የምግብ ቤት ባለቤት የሆነ ሰውየ :በደንበኞቹ መሀል ሲዘዋወር አንድ ዝነኛ ጋዜጠኛ ይመለከታል። ወድያው ባለቤትየው አስተናጋጂቱን ጠርቶ ” እዛ ጥግ ላይ የተቀመጠው ጋዜጠኛ ይታይሻል? ሂጅና የሚፈልገውን እየጠየቅሽ ተንከባከቢው!! ወጥ ካነሰው ጨምሪለት!! እንዲያውም ለኔ ራት ከተሰራው ዶሮ አንድ ቅልጥም ብትሰጪው ደስ ይለኛል። ሲያንሰው ነው!! እንዴት ያለ የሰላ ጭንቅላት ያለው ሰው መሰለሽ!!! የስራ ጫና የበዛበት ይመስላል። ደሞ ትንሽ እንደደበረው ፊቱ ያስታውቃል። እስቲ በኔ ሂሳብ አንድ ብርጭቆ ወይን ቅጂለት ። ድብርቱን ያባርርለታል!!”
” የደበረው ዛሬ ከስራው ስለተጫረ ነው ! ምፅ!” አለች አስተናጋጂቱ።
“የምርሽን ነው?”
” አርሴማ ምስክሬ ናት ”
የምግብ ቤቱ ባለቤት ድምፁን ከረር አድርጎ እንዲህ አለ: “እንደሱ አትይኝም ታድያ!! ይበለው!! እንደ ስራውማ ቢሆን ከቢሮው ብቻ ሳይሆን ካገር መባረር ነበረበት!! ይሄ ቀዳዳ!! የሽንትቤት አገልግሎት አይሰጡም እያለ ስንት ምግብ ቤቶችን በማዘጋጃቤት እንዲታሸጉ አድርጉዋል መሰለሽ? ይሄ አሰልጥ!! በይ አጠገቡ ቁሚና ብርጭቆና ማንኪያውን ወደ ቦርሳው እንዳይከት ባይነቁራኛ ተከታተይው።”
….
ሰውን በሰውነቱ መውደድ የሚባል ነገር በባህላችን ትርጉም አለው? ። ብዙ ጊዜ:ለሰዎች ፍቅርና ርህራሄ ፍቅርና አክብሮት የምናሳየው ይጠቅሙናል ብለን ካሰብን ነው። ምንም አያመጡም ብለን የምናስባቸውን ሰዎች ማክበር ይቸግረናል። ምንም አይሰጡንም ብለን የምናስባቸውን ሰዎች መውደድ ያቅተናል።
“እገሌ ሞተ አሉ የልቤ ወዳጅ
የሚያበላኝ ጮማ እሚያጠጣኝ ጠጅ”
ብላ ያለቀሰቺው ሴትዮ እንባ ያፈሰሰችው ለአቶ እገሌ አይደለም። ከአቶ እገሌ ሞት ጋር አብሮ ለሚቀረው ጠጅ እና ጮማ ነው።
እና አንዳንዴ :በግል ጥቅም ስሌት ላይ ያልተመሰረተ የሰውም ሆነ ያገር ፍቅር ይኖር ይሆን እላለሁ?
በባህላችን ሹመት አጥብቀን እንወዳለን ። ካቶ ሀዲስ አለማየሁ በቀር ስልጣን በሰፌድ ቀርቦለት “ይለፈኝ” ያለ በታሪክ አላቅም። ሹመት ባይደርሰን እንኩዋን : ልጆቻችንን “ተሾመ ” ነጋሲ : ሞቱማ ” እያልን በመሰየም ጥማችንን እናስታግሳለን ። በሹም ፊት ሞገስ ለማግኘት እድሚያችንን ክብራችንን አንዳንዴም ህይወታችንን እንገብራለን። ለተሾመ ሰው ያለን አክብሮት ወደ አምልኮ የተጠጋ የሆነውን ያህል : ለተሻረና ለተሸነፈ ሰው ርህራሄ አናቅም።
በታሪካችን: አንድ ሹም ከስልጣን ከወረደ ህይወቱን ያጣል። ህይወቱን ባያጣ የሰውነት ክብሩን ያጣል። በምድር ላይ መኖሩን የሚያስጠላ ውርደት ይጠግባል። በህይወት ተርፈው ስልጣን የለቀቁ አንዳንድ ነገስታት በከተማ ከመኖር በገዳም መንነው መኖር የሚመርጡት ለዚህ ይሆናል። ለምሳሌ እቴጌ ጣይቱ በስልጣን ላይ በነበሩ ጊዜ ” እቴጌ ጣይቱ እቴጌ ብርሃን” እየተባሉ ይሞገሱ ነበር። ከስልጣን ከተወገዱ በሗላ አድመኛው ጃንሜዳ ላይ ተሰብስቦ እንዳይሸጡ እንዳይለወጡ አድርጎ ዘለፋቸው።
እናም እቴጌይቱ ሲያስከብራቸው የኖረው ወንበራቸው እንጂ ሰብእናቸው አለመሆኑን ሲባንኑ-
” ከተቀመጥኩበት -ከስፍራየ ቢያጣኝ
“አንቱ ” ያለኝ ሁሉ -“አንቺ “ሊለኝ ቃጣኝ”
ብለው አንጎራጎሩ።
ተስፋ አንቁረጥ!! ሰውን በሰውነቱ ብቻ የሚገባውን ፍቅርና ክብር የሚሰጡ ሰዎች ቁጥራቸው ይነስ እንጂ በየዘመኑ በየቦታው መኖራቸው ያፅናናናል።
በድሮ ጊዜ ተደላ ጉዋሉ የተባለ ጌታ : አሉላ ተሰማ የተባለውን የስልጣን ተፎካካሪውን ማርኮ ይዞ መንቆረር ገበያ ላይ አርባ ገረፈው። ግርፊያውን ቆሞ እየተመለከተ ከሚዝናናው ገበያተኛ ማሃል – አንዲት ልበ-ብሩህ ባላገር እንዲህ ብላ በግጥም ሀሳቡዋን ገለፀች።
“ከጮማው አልበላሁ ከጠጁም አልጠጣሁ
አላውቀው አያውቀኝ
አሉላ ተሰማ ቢቀጣ ጨነቀኝ”
ውለታ ሳይቆጥሩ: ሳይውቁን ሳናውቃቸው :የሚጨነቁልንን ያብዛልን!!
One Comment
amen!!!