Tidarfelagi.com

ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት… እኔ የቀጠልኩት (ክፍል ዘጠኝ)

«እኔ ከዚህ በላይ ማስመሰል አልችልም! ከአቅሜ በላይ ነው የምወድህ!» እያልኩት እናቱ ናፍቃው እንዳገኘ ህፃን መንሰቅሰቅ ጀመርኩ።
የሚያስለቅሰኝ ምኑ እንደሆነ ለራሴ ምክንያት መስጠት አልቻልኩም። ፍቅሩ፣ ፍርሃቴ፣ ሳልናገር መታፈኔ ……… አላውቅም። እንደህፃን ድምፅ አውጥቼ እዬዬ ማለት ጀመርኩ። እሱ መጀመሪያ እየከወነ ያለውን ልፋት በቀስታ አቆመ።

«አውቃለሁኮ! » አለ ለእኔ ይሁን ለራሱ የተናገረው በማያስታውቅ አወራር። <አውቃለሁኮ!> ያለበት አባባል <አውቄልሻለሁኝኮ! ፍቅርሽ ገብቶኛል፣ ተረድቼሻለሁ።> ዓይነት አይደለም። የሆነ የቁጭት ዓይነት፣ የብስጭት ዓይነት ነበር። …….. መንሰቅሰቄ ሲብስበት በጎኑ ተኝቶ ደረቱ ላይ አጣብቆ አቅፎኝ ዝም አለ። የሳጌ ድምፅ ከፍ ሲልበት እቅፉን ጠበቅ ያደርገዋል። እንደማባበል ዓይነት። ደቂቃዎች ካለፉ በኃላ ………….. ለቅሶዬን ያለከልካይ ካስነካሁት በኃላ………. እንባዬ ደረቱን ካራሰው በኋላ ………. ከዚህ ሁሉ ደቂቃ በኋላ ጭንቅላቴን ከደረቱ ወደ ክንዱ አሸጋግሮ ቀና አለ። ባላቀፈኝ እጁ ፀጉሬን ከግንባሬ ላይ አሸሸው፣ በእንባ የተጨማለቀ ፊቴን ጠራረገ ፣ የስስት ይሁን የፍቅር ይሁን መግለፅ በማልችለው ስሜት ዓይኔን ፣ ጉንጬን ፣ አፍንጫዬን፣ አገጬን ፣ ግንባሬን ፣ አንገቴን ……… ፊቴ ላይ ስማቸውን ሁላ የማላውቃቸውን ቦታዎቼን በቀስታ እና በተመስጦ ሳማቸው። ከንፈሬን ስሞኝ እንደማያውቀው ፤ ተሰምቶኝ እንደማያውቀው እና የእርሱ እንዳልሆነ አሳሳም እየሳመኝ አቋርጦ
«ልትዪኝ ፈልገሽ ያላልሺኝን፣ ልትነግሪኝ ፈልገሽ ያልነገርሽኝን ንገሪኝ፣ ማድረግ ፈልገሽ የቆጠብሽውን አድርጊኝ! » ይሄን ያወራበትም ድምፀት የእርሱ አልነበረም። የሆነ ፊልሞች ላይ ያለ ያፈቀረ ሰውዬ ድምፀት ነበር።

«ያ ማለት በፈለግኩት ቁልምጭ መጥራትንም ጭምር ያካትታል? (ፈገግ እንደማለት ብሎ በጭንቅላቱ ንቅናቄ አዎ አለኝ) እሺ እያደረግንም እንዴት እንደማፈቅርህ ማውራትንም ይጨምራል?»
«የፈለግሽውን! ያለምንም ገደብ!»
