Tidarfelagi.com

ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት… እኔ የቀጠልኩት (ክፍል ሰባት)

ሰርጉ የራሴ ሆኖ ፣ በሰው ሰራሽ ፋብሪካ የተመረተ ሮቦት ይመስል ዘመድ አልባ ባል ላገባ የተዘጋጀሁት እኔ ሆኜ ሳለሁ፣ ሰርጉ ላይ ሚዜ እንኳን የሚሆን ጓደኛ የሌለው ባል ለማግባት ራሴ አምኜ ………. ምን ይሉ ይሆን ብዬ የምጨነቀው ለቤተሰብ ፣ ሰርጉ እንከን እንዳይኖረው ቁጭ ብድግ የምለው ለታዳሚው ……ሙሽራዋ ግን እኔው …… ቀኑ መሆን የነበረበት የኔ

«ለምን ራስሽን አትሆኝም?» አለኝ አዲስ የሰርጉ ውጥረት ቀልቤን ሲነሳኝ አይቶ
«ይሄ ነገር ስለሚባል ነው አይደል የምትሉት? ራስህን መሆን እኮ …… የምትወደው ራስህ ሲኖርህ ነው! እኔን መሆን እንዴት እንደሚያስጠላ ብታውቅ <ራስሽን ሁኚ> አትለኝም! ራሴን አልወደውም አዲስ! የማልወደውን ራሴን እንድሆን አትንገረኝ! እኔን መሆን ይቀፋል! ሌላን ሰው መልበስ ይሻለኛል። ያ ሰው ማን እንደሆነ ሳታውቁ <ራስህን ሁን> እያላችሁ አትምከሩት! የማነቃቂያ ንግግራችሁ ማስዋቢያ ወይም ንግግር ማሳመሪያ ብቻ ነው። መጀመሪያ ራሱ የሚወደው ማንነት ይኖረው እንደሆነ ጠይቁት እስኪ!! ራሱን ሲሸሽኮ ነው ሌላ ሰው የሚሆነው! » እየጮህኩ እና ስሜታዊ ሆኜ እያወራሁ እንደሆነ የገባኝ አዲስ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከራከርበት ሀሳብ ሰጥቼው በመከራከር ፈንታ በጣም ረጋ ብሎ ሁለቱን እጆቼን ሲይዘኝ ነው

«ቤተሰብ ፣ ማህበረሰብ፣ እኔ ፣ ሀይማኖት ……… ብቻ ምንም በዙሪያሽ ባይኖር ፣ ማንም ካንቺ ምንም ባይጠብቅ ፣ ማንንም ማስደሰት ወይም የማንንም expectation ማሟላት ባይኖርብሽ ………. ምን አይነት ሰው ነው መሆን የምትፈልጊው? ምን ማድረግ ነው የምትፈልጊው የነበረው?»

«ደስተኛ ሴት መሆን ብቻ ነበር የምፈልገው!! ማንም ሳያዋክበኝ ፣ ማንም < ሴት መሆን ያለባት፣ ወጣት መሆን ያለበት፣ ቆንጆ መሆን ያለበት፣ የእቴቴ ልጅ በመሆንሽ መሆን ያለብሽ፣ የዳግም እህት በመሆንሽ መሆን ያለብሽ፣ ክርስቲያን መሆን ያለበት ……… > እያለ የኑሮ ዘይቤዬን ሳያሰምርልኝ ከህሊናዬ እና ከአምላኬ ጋር ሰላሜን እየጠበቅኩ ራሴን መፈለግ ብቻ ነው የምመኘውኮ! ራሴን ማግኘት!! ፍለጋዬን ገና ድሮ ስላጠፉብኝ ማን እንደሆንኩ እንኳን አላውቀውምኮ!!» አሁንም እየጮህኩ ነው የማወራው። እስከዛሬ ለራሴ ራሱ ለማስረዳት በውል የቸገረኝን መሻቴን ሳብራራ ራሴን አገኘሁት።

