ስሚ መስሚያ ካለሽ። ከሰማሽ ደሞ ተስማሚ፤
ወዲያ ሂጂልኝ እስቲ።
ማነሽ እውነት ነኝ የምትይ፣ እስቲ ስሚን
የስንቱን አለመስማት እንችላለን?
መንግስት አይሰማን፣ ፈጣሪ አይሰማን፣ አንቺ አትሰሚን… ኸረ እስቲ አንቺ እንኳን?!!
ማን ነበረ ስምሽ? “እውነት ” ነው አይደል? እውነቱን ልንገርሽ፣ በደረስኩበት ባትደርሺ ደስ ይለኛል።
የፌደራል ዱላ ስታይ ቀልብሽ የሚገፈፍ አንቺ፣ ዶክመንተሪ ስታይ ስጋት የሚሰቅዝ አንቺ… ምናለ ሰቅዘሽ ባትይዢን። ለምንድነው በየሰዓቱ እየመጣሽ ሰላሜን የምትተገትጊው?
አይቴ ውእቱ ሀገርኪ?
እውነት ሀገርሽ የት ነው?
ለምን ወደሀገርሽ አትሄጂም? የትራንስፖርት ጎደለሽ? ስንት ልሙላልሽ በናትሽ?
ሂጂ እስቲ፣ መንገዱን ጨርቅ ያድርግልሽ።
ከድራፍት ብርጭቆዬ ስር መጥተሽ ቁጭ ትያለሽ። ኸረ በሰላም እንኳን ልጠጣበት። የድራፍት በረከቱ በላይ ቢላዩ ሲጋቱት አንቺን ማጠቡ!!
ችግርሽ ጠዋት አብረሽኝ መንቃትሽ!
ለምንድነው ያላገባኋት ሚስቴ የምትሆኚው? ያለፈቃዱ ያገባሽውን፣ በፍቃዱ መፍታት ይከብዳል?
በአንድ የሀገሪቱ ከተማ በወፌፌ ፖሊሶች ሰው በጥይት እየተጣለ አንተ I Am feeling happy ብለህ የፌስቡክ ስታተስ ትለጥፋለህ ትይኛለሽ።
አድርባይ በሞላበት ቤት አንቺን መያዝ ዋናው ዱላ፣ ትርፉ ጥይት መሆኑን አትጠሽው ነው። ተይ የማልፈልገውን አታስወሪኝ እስቲ።
ከፋኝ፣ አዘንኩ፣ ተበደልኩ ብዬ ብፅፍ፣
“ምን አባህ ሆነህ ከፋህ? የምን ጥጋብ ነው ” ቢሉኝ ምን እመልሳለሁ (እራሳቸው በቀን ሶስቴ አበላናቸው እያሉ፣ መልሰው የምን ጥጋብ ነው ይሉናል አየሽ— የተቃርኖ ሀገር፤ ተናገሪ ተብለሽ ዲዳ የምትደረጊበት)
ማነኝ ነው የምትይ ለማንኛውስ?
ከእርኩስ መንፈስ ነሽ ከቅዱስ? የሰው ነብስ እያስገበሩ ቅዱስ አለ?
አቦ ሂጂ በናትሽ።
ሰው ሁሉ እየሄደ ነው። ለይቶለት የሄደ አለ፣ እዚህ ሆኖም የሄደ አለ፤ እስቲ አንቺም ሰዉን ምሰይ።
ወይ ጥርግ ብለሽ ሂጂ፣ ወይ ነፐረሽ መኖርሽ አይታወቅ። ማበይ በሰረፀበት ሀገር ሂያጅ ቢበዛ ትገረሚያለሽ? ይልቅ ያንቺ አለመሄድ ነው የሚገርመው። ሕዝቡ እኮ እንደጠላሽ ውሸትን በመውደድ ነገረሽ፣
እህሳ ምን ቀረሽ?
የሀገሪቱ ዜጎች ገቢ ከሚያገኙባቸው መንገዶች ውስጥ ጥቂቶቹን ልግለፅልሽ
_ አርሶ አደርነት
— አርብቶ አደርነት
— ሰርቶ አደርነት
— ዋሽቶ አደርነት…
ሰው እነዚህን ሰርቶ ያድራል። አንቺን የተናገረ ግን ሲያድር አላየንም። ኸረ ውሎም አያውቅ። ተይኝ እስቲ እቴ፣ ክፉ አታናግሪኝ፤ የምፈራው መንግስት አለኝ።
“እውነትን ተናግሮ የመሸበት ማደር” የሚባል ተረት ከመሸበት ቆየ። ማደርን ተይው፤ ቅንጦት ነው። መጀመሪያ ማን ያስመሸዋል?
ኡፍፍ ወዲያ ሂጂ እስቲ አቦ፣
ሌላ ሀገር ፈልጊ፤ ካልቻልሽ ሌላ ሰው።
ትሰሚያለሽ? ስሚ ከመስማት ብዙ ይገኛል። እኛ ብዙ ያጣነው የሚሰማን አጥተን ነው። በሽ ነው የሚያወራ!
ከአጠገቤ ለመጥፋት አንድ ሁለት እስክል አትጠብቂ። ሂጂ! ራቂኝ።
አንቺን ያቀፈ፣ ምን አተረፈ?
እውነት ነኝ ነው ያልሽው? እስቲ በመጨረሻ ሁለት ጥያቄ ልጠይቅሽ…
1) እውነት ግን አንቺ እራስሽ እውነት ነሽ?
2) እውነት ግን አለሽ? ነው የውሸት ተቃራኒ ሁላ አንቺ እየመሰልሽኝ ነው የምቃዠው? አለሽ ሰለእውነት?
ካለሽ እኚን ሁለቱን ጥያቄዎች መልሰሽ እስከ አድማስ ሽሺኝ እባክሽ!
እየሸሸሁ መኖር አልፈልግም። ሸሽተው የማያመልጡት መንግስት አለብኝ። ተከልለው የማይሰወሩባቸው አድር ባይ ዐይኖች ተተክለውብኛል።
ትሰሚያለሽ?
2 Comments
አጌ ስወድህ
ተው በእናትህ
ሆድ አታብስብን
የሰቆቃ እንጎቻም መጉረሳችን አታስታውስብን
እንቅልፍም እናጣብሃለን፤