ለምን ብዬ አልጠየቅኩም። ሊሰማው የማይፈልገውን ሁሉ በነፃነት እንድለፈልፍ ለምን ነፃነቱን እንደሰጠኝ የምጠይቅበት ማሰቢያ እንዳይኖረኝ ፍቅሩ አቃቂሎኛል። ነገርኩት። ምንም ነገር በዝህች ምድር ላይ ቀርቶብኝ እሱን እንደምመርጥ ነገርኩት፣ ከእርሱ ጋር እስከሁሌውም የመኖር ልዋጭ ከሰጠኝ እናት መሆንን በሱ ፍቅር ለመለወጥ እንደማላመነታ ነገርኩት፣ አብሬው እየኖርኩ ሁላ አቅፌው እየተኛው ሁላ እቅፉ ውስጥ ሆኜ ሁላ እንደምሳሳ ነገርኩት፣ እኔ እንደማፈቅርህ አፍቅረኝ ብዬ አልልህም ምላሹን አልጠብቅም ግን የእኔ ብቻ ሁንልኝ አልኩት፣ አንተ አታፍቅረኝ እኔ ግን በፍቅርህ ስለተሸነፍኩ እንድፈራህ አታድርገኝ አልኩት………. አልኩት …….. ብዙ ነገር አልኩት። በማውቀው የፍቅር ቁልምጭ ሁላ ጠራሁት። እየደጋገመ ያን የእርሱ ያልሆነውን አሳሳም ከመሳም ውጪ ምንም ነገር አላለኝም። ለብዙ ደቂቃ ያለከልካይ ባለኝ አቅምና ችሎታ ሁላ ፍቅሬን ደስኩሬ ሳበቃ የእርሱ ያልሆነ ዓይነት ፍቅር ሰራን …… ምንም ወሬ የሌለው፣ ግን ያለወሬ ወሬ ያለው፣ በጣም ለስላሳ አይነት ነገር ……. በወሬው ምትክ ብዙ መሳም ያለው….. በዓይኖቼ ውስጥ አድርጎ ልቤጋ የሚያደርሰው ዓይነት አስተያየት በየመሃሉ ያየኛል። በሰዓቱ ያልገባኝ ሀዘን እና ስስት ዓይኑ ውስጥ ነበረ። ስንጨርስ እንደቅድሙ ደረቱ ላይ አጥብቆ አቀፈኝ።
ደስ ሊለኝ ነበር የሚገባው አይደል? በምትኩ ነፍሴ ድረስ የዘለቀ የሚያርድ ፍርሃት ነበር የተሰማኝ። አቅፎኝ አስባለሁ። ያስባል። ከብዙ ሀሳብ በኋላ እንቅልፍ ወሰደኝ። ስነቃ ስንተኛ እንደነበረው። የራስጌው መብራት እንደበራ ፣ የምበር ይመስል አጥብቆ እንዳቀፈኝ ፣ዓይኖቹ እንዳፈጠጡ ነው።
«እንቅልፍ አልወሰደህም?»
«አዎ! አልተኛሁም! አሁንማ ነጋ!»
«ምን እያሰብክ ነው?»
«አንቺን!»
«እቅፍህ ውስጥ ሆኜ ስለእኔ ምን ያሳስብሃል?»
አልመለሰልኝም። ተነስቶ ገላውን ተጣጥቦ ሳይስመኝ ቀድሞኝ ወጥቶ ወደስራ ሄደ። ቀኑን ሙሉ መብላትም ማሰብም ልጆቹን ማስተማርም በትክክል ማሰብም ሳይሆንልኝ አሞኛል ብዬ አስፈቅጄ ወደቤት ተመለስኩ። ከስራ እስኪመለስ ጓጓሁም ፈራሁም። የጠዋቱን ሳይሆን የማታውን አዲስ ቢመልስልኝ ፀለይኩ። እየደጋገምኩ <ምናለ ባልነገርኩት?> እላለሁ። ደግሞ መልሼ <አልችልም ነበር> እላለሁ። የሆነኛው እኔ አዲስን ላላገኘው እንደሸኘሁት ነግሮኛል። የሆነኛው እኔ ያን ማመን ስላልፈለገ ጥሩ ጥሩውን ሰበብ ይጎነጉናል። ያልበላሁት ምግብ ሊያስመልሰኝ ያቅለሸልሸኛል። እጄን ያልበኛል። ስቀመጥ ስነሳ ውዬ መጣ። ሲገባ እንደሌላው ቀን አልሳመኝም። ያ የምፈራው አዲስ ሆነ። ጠበቅኩት ከአፉ የሆነ ነገር እንዲወጣ። ምንም ቃል ሳይተነፍስ እራት ቀርቦ በላን።
«ውሎህ ጥሩ ነበር።»
«የተለመደው ዓይነት»
ደሞ የማወራው እፈልግ እፈልግና
«ዛሬኮ አሞኝ ጠዋት ነው አስፈቅጄ የመጣሁት።»
አሞኛል ስለው አጠገቤ ዘሎ ደርሶ የሚነካካኝ አዲስ ምንም ስሜት በሌለው ቀና ብሎ እንኳን ሳያየኝ
«ምነው? ጠዋት ደህና አልነበርሽ?»
