Tidarfelagi.com

ሰንኖር ማንም ሰንሞት ምንም!

በየቀኑ በሚባል ሁኔታ በታላላቅ አለማቀፍ የጥናትና ምርምር ተቋማት ፣ዩኒቨርስቲዎችና የትምህርት ኢኒስቲቲዩሽኖች ከመላው ዓለም የሚጋበዙ የሳይንስ ፣የሃይማኖት ፣ የኪነጥበብ ሰዎች የሚጋበዙባቸው ቁጥር ሰፍር የሌላቸው ሲንፖዚየሞች ዎርክሾፖች ይካሄዳሉ ! ዓለም በሙሉ እንዴት የተሻለ ዓለም እንፍጠር የሚል ሃሳብ በእያንዳንዱ ደይቃ ያወርዳል ያወጣል! ታዲያ እንደሰው በዚህ ሰፊ ዓለም ውሰጥ ኢትዮጲያ ምን እየሰራች ነው ለዓለም የምታበረክተው ከዓለምም የሚገባት ድርሻዋ ምንድነው ብሎ ማሰብ ጤናማ ነውና እጃችን ከምን ስንል መልሱ ይዘገንናል!

እውነቱን ለመናገር ባሁኑ ሰዓት ኢትዮጲያ የት ነው ያለችው ስንል የምናገኘው መልስ ‹‹ካርታ ላይ ብቻ ›› የሚል ይመሰለኛል! ፉከራችን ወንዝ አይሻገር ፣ ቋንቋችን ወንዝ አይሻገር ፣ ታሪክ ብለን የምንኮራበት ታሪክ ወንዝ አይሻገር ፣ ትምህርታችን ወንዝ አይሻገር ፣ ምግባችን ለራሳችን እንደምናጨበጭበው ወንዝ አይሻገር፣ እምነታችን ወንዝ አይሻገር ፣ቁንጅና እያልን የምናቆለጳጵሰው ቁንጅናችን ወንዝ አይሻገር ፣ ዓለም የት እንደደረሰ ከሚደፉብን ዝቃጭ ፊልሞቻቸውና ዜናዎቻችው ያለፈ ትክክለኛ ግንዛቤ የለን ፣ እነሱ እኛ የት እንዳለንም ምን እንደሆንም ከራሳቸው ጥቅም አንፃር ካልሆነ አያውቁን ! ቢመረንም ዓለም ከሚባለው ፈጣን ወንዝ በራሳችን ትንሽ መዓበል እና ስንፍና ራሳችንን አውጥተን አልባሌ ቦታ የጣልን ዜጎች ሁነናል!

እንደአንድ ኢትዮጲያዊ ሊያንገበግበን የሚገባው ጉዳይ እንደሰው መታየት ከምንችልበት ዓለም ዓቀፍ መድረክ እያለን አለመኖራችን ነው!! የራሳችን ቋንቋ ያለን ህዝቦች ግን የራሳቸው ቋንቋ ከሌላቸው ህዝቦች ጋር እንኳን ስንወዳደር እርስ በርሳችን መግባባት የማንችል ፍጥረቶች ! በቅኝ ግዛት ያልተገዛን ህዝቦች ግን በአሁኑ ሰዓት አካላዊም ስነ ልቦናዊም ባርነታችን ቅኝ መገዛትን የሚያስንቅ ህዝቦች!! እዛ ዘመናትን ተሻግረን አክሱም ፣ላሊበላ ከማለት ውጭ እንደትውልድ በኔ ዘመን ይሄን ሰራሁ ብለን የምንናገረው ቁራጭ ታሪክ የሌለን ህዝቦች!

አገራችን የትም ይሁን ታሪካችን ምንም ይሁን ፣ ፣ የምንወዳደርበት እውቀትና ብቃት ፣ የምንፎካከርበት እልህና እኔነት ፣ የምናሸንፍበት ቴክኖሎጅና የሰለጠነ የሰው ሃይል ፣ ሌሎችን የምንስብበት የተፈጥሮም ይሁን ሰው ሰራሽ ጥቅም ላይ የዋል ሃብት ከሌለን…. ሰንኖር ማንም ሰንሞት ምንም ነን!!

One Comment

  • Anonymous commented on September 29, 2019 Reply

    min waga alew

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...