ለደቂቃ ያህል ዝም ካለኝ በኋላ
«ሰርጉን መሰረዝ ትፈልጊያለሽ? ማንንም የማታዪ የማትሰሚበት ቦታ ሄደሽ ከራስሽ ጋር ብቻ ጊዜ እያሳለፍሽ ራስሽን መፈለግ ትፈልጊያለሽ? ያን ላሳካልሽ እችላለሁ። ነገር ግን ሁሉንም ከኋላሽ የመተው አቅሙ አለሽ?»
«አቅሙ የለኝም! አልፈልግምም! አየህ ወፍ መብረር እችላለሁ ብላ የፈለገችበት ዝም ብላ አትበርም። ስደተኛ ወፎች የሚባሉትን ታውቃቸዋለህ? ተፈጥሯዊው የአየር እና ወቅት ለውጥ የኑሮ ዘይቤያቸውን እነርሱ ወደፈለጉበት ሳይሆን ምግብ ወደሚገኝበት፣ መኖሪያቸውን በረዶና ንፋስ ሳያፈርስባቸው ወደሚኖሩበት አቅጣጫ እንዲበሩ ያስገድዳቸዋል። አየህ ህብረተሰብ ቤተሰብ ሀይማኖት ባህል ምናምን የማይዛት ወፍ እንኳን ተፈጥሮ በሆነ መልኩ ያጥራታል። ወደድንም ጠላንም የምትታሰርበት ሸምቀቆ እንደግለሰቡ ከመጥበቁ እና ከመላላቱ ውጪ ሁላችንም በአንደኛው ገመድ ተጠፍንገናል። ምክንያቱም የዚህ ማህበረሰብ አካል ነና! የምንኖረው ከዚሁ ማህበረሰብ ጋር ነዋ! የምንኖረው ለዚሁ ማህበረሰብ ነዋ! እንደአለመታደል ሆኖ አንዳንዶቻችን የታሰርንበት ገመድ አንቆ ሊገድለን አንገታችን ሰልሎ እንኳን ለማምለጥ አቅሙ የለንም!» አይኔ ይሁን እንጃ ያዘነልኝ መሰለ? የሆነ ውሳኔ ለመወሰን ያመነታ መሰለ። ግንባሩ ላይ ስሜቶቹ ተቁነጠነጡ።

«እሺ በተወሰነ መልኩ ውጥረትሽን ከቀነሰልሽ ስራ ቦታ ያሉ ሰዎችን ሚዜ እንዲሆኑልኝ ጠይቃቸዋለሁ። የተወሰኑትንም ሰርጉን እንዲታደሙ የጥሪ ወረቀት እሰጣቸዋለሁ። ይሄ የሚያቀልልሽ ነገር አለ?»
«አዎ በጣም! በጣም እንጂ! በጣም ብዙ ነገር ያቀልልኛል። አመሰግናለሁ!» እንደህፃን ልጅ መጨፈር ቃጣኝ። ማድረግ የፈለግኩት ከንፈሩን መሳም ነበር ግን ጉንጩ ላይ አረፍኩ። ሰርጌ ሳምንታት እየቀሩት የማገባውን ሰውኮ በጭራሽ አላውቀውም! እሱ ላይ ስልጣንና መብቴ ምን ድረስ እንደሆነ እንኳን አላውቅም።

«የሰውን ልጅ ልወቀው ብለሽ እድሜሽን አትፍጂ ይልቅ ያንን ኢነርጂ ራስሽ ላይ አውዪው። እመኚኝ ራስሽን ለማወቅ የምታደርጊው ፍለጋ በራሱ እንኳን እድሜ ልክ ይፈጃል እንኳን የውስጥ ሀሳቡን ልታውቂ የማትችዪውን ሌላ ሰው ማወቅ» ይለኛል ላውቀው እንደምፈልግ ስነግረው።
«እውነት ነው የሰው ልጅ ሙሉ በሙሉ ልታውቀው የምትችለው ፍጡር አይደለም። ግን ሁሉም ሰው የማይቀየሩ ወይም ቢቀየሩም ሙሉ በሙሉ የማይጠፉ መሰረታዊ የሆነ የማንነት ምሰሶ አለውኮ!»