እራቱን ሲጨርስ ወደ ላይብረሪው ሄደ። መኝታዬ ላይ ተኝቼ ከአሁን አሁን መጣ ብዬ ስጠብቀው እና በሃሳብ ስባዝን እንቅልፍ ይዞኝ ሄደ። ለሊት 10 ሰዓት ስባንን አጠገቤ የለም። ተነስቼ ላይብረሪው ስሄድ እዛም የለም። ክፍሎቹን እየከፋፈትኩ የሆነኛው ሌላ ክፍል ተኝቶ አገኘሁት። ማልቀስ አማረኝ። እሪሪሪሪ ብዬ ማልቀስ ……. የመብራት መብሪያ እና ማጥፊያ ቀጭ ሲል የሚነቃ ንቁ ሰውዬ በሩን ከፍቼ ስገባ እንዳልነቃ ሰው ረጭ ብሎ የተኛ መሰለ። በሩን መልሼ ዘግቼለት ወጣሁ። ይሄ ቂል ልቤ ደግሞ <አምሽቶ እንዳይረብሽሽ ነው ሌላ ክፍል የተኛው> ይለኛል። ሄጄ አልጋዬ ላይ ተገላበጥኩ እና ነጋልኝ። የተኛበት ሄጄ
«አውራኝ ምንድነው ያደረግኩህ? ማፍቀሬ ሃጥያት ነው? ቆይ እሺ ደግሞስ ላፍቅርህ ብዬ መሰለህ ያፈቀርኩህ? ለየትኛው በደሌ ነው የምትቀጣኝ? ታውቅ ነበርኮ አይደል እንዳፈቀርኩህ? አፌ ላወራቸው ቃላት ነው የምትቀጣኝ?»
ጥያቄም አልነበረም። ልመና ነበር። መጨረሻ ላይ ከአፉ የወጣው ቃል።
«እንፋታ!» የሚል ነበር። ራሴን የምስት መሰለኝ። የሰማሁትም ቃል እኔ ጆሮጋ ሲደርስ አበላሽቼ ሰምቼው መሰለኝ
«ምን? እንፋታ አይደለም አይደል ያልከው?»
«ነው! እንፋታ ነው ያልኩሽ!» ቃላቶቹን ሁሉ ሲላቸው በጭካኔ ነበር።
«እህህ ቆይ ምንድነው ያደረግኩህ? ንገረኝ ምንድነው ምክንያትህ?»
«ምክንያቴን ልነግርሽ አልችልም! »
« በእኔ መፈቀር የዚን ያህል የሚያስጠላ ነገር ነው? ፍቺን የሚያስመርጥ ነው? በመነጋገር ታምን የለ? የማንነጋገረው ነገርኮ ኖሮ አያውቅም! እሺ ፍታኝ ግን ቢያንስ ምክንያቱን እንኳን ማወቅ የለብኝም?»
ተነስቶ ከአልጋው እየወረደ ያሳዘንኩት በሚመስል ሁኔታ በሚያባብል ድምፅ
«ላንቺ ምክንያቴን ለማስረዳት መቼም አልነግርሽም ያልኩሽን ድሮዬን ማስረዳት አለብኝ። እሱን ማድረግ ደግሞ አልፈልግም። ምክንያቱ ለእርሱ በቂ ቢሆን ነው ብለሽ አስቢው። ደግሞ ውላችን አንደኛው አካል መፋታት ከፈለገ……… » ሳይጨርስ ጮህኩኝ እንባ ያነቀው ጩኸት ፣ እልህ ያነቀው ንዴት
«ውል ህግ አትበልብኝ። ውልና ህግ ብቻውን የሰውን ህይወት ቢመራ ዛሬ ያንተ መጫወቻ አልሆንም ነበር።» ጥዬው ወጣሁ።
ከዛ ቀን በኋላ እንደፈለገው እንዲሆን ተውኩት። ጭራሽ ሊያየኝ አለመፈለጉን አከበርኩለት። እኔ ግን በየቀኑ አለቅኩ። በ50 ኪሎሜትር ርቀት ዓይነት እየገፋኝ በ100 ኪሎሜትር ዓይነት ርቀት ወደእርሱ እወነጨፋለሁ። ሁሉ ነገር አቃተኝ። በሳምንታት ውስጥ እያየሁት ሰውነቴ ቀነሰ። መልበስ፣ መብላት፣ መስራት፣ መተኛት …….. ሁሉ ነገር ታከተኝ። ከሳምንታት በኋላ ስለእርሱ ላወራው የምችለው ሰው ትዝ አለኝ። ፀዲ! የመጀመሪያ ሚስቱ! ያኔ ብር ልናቀብላት እቤቷ ሄደን አልነበር?
