አሜሪካን አገር፥ አበሻና ላቲኖ የሚበዛበት ሰፈር ውስጥ ቤት ስከራይ ለደላላው እማቀርበው የመጀመርያው ጥያቄ “ ሽንት ቤቱ የብቻ ነው የጋራ ?” ሚል ነው።
ወድጄ አይደለም፤ ደባል አበሻ ነህ እንበል! ዶሮ ወጥ ትወዳለህ! አሜሪካን አገር ያለው “ችክን” ደግሞ ችክ ያለ ነው ፤ አጥንት ያለው አይስክሬም እንደመብላት ልትቆጥረው ትችላለህ ። እናትህ የላክህላትን ዶላር መንዝራ ፤ ስድስት ዶሮ ረሽና ጉርድ በርሚል በሚያክል አገልግል አጭቃ ትልክልሀለች ፤ ዶሮ ወጡ ፤ ከናትህ ወደ መልክተኛው፥ ከፍሪጅ ወደ ሻንጣ ሲንከራተት ከርሞ ይደርሰሀል፤ አንተም ተቀብለህ በቅርስነት በማስመዝገብ ፋንታ ወደ ሆድህ ታዛውረዋለህ ! ከዚያ በማግስቱ የዳጉሳ ቂጣ እንደበላ ምስኪን ዘለግ ያለ ምጥ ይጠናብሀል፤( በተወለድሁበት አካባቢ ጤፍ መሸመት የማይችል ሰው ዳጉሳ ይበላል፤ ዳጉሳ ለማምረት የሚያስቸግር በልቶ ተረፈ ምርቱን ለማስወገድም የሚከብድ እህል ነው፤ እና ሲተረት “ የዳጉሳ ጣሩ እስከ …ሩ” ይባል ነበር ) እና ምጥ ሲፋፋምብህ ሳምሶናይት እሚያህል ላፕቶፐህን ይዘህ፥ ሽንት ቤት ትገባና ከላይም ከታችም ዳውንሎድ እያደረግህ እኩለቀን ትዘፈዘፋለህ። ታድያ ይሄን እያየሁ” ሽንት ቤት የግል ነው ፤አገር የጋራ ነው” ብል ይፈረድብኛል?!
በአለም አንደኛ የሚባል አመት በአል ካለ” እንቁጣጣሽ “ መሆን አለበት። የደስታው ምስጢር ተነፋፍቆ መገናኘት መቻል ይመስለኛል። ተራርቆ የኖረ ወዳጅ በሰበቡ ይገናኛል፤ ተሰውሮ የቆየብን ልምላሜ ፤ ቄጤማ ፤ አደይ አበባ እና እንደ ሉባንጃ የሚጥም አየር ይጎበኘናል ። በጦም ወይ በእጦት ምክንያት ተለያይቶን የኖረውን የክት ምግብና መጠጥ እናገኘዋለን ። ያስቴር አወቀን “ አበባየ ሆይ “ ጨምሮ ሌሎች ምርጥ ምርጥ የህይወት ጸጋዎች ተካፋይ የምንሆነው ባውዳመት ነው።
ፈረንጅ አመት በአል አያምርበትም ። ትንሽ ለየት ያለው “ ሀለዊን” የተባለው አመት በአል ይመስለኛል ። የሰማእታት መታሰቢያ ቀን ነው ይሉታል፤ ዜጎች የጭራቅ ማስክ አድርገው የጎረቤቶቻቸውን ቀልብ ለመግፈፍ ተፍተፍ የሚሉበት በአል ነው። በተለይ ከሁለተኛው አለም ጦርነት ወዲህ ጦርነት የጤረረባቸው የበለጠጉ አገሮች ከተንዛዛ ሰላም የመነጨ ድብርት ለማባረር ይጠቀሙበታል፤ በአሉን ዘግናኝ ፊልም በማየት ወይም አሰቃቂ ታሪኮችን በመለዋወጥ ያሳልፉታል።
“ ሀለዊን በአገራችሁ ይከበራል?” አለኝ አንዱ ባለፈው ።
“ በኛ አገር ካመት እስከ አመት “ሀለዊን” ስለሆነ የተለየ ቀን አያስፈልገንም” ብየ መለስኩ።
እንደ ታከለ ኡማ ፤ በአደይ የዘነጠ አወዳመት ተመኘሁላችሁ።
2 Comments
ስወድህ ክበርልኝ::
<a href=[Link deleted]