«አትሳሳቺ! ፐርሰናሊቲ ካዳበርሽው የሚያድግ፣ ከተውሽው የሚሞት፣ ወይም በማህበረሰብ ሚዛን ጥሩ ወይም መጥፎ ከሆኑት ፅንፎች ከሌላው ሰው የሚቀዳ ነው። ሰው ማሰብ ካላቆመ በቀር ይቀየራል። እንደቁስ እዚህጋ አስቀምጬሃለሁ እና ከዝህችው አንተነትህ ፈቅ እንዳትል ልትዪው አትችይም! ያስባላ! ሰዎች ባላቸው የተለያየ ግንኙነት የሚጣሉት ለምን ይመስልሻል? በአብዛኛው በጊዜ ሂደት የሚመጣውን የዛኛውን ሰው ማንነት መቀበል ስለሚያቅታቸው ነው። ወንድ እና ሴት ይጋቡ እና ከአስር ዓመት በኋላ ይለያያሉ። ለምን ብትያቸው <ሳገባው የነበረው ዓይነት ሰው አይደለም> ትልሻለች ወይም ይልሻል። ከዓመታት በፊት የተመቸው ነገር ተመችቶት እንዲቀጥል ትጠብቃለች። የሌላን ሰው ለውጥ መቀበል አንወድም! ወደ ራሳችን ብናይ ግን በነዛ ዓመታት ራሳችንም ተለውጠናልኮ! ለምን ነገ ሊቀየር የሚችል እኔነቴን ለማወቅ ጊዜ ታባክኛለሽ? አወቅኩት ብለሽ ስታስቢ ተቀይሬ ብታገኚኝ ጊዜና ጉልበትሽን አባከንሽ ማለትም አይደል?»
ተውኩት። ያለፈውን የእምነት መሰረቱን ለማወቅ መቆፈሬን ተውኩት። ዛሬ ላይ ብቻ አተኮርኩ። አብሬው ስሆን ያለው አዲስ ላይ ብቻ አተኮርኩ። ዛሬ የትናንታችን ውጤት መሆኑን ልቤ እያወቀ ትናንትን ከእኔና ከእርሱ መሃከል አሽቀንጥሬ ጣልኩት። ትናንት ምን ያህል ቢገፉት አራሙቻውን በጣጥሶ ዛሬ ላይ የመንገስ አቅም እንኳን እንዳለው ልቤ እያወቀ። ትናንትን እንደአሮጌ ሸማ አጣጥፌ የማልከፍተው ያረጀ ሳጥን ውስጥ ቆልፌ ከአዲስ ጋር አዲስ ኑሮ ጀመርኩ።

ሽማግሌዎቼን ራሴ መርጬ አስላኩኝ። ሰርጌ ደመቀ። «አሁን ደመቅሽ የኛ ልጅ !» ተባለልኝ። በቤተሰባችን ታሪክ ያልታየ የተባለለትን ደማቅ ሰርግ ደገሰልኝ። «የማታ ትዳር ሰጣት » ተባለልኝ። ቆማ ቀረች ያለኝ ዘመድ አዝማድ «እንኳንም ታግሰሽ ጠበቅሽ! ትዕግስት ፍሬዋ …..» እያለ አገላብጦ ሳመኝ። «ውለዱ ክበዱ !» ተባልንልን! ላለመውለድ ላለመክበድ ፈርሜ እንደገባሁ አያውቁም! የቤተሰብ ቅልቅል፣ መልስ አንጃ ግራንጃውን « ቤተሰቦቹ እዚህ ሀገር አይደሉም!» እያልኩ ስዋሽ ከረምኩት። አዲስ ዝም ብሎ አላለፈኝም። በየመሃሉ ሀሳብ ከመስጠት አይቦዝንም። ግን ባይዋጥለትም ለእኔ ከማዘን ውጪ ቀኔን አላበላሸብኝም።

«ኸረ ተይ ሰዎች በህይወትሽ ውስጥ ያላቸውን ስልጣን ገደብ አበጂለት? ቤተሰቦችሽም ቢሆኑ ህይወትሽን የሚያማስሉበት ገደብ አለው። ዛሬ ለእነሱ ብለሽ ሰርግ ደገስሽ፣ አገባሽ፣ ዋሸሽ …… አያቆምምኮ አንቺ የማስቆም ሀሳብ ከሌለሽ» ብሎኝ ነበር የቅልቅሉ ቀን።
እኔም የተገላገልኩ መስሎኝ ነበር። ገና መጀመሪያው መሆኑ የገባኝ አግብቼ ብዙም ሳልቆይ ሁሉም በየፊናው <ሴት ልጅ ጠቢብ ናት። ያዝ ቆንጠጥ ማድረግ ልመጂ> አይነት የጨዋ የሚመስል ግን ሀብቱ በእጅሽ እያለ ስረቂው አይነት ምክር መምከር ሲጀምሩ፣ <ገንዘብ አይሰጥሽም እንዴ? ይሄን ያህል ሀብት ላይ እየዋኘሽ መዋዕለህፃናት የምታስተምሪው ለምንድነው?> ዓይነት ጥያቆዎች ሲጠይቁኝ ፣ <እንዴ እስከመቼ ነው? ለምን የግልሽ ስራ እንዲከፍትልሽ አትጠይቂውም?> እያሉ በእኔ ባል ገንዘብ ምን ቢከፍትልኝ እንደሚያዋጣኝ ትርፍ እና ኪሳራውን እያሰሉ እንቅልፍ ሲያጡብኝ ፣ በአመቱ «ምንድነው የምትጠብቂው ሁሉ እያላችሁ ልጅ የማትወልዱት ለምንድነው?» እያሉ ሲነተርኩኝ ነው። ………. ገደብ እንደሌለው ገባኝ! እድሉን ከሰጠኋቸው ከባሌ ጋር የማደርገውን የአልጋ ልፊያ ፖዝሽን እንምረጥልሽ እንደሚሉኝ ገባኝ።

