Tidarfelagi.com

ሰሞንኛ ጨዋታ

ትናንት ቀለል ያለ ራት ለመብላት ፈለግሁ ፤ እናም” ባጫ ህንጻ “ውስጥ በሚገኘው የ”አማራ ባንክ” ቅርንጫፍ ጎራ ብየ በርከት ያሉ ሁለት መቶ ብሮችን ሸመጠጥሁ፤ ምግብ ቤት ገብቼ ፥ ምግቡ አላግባብ ውድ ከሆነብኝ ሂሳብ ለማካካስ ብዙ ነገሮች እጠቀማለሁ፤ ለምሳሌ ሬስት ሩም ገብቼ ለረጅም ጊዜ እቆያለሁ፤ ባጭሩ ፥ሬስት ሩምን ርስት ሩም አደርገዋለሁ፤ ያን ቀን ወደ ቤተ-ሰገራ ወሽንቤቱ ስራመድ መብራት ድርግምም አለ፤ ከግማሽ ሰአት የፈጀ ዘለግ ያለ ሽንት ሸንቸ ሳበቃ እያፍዋጨሁ ስወጣ የጽዳት ሰራተኛዋ፥
“ሴቶች ሽንት ቤት ውስጥ መሽናትህ የሚያሳፍር ነው” አለችኝ።
“በዚህ ጨለማ ፥ ኪችን ውስጥ ባለመሽናቴ ልታደንቂኝ ይገባል “ ስላት ፈገግ አለችልኝ ፤ (ግን ጨለማ ከሆነ ፈገግታዋ እንዴት ሊታየኝ ይችላል ? ሰው ምን ይለኛል አይባልም? )
ባጭር ጊዜ የሌለ ተመቻቸን፤ መጨረሻ ላይ ቁጥርሽ ስንት ነው?” ስላት፤ “ የጫማየ ወይስ የወገቤ” ብላ ስለመለሰችልኝ አጥብቆ ደበረኝ!
ድብርቴን ለማባረር የሚከተሉትን ሁለት ቀደዳዎች አስታወስኩ፥
ጉዋደኛየ ባለፈው ለአለቃው ‘ የሞተር መኪና አደጋ ስለደረሰብኝ ዛሬ መምጣት አልችልም “ ብሎ ለአለቃው መልክት ሰደደለት፤ አለቅየው “ ይገርማል፤ ዛሬ በጀት መዝጊያ ስለተቃረበ በመስርያ ቤታችን ውስጥ ሰርፕራይዝ ፓርቲ አዘጋጅተን ነበር ፤ ለሰራተኞች ዳጎስ ያለ የገንዘብ ስጦታም አሰናድተናል፤ እንዲሁም ዳጎስ ዳጎስ ያለ መቀመጫ ያላቸው ሴቶች ፓርቲውን ያደምቁታል ፤ በዚህ ዝግጅት ተሳታፊ ባለመሆንህ የተሰማኝ ደስታ ማለቴ ሀዘን ወሰን የለውም ፤ ለማንኛውም ነፍስ ይማር፤ I mean እግዜር ይማርህ” ብሎ መለሰለት፤
ግብዣው በመጦፍ ላይ እያለ ረፍት የጠየቀው ጉዋደኛየ እንደቆሰለ አርበኛ በሁለት ወንድሞቹ ግራናቀኝ ተደግፎ ከች አለ፤
አለቅየው እንዳየው ምን አለ ?
“እያመመው መጣ!“
በዙ ጊዜ የሰይፉ ሾውን ስመለከት የራሴን ፈጠራ ነስነስ አደርግበታለሁ፤ ባለፈው ሰይፉ የሀይሌ ገብረስላሴን ፊት ይዞ የተፈጠረ ሰውየ አቀረበ፤ ሰውየው ሀይሌን እንዳገኘው “ ወንድሜ ! ብሎ እንደበረኛ ተጠመጠመበት ፥
ሀይሌ;- ወል እንግድ ! በአርባ ደቂቃ ውስጥ ለሚ ኩራ ደርሰህ ከተመለስህ ወንድሜ መሆንህን እቀበላለሁ”
ሰውየው;- “ እሺ! አውቶቢስ ልያዝ ወይስ ራይድ ትጠሩልኛላችሁ? “
በመጨረሻ የዲኤን ኤ ምርመራ ተደርጎ ውጤቱ መጣ
ሰውየው ;- በምርመራው መሰረት ወንድምህ መሆኔ ተረጋግጧል ፥ የሆነ ነገር አታካፍለኝም?”
ሀይልሽ፤- ነገ ቢሮ ብቅ በልና የህይወት ልምዴን አካፍልሀለሁ”

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

One Comment

  • makonjo@yahoo.ca'
    አሌክስ commented on July 13, 2022 Reply

    በጣም አሪፍ ነው በርቱ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...