«እመኚኝ አንቺ ከምታውቂው የተለየ ስለእርሱ የማውቀው ነገር የለም። እኔ የመጀመሪያው ስለሆንኩ የማውቀው ነው የሚመስላችሁ?» ስትለኝ በብዙ ቁጥር የጠራችኝ ከማን ጋር ደርባ እንደሆነ ሳስብ ሁለተኛ ሚስቱ ልክ እንደእኔ ግራ ሲገባት መጥታ አዋርታት እንደነበር ነገረችኝ።
«እኔ ሳገባውም በፍቅሩ ጧ ብዬ ነው ያገባሁት። እንደምታውቂው ነገረ ስራውን ላትወጂው አትችዪም። አስብ የነበረው ፍቅሩን መግለፅ ስለማይችል እንጂ ያፈቅረኛል ብዬ ነበር። ስህተቴ የነበረው ታውቂያለሽ < ብልህ ሴት ወንድን ልጅ ትቀይራለች> በሚል እሳቤ ነው ያደግኩት እና ከትዳር በኋላ ይቀየራል የሚለው እምነቴ ነበር። ተጋብተን መኖር ከጀመርን በኋላ ግን የሚያደርግልኝን የሚያደርገው በባህሪው ጥሩ ሰው ስለሆነ እንጂ በፍቅር አለመሆኑን አወቅሁ። በዛ ላይ ለማያፈቅረኝ ሰው ስል እናት የመሆን ስጦታን መዝለል ልቀበለው አልቻልኩም። የሆነ ቀን እንደምለየው እርግጠኛ ስሆን ተነጋገርን እና ተፋታን!!»
ስለእርሱ ሳወራ ከሚገባው፣ እሱን አብሮ ኖሮ ከሚያውቀው ሰው ጋር ስለእርሱ ማውራት የሆነ ደስ የሚል ስሜት ስለሰጠኝ ከእኔጋር የተፈጠረውን ስነግራት።
«በቃ?» ብላ ጮኸች
«አዎ በቃ!»
«የሆነ ነገርማ አለ። እንደምታፈቅሪው ስለነገርሽው እንፋታ አይልም አዲስ! ሳንጋባ በፊት ጀምሮ እስከምንለያይ ድረስ እንደማፈቅረው በየቀኑ እነግረው ነበር። ከእርሱ ምንም ምላሽ አታገኚም እንጂ ያንቺን ስሜት አይከለክልሽም! Come on ሰውየውኮ አዲስ ነው። የሰው ልጅ ሀሳቡን ሳይበርዝ በነፃነት መግለፅ አለበት ብሎ የሚያምን ሰው ነው። ያመነውን ደግሞ እንደሚኖር ታውቂያለሽ።»
«በእናቴ እምልልሻለሁ ያልነገርኩሽ ነገር የለም። ከዚህ የተለየ ያደረግኩት ምንም ነገር አልነበረም።!»
«ሰብለን ከፈለግሽ ጠይቂያት (ሁለተኛ ሚስቱ ናት) እሷም እንዳንቺ ከገባች በኋላ ነው በፍቅር የበሰለችው። ምላሹን እንደማታገኝ ተስፋ ቆርጣ ፍቺ እስከፈለገች ቀን ድረስ እንደምትወደው ነግራዋለች። ምንም ሊገባኝ አልቻለም። ohhh my God ማሰብ እንኳን አልችልም! ምናልባት የራሱን ስሜት እንዳይሆን መሸሽ የፈለገው? » ብላኝ የሆነ ግኝት እንዳገኘ ሰው ጮኸች።

ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት ….. እኔ የቀጠልኩት (ክፍል አስር)

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...