በተጋባን በወራት ውስጥ አዲስ ለቤተሰቦቼ በሀሳባቸው እንኳን ሽው ብሎ ሊያውቅ የማይችል ትልቅ ዘመናዊ ቤት ገዛልኝ። አባቴ ስምንት ልጅ ወልዶ ያሳደገበትን የቀበሌ ቤት ያስረከበ ቀን ቀበሌ ለሚሰሩት ለእያንዳንዳቸው እየዞረ « ህልም የመሰለ ቤት ልጄ ገዛችልኝ! ልጅ ማለት እንዲህ ነውይ!» እያለ የቤቱን ፎቶ ሲያሳያቸው ዋለ። ትምህርት ቤት በተጠራ ቁጥር «አንቺ መቼም እኔን ከማዋረድ የተሻለ ስራም የለሽ። ደግሞ ምን አጥፍተሽ ነው?» ያለኝን እልፍ ቀን በዝህች አንድ ቀን ሙገሳ አጣፋሁት!! እማዬ ቤቴን መርቁልኝ ብላ ጎረቤቶቿን እና ገጠር ያሉ ዘመዶቿን ሁላ ሳይቀር ጠርታ አዲሷ ቤቷ ውስጥ ከአንድ ክፍል ወደሌላው ክፍል ሽር ብትን እያለች «እልልልልልልል እንደው ልጄ በመድከሚያዬ ማረፊያዬን እንዳሳመርሽልኝ ትዳርሽን ያሳምርልሽ!» እያለች ስትመርቀኝ ዓለሜ የሞላ መሰለኝ። በቃ ከዚህ በኋላ ለእነርሱ ኩራት ለመሆን መንፈራገጤን የማቆም መስሎኝ ነበር።

«ራስሽ ለማቆም ካልወሰንሽ ማብቂያ የለውም! የሆነ ቦታ መወሰን ካልቻልሽ ሁሌም እነሱን ለማስደሰት ብቻ ነው የምትኖሪው።» የሚለኝ የአዲስ ቃል እየቆየ ነው የሚገባኝ። ምንም ቢጠይቁኝ <እንቢ> <አልችልም> ማለት ሲያቅተኝ። ሁሌም «የእኔ ልጅኮ!» ለመባል የማይቻለውን ለመቻል ስዳክር፣ እየቆየ <ይሄን አሁን ማድረግ አልችልም! ጊዜ ስጡኝ> ስል ማኩረፍ ሲዳዳቸው፣ አለፍ ሲልም <ቤተሰብሽን እንኳን ለመርዳት ካልቻልሽ እያዩ የማይበሉት ሀብት ለጉራ ካልሆነ ምን ይሰራል?> አይነት ወቀሳ ጣል ሲያደርጉ ሳልፋቸው፣ ለቤተሰብ እና ለዘመድ ከማደርገው መቶ ነገር ይልቅ አንድ ያላደረግኩት ሲቆጠርልኝ ፣ ላደረግኩት እልፍ ነገር ከመመስገን ይልቅ ላላደረግኩት አንድ ነገር ዓመቱን ሙሉ ስረገም ……. ዘግይቶም ቢሆን ገባኝ። የተባረኩኝ ልጅ ወይም ጥሩ እህት መሆኔን ለእነሱ ለማስመስከር ስዳክር ጉልምስናዬ ላይ መድረሴ ሳያንስ ራሴን ለማስደሰት ሳልኖር ላረጅ መሆኑን አወቅኩ። ማድረግ ከምችለው በላይ ራሴን ላለማስጨነቅ ወሰንኩ። የምችለውን በእነሱ ለመሞገስ ሳይሆን ለነሱ ማድረግ በመቻል ውስጥ ስላለው እርካታ ስል አደርጋለሁ።
አዲስ ገንዘብን በተመለከተ ስግብግብ የሚባል ሰው አይደለም። ያለምክንያት ግን ሽራፊ ሳንቲም አያወጣም። አንደኛውን የባንክ አካውንቱን በሁለታችን ስም አድርጎታል። ከ50 ሺህ ብር በላይ ማውጣት ስፈልግ ግን የግድ እሱ መፈረም አለበት። በራሴ ምክንያት ከፍ ያለ ገንዘብ አውጥቼ አላውቅም። ሁሌም በቤተሰብ ምክንያት ነው። ካላሳመነው አይስማማም። ካሳመነው ዝም ይላል። አንዳንዴ ሲመስለኝ ባይዋጥለትም ለእኔ ብሎ ያልፈኛል።

