አሜሪካ የነጮች ምድር ስትሆን የጥቁሮች ደግሞ ምድረ-ፋይድ ናት፤
ለምሳሌ አንድ የፈላበት ጎረምሳ ፈረንጅ መቶ ጎራሽ ጠመንጃ ታጥቆ ወደ አንድ ምኩራብ ወይም ወደ አንድ የኤሽያ ማሳጅ ቤት ገብቶ ይተኩሳል፤ በፊቱ ያገኘውን ሁሉ ይገነዳድሳል ፤ ፖሊሶች ይደርሱና ከብበው፤ በላዩ ላይ ያሳ መረብ ጥለው ይይዙታል፤ ከዚያ” ቃታ የሳብክበት ጣትህ ወለም ሳይለው አይቀርም ማሳጅ እናደርግልህ “ “የተኩስህም ድምጽ ጆሮህን ሳይጎዳው አይቀምና እናሳክምህ” ብለው በአምቡላንስ ይወሰዱታል፤ በምላሱ ድንጋይ ቀቅሎ ማብሰል የሚችል ጠበቃ ይቀጠርለታል፤ አንድ ነገር ነከቶት ነው እንጅ በጤናውማ እንዲህ ያለ እልቂት አይፈጽምም” ብለው የሆነ የአአምሮ ህመም ይፈበርኩለታል፤ ከዚያ ወይ በሀኪም ቤት አለበለዝያም በማረሚያ ቤት ውስጥ ኦርጋኒክ ምግብ እየበላ በኦርጋኑም እየተጫወተ ቀሪው እድሜውን እንዲያሳልፍ ይፈቅዱለታል።
ጥቁር ከሆንክ ሌላ ነው፤ ፖሊስ ባለበት አካባቢ ገላህን አሳክኮህ እጅህን ወደ ሽንጥህ ከሰደድህ “ ሊተኩስብን ነው” ብለው ጥይት ያራግፉብሀል ፤ ሳታስበው ማኖ ነክተህ “በቁጥጥር ስር ውለሀል” ካሉህ ፤ “ ጀንትል ሜን! ካቴናው ከኔ ይሁን ወይስ ከናንተ “ እያልህ መተባበር ነው ያለብህ፤ “ያዙኝ ለቀቁኝ ካልህ” ይይዙሃል፤ ግን በህይወት አይለቁህም! ትንሽ ከተፈራገጥህ አንተን አያርገኝ፤ አፈር ያስግጡሀል፤ አሜሪካ ከተሞች ውስጥ አፈር በቀላሉ አይገኝም፤ ግን ካፍጋኒስታም ቢሆን አስመጥተው ያስግጡሀል።
እስካሁን የጻፍኩት ግነት እንደበዛበት ለኔም ታውቆኛል ፤ ያም ሆኖ በኩሸቱ ውስጥ እውነት እንዳለበት አይጠፋሺም፤
አሜሪካ ከሌሎች አገሮች ጋራ ያላት ግኑኝነት በፍትህ ላይ ሳይሆን ባሰላለፍ ላይ የተመሰረተ አንደሆነ ከዚህ ጽሁፍ አንባቢ የተሰወረ አይደለም!
ከአመታት በፊት፥ ሰአሊው ወዳጄ ግዛቸው ከበደ ቤት ያየሁት ነገር ትዝ አለኝ፤ ጋሽ ተምትሜ የተባሉ ጥሮተኛ ሽማግሌ አልፎ አልፎ እየመጡ ወዳጄን ይጎበኙታል፤ መጠነ ሰፊ ቁልምጫና ውዳሴ አጉርፈውለት ሲያበቁ አንድ አምሳ ብር ይፈልጡታል፤
አንድ ቀን እንደልማዳቸው መጥተው ዳር ዳር ሲሉ ግዛችው” ልጅ የለዎትም?” ሲል ጠየቃቸው፤
“አለቺኝ!” አሉ ጋሸ ተምትም” ግን እምትበላ ናት”
ከራስዋ አልፋ ለሌላ ለመትረፍ አልደረሰችም ፤ ማለታቸው ነው።
አገራችንም እንደ ጋሸ ተምትሜ ልጅ “ እምትበላ ናት፤ የበላችበትን ሂሳብ የሚዘጉትም ሀብታም አገሮች ናቸው ፤ ያለ ሀብታም አገሮች ረድኤት በቀንጃ በሬ ታርሶ ሞሰቡዋ ደርበብ እንደማይል እናወቃለን፤ ኢትዮጵያ ግብጥና ኢራቅን ተከትላ ፥በስድሰተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ የአሜሪካ ተረጣቢ አገር ናት፤ ይሄንን ረድኤት ቢወስዱብን ሌላ ቀለብ ሰፋሪ አሰናድተናል? ወይስ የልብ ኩራት ብቻ ያሳድረናል?
“አሜሪካ በኛ ጣልቃ አትግባ” እሚለው ንግግር ከመፈክርነት ያለፈ ትርጉም አሚኖረው ጣልቃገብነትን የሚመክት ጉልበት፥ እውቀት እና ሀብት ሲኖረን ነው፤ ካልተሸዋወድን በቀር እኒህን ጸጋዎች በቅርብ ርቀት እንኳ እንደማናያቸው እናውቃለን፤ ሽቅብ የሚያዳልጣቸውን ሰዎች ፉከራ ወደጎን ትቶ የቤታችንን ጣጣ መፍታት አና የዲፐሎማሲ ብልጠት ላይ መትጋት አይሻልም? አንድ የበራለት ወያላ አንዳለው፡ “ ከማያዋጣ ጉልበት ፤በህግ አምላክ ማለት”