ከሀያ ዓመት በላይ የሆናቸው በወጣትነቷ ውዷ ከፃፈላት ደብዳቤዎች ዛሬም ድረስ አብረዋት ያሉ እያንዳንዱን በቃሏ የምታውቃቸው 23 የፍቅር ደብዳቤዎች አሏት። ሁሉንም ከነተፃፉበት ቀን ሳይቀር እኔም በቃሌ አውቃቸዋለሁ። እንደዚህ ከፍ ያለ ፍቅር መቋጫው እንዴት አስከፊ መለያየት እንደሆነ ሳስብ ይገርመኛል። እሷ ዛሬን ማሰብም መኖርም አትፈልግም። በትናንት ትዝታዋ ውስጥ ተወሽቃ ቀኖቿን መጨረስ ነው የምትፈልገው። እናቴ ያልገባት ነገር የሷን ትዝታ ስተዘትዝ የእኔም ቀኖች ከመድረሻቸው እየተቀነሱ እንደሆነ ነው።
“ቦስ ሰላም ነሽ?” ለሶስተኛ ጊዜ ስልክ ደውሎ ነው።
“ደህና ነኝ አልኩህ እኮ ፍትህ! ነገ እንገናኛለን። በቃ ደህና እደር!”
“እሺ ምግብ በልተሻል? አድራሻሽን ከነገርሽኝ ያለሽበት ላምጣልሽ?”
“ፍትህ ምግብ በልቻለሁ። ራሴን መንከባከብ አያቅተኝም። ባክህ እረፍ!”
ፍትህ ማለት በብዙ የሚያበሽቀኝ በበሽ የሚያበግነኝ ባህሪ ያለው ነው። ቢሯችንን የከፈትነው ከሁለት ምርጥ ጠበቆች ጋር በጋራ ነበር። አንደኛው ከወራት በፊት በግሉ ምክንያት ስራ ሲያቆም ፍትህን የቅርብ ጓደኛውና ጎበዝ ጠበቃ መሆኑን አሳምኖን ነው አብረን መስራት የጀመርነው።ፍትህ ቅንጡና ለብዙ ነገር ግድ የለሽ ነው። ለምን በየዕለቱ ቢሮ እንደሚገባም ሆነ ለምን ጠበቃ መሆን እንደፈለገ አይገባኝም። ምክንያቱም ለስራው ፍቅርም ትጋትም የለውም። ገንዘብ የሚያሳስበው ሰው እንዳልሆነ ለመገመት ደግሞ የሚጠቀማቸውን ቁሶችና አላስፈላጊ ወጪዎቹን ማየት በቂ ነው።
ከነገረስራው ሁላ ሴትን ልጅ ከአልጋ ወርዳ ማሰብ የሚከብደው ብሽቅ መሆኑ ያናድደኛል። ስማቸውን እንኳን በውል ከማያስታውሳቸው እልፍ ሴቶች ጋር ነው።
“ባል ሳታገቢ ነው የምታረጂው ታስታውቂያለሽ።” ይለኝ ነበር ስራ የጀመረ ሰሞን እራት ልጋብዝሽ ብሎኝ እንቢ ስላልኩት ሲያበሽቀኝ።
“አንቺ የሴት ልስላሴ የለሽም። ነገር ላይ እርርርር ትያለሽ። ጠብሰሽ ማወቅሽንም እንጃ።” ይለኛል በሌላ ቀን። ልስማው አልስማው ግድ የለውም ይለፈልፋል። ልቀየመው ልናደድበት ግድ የለውም አፉ እንዳመጣለት ነው የሚመርገው።
“አለቃ አለቃ መጫወት ትወጃለሽ። ሁሉም ቦታ ዋና አክተር መሆን አይደብርሽም?” ይለኛል በምንም ጉዳይ አስተያየት ልሰጠው ከሞከርኩ።
“በራስሽ ትመፃደቂያለሽ። ራስሽን ለዓለም ህዝብ እንደተላከ መሲህ ነው የምትቆጥሪው። ሁሌ ልክ እንደሆንሽ፣ ካንቺ በላይ አዋቂ እንደሌለ ነው የምታስቢው።……” ብሎኛል ጠጥቶ አድሮ የፍርድ ቤት ቀጠሮ ያመለጠው ቀን ልክ እንዳላደረገ ስነግረው። ለምን እንደሆነ አይገባኝም ብቻ የምሰራው ሁሉ አይዋጥለትም። እንደማንኛዋም ሴት መሆኔን ሳይጠቁመኝ አያልፍም። እኔን የሚናገርበት ስህተት ያገኘብኝ ከመሰለው አለቀልኝ። በነገር ሲተረኩሰኝ ይሰነብታል።
