱ ነው?

‹‹ማነው ጠልታሃለች ያለህ ? ለምንድነው የምጠላህ?››
‹‹እሱን እኮ ነው የምጠይቅሽ ያለሁት….›› አለ ፍዝዝ ብሎ እያየኝ። ‹‹ ጥፋቴን ለምን አትነግሪኝም…የኔ ማር፣ አስቀይሜሻለሁ? ስልክ ላይ እንደዛ በረዶ ስትሰሪብኝ ጭንቅ ሲለኝ ዋለ…አንድ ስራ አልሰራሁም ዛሬ…አንድ ስራ!.››
‹‹ስራህን በማደናቀፌ እዝናለሁ….እርግጠኛ ነኝ ሌላ ሴት ብትሆን እንዲህ አታደርግህም…ማለቴ ስራህን አታስተጓጉልም››
‹‹እንደዛ አላልኩም!››
‹‹ተውንጂ! ታዲያ ምንድነው ያልከው? እኔ የሰማሁት እንደዛ ነው እንግዲህ…ድድብናዬ ይሆናል….››

በድንገት ብድግ አለ።
‹‹በይ ተይው…ዛሬ ምንም አልሆነልኝም! የምናገረው ሁሉ ጭራሸ አዲስ ማገዶ እየሆነሽ ነው…..ብሄድልሽ ይሻልሽ ይሆን?›› በቁሙ ጠየቀኝ።

‹‹ደስ እንዳለህ ሁን….ልብህ ተሰቅሎ እዚህ ከምትቀመጥ ለምን ደስ የሚልህ ቦታ አትሄድም…የማይደብርህ ቦታ? አለ አይደል…ለምሳሌ ኤደን ታምሩ ቤት!…እርግጠኛ ነኝ በፈንጠዚያ ነው የምትቀበልህ…..››
‹‹ኤደን ታምሩ? የትም መሄድ አልፈልግም…ለምንድነው ኤደን ጋር የምሄደው? በጣም ነው ምታስጠላኝ….››
‹‹ተውንጂ!?….›› ድምጼን ከፍ አድርጌ፣ ብስጭት ብዬ መለስኩለት። ‹‹የትላንቱ እራት ላይ ግን የምታስጠላህ አትመስልም ነበር….ያላየኋችሁ መስሎህ ነው? በደንብ አይቻችኋለሁ……..ሙሉ ምሽቱን ከእሷ ጋር ተጣብቀህ ያመሸኸው ስለምታስጠላህ ነው….?››
‹‹ህህ! ለምን ከእሷ ጋር ሳወራ እንዳመሸሁ ታውቂያለሽ?›› አለ ብስጭት ብሎ።
‹‹እኔ ምን አውቄ…ምናልባት ቆንጆ ስለሆነች?….ብዙ ሰው ነው ኤደን እኮ ሼፑዋ….ሰውነቷ…መልኳ እያለ የሚያወራው….እኔ በበኩሌ ቁንጅናዋ ምኑም አይታየኝ ግን ምናልባት አንተም ቆንጆ ናት ብለህ ታስብ ይሆናል…››
‹‹ቆንጆ ትሁን ፉንጋ አላውቅም…ደግሜ ባያት እንኳን ማውቃት አይመስለኝም…ከእሷ ጋር ሳወራ ያመሸሁት አንቺን ምንም ያህል ብለማመጥሽ ስለዘጋሽኝ ነው…..››
‹‹ማ? እኔ? መቼ ነው የዘጋሁህ?››
‹‹መቼ ነው ያናገርሽኝ? እሷን ሰላም ብዬ መጥቼ ካንቺ ጋር ልቀመጥ ስል ትላንት እንደተዋወቅሽው ሰው ‹‹ሃይ…እንዴት ነህ›› ብለሽኝ አልጠፋሽም?››
‹‹ታዲያ እንድለምንህ ፈልገሃል…?እኔ ቀኑን ሙሉ ላንተ ስዋብ… ስቆነጃጅ ውዬ ሰፍ ብዬ ስጠብቅህ ገና ከበር እንደገባህ እሷ ጋር ሄደህ ስትለጠፍ…አፍ ለአፍ ገጥማችሁ ስታወሩ አየሁ…ምን ማደርግ ነበረብኝ….ደስ የሚል ጊዜ እያሳለፍክ ነበር…መጥቼ መበጥበጥ ነበረብኝ…እ?››
‹‹ወይ አምላኬ! አንቺን ከማግኘቴ በፊት መጥታ ስታናግረኝ ገፍትሬያት ማለፍ ነበረብኝ?››
‹‹ባትገፈትራት እንኳን ልሂድ ለማለት ስትሞክር አላየንህም…››
‹‹ካንቺ ጋር ለማውራት ስሞክርስ አላየሽኝም ነበር? ዘግተሽኝ ስትሄጂሽ አላየሽም….? አንቺ ጥለሽኝ ስትሄጂ ተመልሳ መጥታ በወሬ ጠመደችኝ….በጣም ነበር የደበረኝ….በጣም የምታታክት ሴት ናት..አሰልቺ…..ባዶ ቆርቆሮ…ደሞ ወሬዋ አያልቅ…ወሬኛ ናት…ተረረረረረረረ›››
ሳላስበው ፈገግ አልኩ። ረጋ አልኩና፣
‹‹እሱስ አዎ…እኔም በወሬኛነቷ ነው የማውቃት….ግን ያው ሰው ሁሉ ቆንጆ ናት ሲል ነው የምሰማው…ሰውነቷ ምናምን ይላሉ›…››አልኩት።
‹‹ ናፍቆትዬ…አንቺ ባለሽበት ክፍል እንዴት ነው እሷ ቆንጆ የምትባለው…?አረ ክፍሉን ተይው…አንቺ ባለሽበት አለም እንዴት ነው ኤደን ቆንጆ የምትሆነው….?›› ድምጹ ለሰለሰ። ቁጣና ኩርፊያዬ ባንድ ጊዜ ተነነ።
እንዳነሳሱ ሁሉ ፍጥን ብሎ አጠገቤ ተቀመጠ። ተጠጋኝ። በጣም ተጠጋኝ። ከዚያ…ቀስ አለና በሃፍረት የዞረ አንገቴን በቀኝ እጁ ቀስ ብሎ አዙሮ አገጬን እንደ ብርጭቆ ያዘና….‹‹አፍንጫዋን አይተሸዋል? የሽሬክን እኮ ነው የሚመስለው….›› አለኝ።