ከቤተሰቦቼ አዙሪት ውጪ ትዳሬ እንደተለመዱት የትዳር አይነቶች ቅርፅ ሳይዝ ቀጠለ። በፍቅር ወይም በተለመደው የትዳር ህግ ሳይሆን የሚተዳደረው ራሳችን በተስማማንባቸው ህጎች ነው። ያልፃፍናቸው ግን የተስማማንባቸው ብዙ ህጎች አርቅቀናል። በትንሹ ሀኒ፣ ቤቢ፣ ማሬ ውዴ የሚሉትን የቁልምጫ ቃላቶች ካለመጠቀም ጀምሮ ልጅ እስካለመውለድ ድረስ……..ያለፈ ህይወታችንን (አንደኛው አካል ፈቃደኛ ሆኖ መናገር እስካልፈለገ ድረስ) ለመቆፈር ምንም አይነት እርምጃ ካለማድረግ እስከ አንደኛው አካል ትዳሩን ለቆ ለመሄድ በፈለገው ጊዜ መብቱ እንደሚከበርለት። ብዙ ህጎች …….. ሁለታችንም ያልገባን ወይም ማመን ያልፈለግነው ህግን የሚጥስ ስሜት መኖሩን ነው። ሳላውቀው፣ ሳላሰላ፣ ምንም አይነት ሂሳብ ሳልሰራ ህግ ጣስኩ።
ዛሬ ላይ ለምቀጣው ቅጣቴ ሁላ ጥፋቴ ያ ነበር………. አብሬው ስኖር ያወቅኩትን አዲስ በአዕምሮዬ ትግል የልቤን ስሜት አሸንፌ አለመውደድ አቃተኝ። በእያንዳንዷ ቀን አፍኜ እስከማልይዘው ድረስ ፍቅሩ ልቤ ውስጥ ተቆለለ። መቼ እንደሆነ አላውቅም ብቻ ግን የሆነኛው ቀን ላይ እሱ ልብ ውስጥ ለመቀመጥ ምንም ነገር መስዋዕት የማደርግ አቅመ ቢስ ሆኜ ራሴን አገኘሁት። ይኸው ነበር ጥፋቴ! እንዳገባው ለራሴ ለማሳመን ምክንያቶችን የደረደርኩለትን ሰው እንዳላጣው የትኛውን ምክንያት እንደማደረጅ ቸገረኝ።
«ምንድነው?» አለኝ የሆነ ቀን ማታ ልንተኛ ወደአልጋችን ሄደን እየተሳሳምን አቋርጦኝ።
«ምኑ?» አልኩት ግራ ገብቶኝ
«አሁን የሳምሺን መሳም! ልክ ያልሆነ ነገር አለው።» አለኝ።
ያለው ገብቶኛል። <አዎ ፍቅር አለበት> ብለው ደስ ይለኝ ነበር። ምላሹ ምን እንደሚሆን ልቤ አስቀድሞ አውቆ ነው መሰለኝ ፈራሁት። ባሌን ፣ አብሬው ኑሮ የምጋራውን አጋሬን፣ አቅፌው የምተኛውን ፍቅሬን፣ ምንም የማልደብቀውን የልብ ጓደኛዬን ……….. ማፍቀሬ በደል ሆነብኝ። ስለየትኛውም ስሜቴ ይዳኘኛል ብዬ የማላፍረውን ባሌን ፍቅሬን ዋሸሁት። ከንፈሮቹ እሱ እንደሚለው ከስሜት መጠቃቀም ልቀው መለኮታዊነት ያለበት ዓለም ውስጥ እንደሚከቱኝ መንገር አፈርኩ።

ሰይጣን ወይ እግዜር የጀመሩት… እኔ የቀጠልኩት (ክፍል ስምንት)

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...