አባቴ ቢሮ መጥቶ ዓይኖቼ በእንባ ተሞልተው ሳወራው ካየኝ ቀን ጀምሮ የማውቀው ፍትህ አልሆነም። ምናልባት ግትርና ደንዳና የምትመስለው ሴትዮ ተሸንፋና ተመሳቅላ ስላያት የቆለላት ሴት ተንዳበት ግራ ገብቶታል ወይም ደካማ ጎኔን አውቆ ሊሳለቅ እየተከታተለኝ ነው አልያም አሳዝኜዋለሁ። ሁሉም እንዲሆኑ የማልፈልጋቸው ናቸው።
“ቦስ ቅድም አባትሽ መጥተው ነበር።” አለኝ ከፊቴ ላይ ስሜቴን እየዘገነ
“እና?” አልኩት ምንም ያልተሰማው ለመምሰል ዘና እያልኩ።
“እኔን ፈልገው ነው የመጡት። አንቺ ፍርድ ቤት መሆንሽን አስቀድመው አረጋግጠው ነው የመጡት።” አነጋገሩ ‘ምን ማድረግ እችል ነበር?’ የሚል አንድምታ አለው። ፀጥ አልኩ። ለሰከንዶች ጭንቅላቴ ረጭ አለ። ማሰብ አቆምኩ።
“ከእናትሽ ጋር መፋታት እንደሚፈልጉ እና አንቺ እንቢ ስላልሻቸው ሊያማክሩኝ ነበር። ጠበቃቸው እንድሆን ይፈልጋሉ።” የውብዳርን እናትሽ ማለቱ ብዙ እንዳላወሩ ገባኝ። …… ጭንቅላቴ ወና ስለሆነ የምጠይቀውም የማወራውም አልነበረኝም።
“የእህትሽን የሰርግ ካርድ ሰጥተውኝ ነው የሄዱት። እንዳልቀርና ብዙ የሚያጫውቱኝ ነገር… …” ቀጠለ…… “የሆነ ነገር በይኛ ቦስ?” ምን ልበለው? አትሂድ? እንደውም አባቴን አታናግረው? ለአባቴ ጠበቃው ከሆንክ ስለእኔ ብዙ ታውቃለህና ይቅርብህ? እናስ? ደከማ ጎኔ እንዳይታወቅ? ፍትህ እንዳያሸንፈኝ? በስራዬ የሚያውቁኝ ሁሉ የሚያውቋትን ጠንካራ እና በራሷ የምትተማመን ሴት ዙፋን ለማስጠበቅ?
ስራዬንም ቢሮዬንም እወደዋለሁ። ምክንያቱ ደግሞ ከቢሮዬ ውጪ ያለውን ፣ ያለፈውንና የሚመጣውን የማላስበው እዚህ ነው። እዚህ ሌላ ሴት ነኝ። አንድ ደራሲ መፅሃፍ ሲፅፍ የሚቀርፃቸውን ገፀ ባህሪያት ኑሮ ሲያበጅ ራሱን በፈጠራቸው ገፀ– ባህርያትና ዓለም ውስጥ የሚደብቅ ይመስለኛል። ለኔ ስራዬ እንደዛ ነው። በማገለግላቸው ደንበኞቼ ውድቀትና መነሳት ውስጥ ራሴን ደብቃለሁ። አንዳንዱ በመጠጥ አንዳንዱ በሌላ ሱስ ያደለው ደግሞ በሚወደው ሰው እና በፍቅር ውስጥ ራሱን እንደሚደብቀው።
ፍትህ የአባቴ ጠበቃ ሆነ ማለት ስለቤተሰቦቼ እኔ የማላውቀውንም ጉዳይ ጭምር አወቀ ማለት ነው። ያ ማለት ደግሞ ቢሮዬ ውስጥ የነበረኝ በራስ መተማመን እና ነፃነት ጠፋ ማለት ነው። ከዛ ቢሮ መግባት እጠላለሁ። ያኔ ራሴን የምሸሽግበት ቦታ አይኖረኝም። አደባባይ ተሰጣሁ ማለት ነው። ያኔ ለመንኮታኮት ተምዘገዘግኩ ማለት ነው።
“እና ትሄዳለህ? ማለቴ ሰርጉን?” አልኩት በመጨረሻ። ሰርጉ የድሮ ፍቅረኛዬና የእህቴ እንዳልሆነ ሁሉ እንደማንኛውም ‘ሰርጉን’ ብዬ
“ለምን እቀራለሁ?”
“ጠበቃው ልትሆን ወስነሃል ማለት ነው?”
“እንዳልቀበል የሚያደርገኝ ምክንያት አለሽ?”
“አይ ምክንያት የለኝም። ግን ባትቀበለው ደስ ይለኛል።”
“እኮ ለምን?” ለምንም ነገር ግድ የሌለው ሰው ይሄ ኬዝ እንዲህ ሀሳቡን የሰረቀው ከእኔ ጋር ስለተያያዘ ብቻ ነው። ለ‘ለምኑ’ መልስ የለኝም።