ከት ብዬ ሳቅኩ።

‹‹ልክ ነህ…በጣም የሚስጠላ አፍንጫ ነው ያላት….ሴት ፊት ላይ እንደዚያ አይነት አፍንጫ ይዘገንናል››
ሳቀና ከንፈሬን በከንፈሩ በስሱ ሳም አደረገኝ።
‹‹አፍንጫ ላሳይሽ? አፍንጫ ማለት እንደዚህ ነው ….›› አለና አፍንጫዬ ላይ ሳም አደረገኝ፡
ልቤ እየቀለጠ፣ ሰውነቴ እየጋመ ‹‹ውሸታም…..›› አልኩት የውሸቴን።
‹‹አንቺ እኮ….አይንሽ ያምራል›› አለ አይኔን እየሳመ።
ልቤ ዳንኪራ እየረገጠ፣ አጥንቴ በስሜት እየቀለጠ ‹‹ውሸታም….›› አልኩት ውሸቴን።
‹‹አንቺ እኮ…እጅሽ ያምራል….አሁን እስቲ የማን እጅ ከዚህ እጅ በላይያምራል?›› አለ እጆቼን እያፈራረቀ እየሳመ።
ቀና አልኩና ‹‹የኤደን ታምሩ?› አልኩት።
ክው አለ።
‹‹..ጅል…! ቀልዴን ነው…›› አልኩና ከንፈሩን ሳምኩት።

‹‹ኤደን ታምሩ…ኤደን ታምሩ ብሎ ሰው….በዚች ሽሬንክን በምትመስል አስቀያሚ ወሬኛ ሴት ተቀንቶ…. ተኳርፎ…ስራ ሳይሰራ ተውሎ…..ናፍቆቴ….እብድ…እብድ እኮ ነሽ….››

ሳቅኩ።
‹‹ፊትሽን በመስታወት አታይም? አንቺ እኮ…ቁርጭምጭሚትሽ እንኳን ያምራል›››

ሳቅኩ።

ከዚያማ…ከዚያማ….
እሱ….. ‹…..አንቺ እኮ….ጆሮሽ እንኳን ያምራል…በምን ተአምር አንቺን የመሰለ ሴት በዛች ጓጉንቸር ይቀናል? ›› ብሎ የሞቀ ትንፋሹን በጆሮዬ ቀዳዳ ይለቅቃል
አንገቴን ከሰሜን እስከ ደቡብ….ከምስራቅ እስከ ምእራብ በከንፈርና በምላሱ ያካልላል….
‹‹ሴት ሁሉ ባንቺ ይቀናል እንጂ በምን ታምር አንቺን የመሰለ ሴት በማትረባ ሴት ይቀናል…›› ይላል….

እኔ ደግሞ….ሁለንተናዬ ክፍትፍት ብሎ….ይሄንን የመሰለ ነገር እላለሁ
‹‹አልቀናሁም….አልቀናሁም….ይልቅ ይሄ ሃብል አዲስ ነው…ቆይ ላውልቀው….እንዳትበጥሰው………አንተ….አንዴ…..ቆይ…. ››

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...